ወደ አምላክ ቅረብ
‘እሱ የሕያዋን አምላክ ነው’
ሞት ከአምላክ የበለጠ ኃይል አለው? በፍጹም! ሞትም ሆነ ሌላ ማንኛውም ዓይነት “ጠላት” ‘ሁሉን ከሚችለው አምላክ’ የበለጠ ኃይል እንዴት ሊኖረው ይችላል? (1 ቆሮንቶስ 15:26፤ ዘፀአት 6:3) አምላክ ሙታንን ስለሚያስነሳ ከሞት የበለጠ ኃያል አለው፤ ደግሞም ወደፊት በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲህ እንደሚያደርግ ተስፋ ሰጥቷል። * ይህ ተስፋ በእርግጥ ይፈጸማል? የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ይህ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንድንጠባበቅ ያስችለናል።—ማቴዎስ 22:31, 32ን አንብብ።
ኢየሱስ፣ በትንሣኤ የማያምኑትን ሰዱቃውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ አምላክ የነገራችሁን አላነበባችሁም? ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ብሏል። እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ኢየሱስ ይህን ሐሳብ ሲናገር፣ በ1514 ዓ.ዓ. ገደማ አምላክ ለሙሴ በእሳት በሚንቀለቀለው ቁጥቋጦ አጠገብ የነገረውን እየጠቀሰ ነበር። (ዘፀአት 3:1-6) ይሖዋ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” በማለት ለሙሴ የተናገረው ሐሳብ ትንሣኤ መኖሩን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ኢየሱስ ጠቁሟል። ግን እንዴት?
በመጀመሪያ ታሪኩ የተፈጸመበትን ወቅት እንመልከት። ይሖዋ ከሙሴ ጋር ሲነጋገር አብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆብ ከሞቱ ብዙ ጊዜ ሆኗቸው ነበር፤ በዚህ ወቅት አብርሃም ከሞተ 329 ዓመታት፣ ይስሐቅ ከሞተ 224 ዓመታት እንዲሁም ያዕቆብ ከሞተ 197 ዓመታት አልፈው ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ‘አምላካቸው ነኝ’ እንጂ ‘አምላካቸው ነበርኩ’ አላለም። እነዚህ የእምነት አባቶች ቢሞቱም ይሖዋ ስለ እነሱ ሲናገር ሕያው እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል። ለምን?
ኢየሱስ ምክንያቱን ሲገልጽ “እሱ [ይሖዋ] የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” ብሏል። እስቲ ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው ለማሰብ ሞክር። ሙታን የማይነሱ ከሆነ አብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆብ ለዘላለም ከሞት ነፃ መውጣት ስለማይችሉ ይሖዋ የሙታን አምላክ ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ ሞት ከአምላክ የበለጠ ኃይል አለው ማለት ነው፤ በሌላ አባባል አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ከሞት ነፃ የማውጣት አቅም የለውም ማለት ነው።
ታዲያ አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን ጨምሮ ሌሎች በሞት ያንቀላፉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ኢየሱስ “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል። (ሉቃስ 20:38) ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹን ሕያዋን እንደሆኑ አድርጎ ማሰቡ እነሱን የማስነሳት ዓላማ እንዳለውና ይህ ዓላማው መፈጸሙ እንደማይቀር ያረጋግጣል። (ሮም 4:16, 17) ይሖዋ ገደብ የለሽ የማስታወስ ችሎታ ያለው በመሆኑ ታማኝ አገልጋዮቹን አይረሳም፤ እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ እንደገና ሕያው ያደርጋቸዋል።
ይሖዋ ከሞት እጅግ የላቀ ኃይል አለው
በሞት የተለዩህን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና ማግኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው ይሖዋ ከሞት እጅግ የላቀ ኃይል እንዳለው አስታውስ። አምላክ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ የሰጠው ተስፋ እንዳይፈጸም ሊያደርግ የሚችል አንዳች ነገር የለም። ታዲያ ስለ ትንሣኤ ተስፋና ይህን ተስፋ ስለሚፈጽመው አምላክ የበለጠ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? እንዲህ ማድረግህ ‘የሕያዋን አምላክ’ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ እንደሚረዳህ ጥርጥር የለውም።
^ စာပိုဒ်၊ 3 ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚከናወነው ትንሣኤ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።