በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትርጉም ያለው ሕይወት—ኢየሱስ መንገዱን አሳይቶናል

ትርጉም ያለው ሕይወት—ኢየሱስ መንገዱን አሳይቶናል

‘ኢየሱስ በተመላለሰበት መንገድ ተመላለሱ።’1 ዮሐንስ 2:6

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ትርጉም ያለው ሕይወት ኖሯል። ስለዚህ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ከፈለግን የእሱን ምሳሌ መከተልና ምክሩን ማዳመጥ ይጠቅመናል።

ደግሞም ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ እንደሚያሳየው ይሖዋ ይህን እንድናደርግ ያሳስበናል። ኢየሱስ በተመላለሰበት መንገድ መመላለስ የእሱን ምሳሌና ትምህርት በመላ ሕይወታችን መከተልን ይጨምራል። እንዲህ ማድረጋችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንኖር ያስችለናል።

ኢየሱስ፣ እሱ በተመላለሰበት መንገድ እንድንመላለስ የሚረዱን መመሪያዎችን አስተምሯል። ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል አብዛኞቹ በሰፊው በሚታወቀው የተራራ ስብከቱ ውስጥ ይገኛሉ። እስቲ ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ጥቂቶቹን በመመርመር በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል እንመልከት።

መመሪያ፦ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”ማቴዎስ 5:3

ይህ መመሪያ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ሰዎች በተፈጥሯቸው መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግሯል። እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንፈልጋለን፦ የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? በምድር ላይ ይህን ያህል መከራ የበዛው ለምንድን ነው? አምላክ በእርግጥ ያስብልናል? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ልናገኝ የምንችለው ከአምላክ ቃል ብቻ እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) የአምላክ ቃል በእርግጥ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን እንድናረካ ያስችለናል?

እውነተኛ ታሪክ፦

ታዋቂ በሆነ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ዘፋኝ የነበረው ኢሳ የሮክ ሙዚቃ ኮከብ የመሆን አጋጣሚ ተከፍቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ኢሳ አንድ ነገር እንደጎደለው ይሰማው ነበር። “የሙዚቃ ቡድኑ አባል መሆን ያስደስተኝ የነበረ ቢሆንም ሕይወቴ ትርጉም እንዲኖረው እጓጓ ነበር” ብሏል። ይሁንና ኢሳ ከጊዜ በኋላ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘ። ኢሳ እንዲህ ብሏል፦ “የጥያቄ መዓት አዥጎደጎድኩበት። የሰጠኝ አሳማኝና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነ መልስ የማወቅ ጉጉቴን ስለቀሰቀሰው ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆንኩ።” ኢሳ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠና ያገኘው እውቀት ልቡን ስለነካው ሕይወቱን ለይሖዋ ለመወሰን ተነሳሳ። “ከዚህ በፊት በየጊዜው ችግሮችና አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ እገባ ነበር። አሁን ግን ዓላማ ያለው ሕይወት እመራለሁ” ብሏል። *

መመሪያ፦ “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው።”ማቴዎስ 5:7

ይህ መመሪያ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?

ምሕረት ማድረግ ለሌሎች ርኅራኄ፣ ደግነትና አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል። ኢየሱስ ለተቸገሩ ሰዎች ምሕረት አሳይቷል። በርኅራኄ ስሜት ተነሳስቶ ሰዎችን ከሚደርስባቸው መከራ ለመገላገል ማንም ሳይጠይቀው እርምጃ ወስዷል። (ማቴዎስ 14:14፤ 20:30-34) ምሕረት በማድረግ ረገድ የኢየሱስን አርዓያ ስንከተል ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ይኖረዋል፤ ምክንያቱም ምሕረት የሚያሳዩ ሁሉ ይህን በማድረጋቸው ደስተኛ ይሆናሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ለሌሎች ምሕረት ማሳየት እንችላለን፤ እንዲህ ስናደርግ የእኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እፎይታ ያገኛሉ። ምሕረት ማሳየት በእርግጥ የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል?

ማርያ እና ካርሎስ

እውነተኛ ታሪክ፦

ማርያና ባለቤቷ ካርሎስ ምሕረት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። የማርያ አባት ባለቤታቸውን በሞት ያጡ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል። በመሆኑም ማርያና ካርሎስ ወደቤታቸው አመጧቸው፤ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ ሁሉ ያደርጉላቸው  ጀመር። እነዚህ ባልና ሚስት እንቅልፍ ባይናቸው ሳይዞር የሚያድሩበት ጊዜ አለ፤ በተጨማሪም የማርያ አባት የስኳር በሽታቸው አደጋ ላይ ሲጥላቸው በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ይወስዷቸዋል። ማርያና ካርሎስ አንዳንድ ጊዜ በጣም እንደሚደክማቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደተናገረው ደስተኞች ናቸው፤ ምክንያቱም ለማርያ አባት አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረጋቸው ጥልቅ እርካታ አስገኝቶላቸዋል።

መመሪያ፦ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው።”ማቴዎስ 5:9

ይህ መመሪያ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?

ሰላም ፈጣሪ መሆን ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው? በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እየተሻሻለ ይሄዳል። “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። (ሮም 12:18) “ሰው ሁሉ” የሚለው አባባል የቤተሰባችንን አባላትና እምነታችንን የማይጋሩ ሌሎች ሰዎችን ይጨምራል። ታዲያ ‘ከሰው ሁሉ’ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይዞ መኖር ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል?

ናኢር

እውነተኛ ታሪክ፦

ናኢር የተባለችን የአንዲት ሴት ተሞክሮ እንመልከት። ለበርካታ ዓመታት ሰላሟን የሚፈታተኑ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከሰዎች በተለይ ደግሞ ከገዛ ቤተሰቧ አጋጥመዋታል። ከ15 ዓመት ገደማ በፊት ባሏ ትቷት የሄደ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልጆቿን ብቻዋን ስታሳድግ ቆይታለች። ከወንድ ልጆቿ መካከል አንዱ የዕፅ ሱሰኛ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጊዜ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል፤ እንዲሁም በእሷና በሴት ልጇ ላይ ዛቻ ይሰነዝራል። ናኢር ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘችው ትምህርት እንዲህ ባለው ፈታኝ ሁኔታ ሳይቀር ሰላማዊ ለመሆን የሚያስችላትን ጥንካሬ እንደሰጣት ታምናለች። አወዛጋቢ ጉዳዮች ሲነሱ ከሰዎች ጋር ላለመጨቃጨቅ ወይም ላለመጣላት ጥረት ታደርጋለች። ለሌሎች ደግ፣ አዛኝና አሳቢ ለመሆን ትጥራለች። (ኤፌሶን 4:31, 32) ሰላማዊ ስለመሆን ያገኘችው ትምህርት ከራሷ ቤተሰቦችና ከሌሎች ሰዎች ጋር በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራት ማስቻሉን ታምናለች።

የወደፊቱን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት

ኢየሱስ የተናገራቸውን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች የምንከተል ከሆነ ሕይወታችን ደስታና እርካታ የሞላበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ከፈለግን ስለ ወደፊቱ ጊዜም ማወቅ ያስፈልገናል። ደግሞስ ‘የሰው መጨረሻ ማርጀት፣ መታመምና መሞት ብቻ ነው’ የሚል አመለካከት ካለን ሕይወታችን ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? እርግጥ እነዚህ ነገሮች በዚህ ዓለም ላይ በተጨባጭ የምናያቸው እውነታዎች ናቸው።

ደስ የሚለው ነገር አንድ ምሥራች አለ! ይሖዋ ‘ኢየሱስ በተመላለሰበት መንገድ ለመመላለስ’ ጥረት ለሚያደርጉ ሁሉ፣ ብዙ በረከት አዘጋጅቷል። ይሖዋ በቅርቡ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ እንዲሁም እሱ ለሰው ዘሮች ባለው ዓላማ መሠረት ታማኝ የሆኑ ሰዎች ፍጹም ጤንነት አግኝተው ለዘላለም እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4

ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች በመጀመሪያው ላይ የተጠቀሱት ማርያ የተባሉ የ84 ዓመት አረጋዊት ይህ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። አንተስ? በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር ስለሚገኘው ‘እውነተኛ ሕይወት’ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገር ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ። *

^ စာပိုဒ်၊ 8 የኢሳን ታሪክ በዚህ መጽሔት ውስጥ በሚገኘው “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል—መጥፎ ባሕርይ ነበረኝ” በሚለው ርዕስ ላይ ማንበብ ትችላለህ።

^ စာပိုဒ်၊ 18 በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብዙ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍት ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚናገሩትን እንዲያውቁ አስችሏቸዋል።