በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የይሁዳ ወንጌል” ምንድን ነው?

“የይሁዳ ወንጌል” ምንድን ነው?

ሚያዝያ 2006፣ በመላው ዓለም የታተሙ ጋዜጦች አንድ አስገራሚ ዘገባ ይዘው ወጥተው ነበር፤ ዘገባው በቅርቡ በተገኘውና “የይሁዳ ወንጌል” የሚል ርዕስ ባለው ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ አንድ የምሁራን ቡድን ለሕዝብ ይፋ ሊያደርገው እንደሆነ የሚገልጽ ነበር። ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ ኢየሱስን ስለካደው ደቀ መዝሙር ማለትም ስለ ይሁዳ ባለን አመለካከት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ምሁራኑ መናገራቸውን ጋዜጦቹ ጠቅሰው ነበር። ምሁራኑ ይሁዳን ጀግናና የኢየሱስን ማንነት በትክክል የተረዳ ብቸኛው ሐዋርያ አድርገው የገለጹት ሲሆን ኢየሱስ እንዲገደል አሳልፎ የሰጠውም በራሱ በኢየሱስ ጥያቄ መሠረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በእርግጥ ይህ ጽሑፍ ጥንታዊ ነው? ከሆነ አስቆሮቱ ይሁዳን፣ ኢየሱስን ወይም የጥንት ክርስቲያኖችን በተመለከተ ተሰውሮ የቆየ እውቀት ይገልጥልን ይሆን? ስለ ክርስትና ባለን አመለካከት ላይስ ለውጥ ያመጣ ይሆን?

“የይሁዳ ወንጌል” መገኘት

“የይሁዳ ወንጌል” የተገኘው እንዴት እንደሆነ እስካሁን ድረስ በእርግጠኝነት አይታወቅም። ይህ ጽሑፍ በአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በቁፋሮ የተገኘ ሰነድ ሳይሆን በ1970ዎቹ መጨረሻ ወይም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጥንታዊ ዕቃዎች በሚሸጡበት ገበያ ላይ በድንገት ለሽያጭ ቀርቦ የተገኘ ነው። ጽሑፉ የተገኘው በ1978 ግብፅ ውስጥ በአንድ ባዶ መቃብር ምናልባትም በአንድ ዋሻ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ጽሑፉ በኮዴክስ (ጥንታዊ የመጽሐፍ ዓይነት ነው) ተዘጋጅተውና በኮፕቲክ (ከጥንታዊቷ ግብፅ የመጣ ቋንቋ ነው) ተጽፈው ከተገኙ አራት የተለያዩ ጽሑፎች አንዱ ነው።

ደረቅ በሆነው የግብፅ የአየር ጠባይ ምክንያት ለብዙ መቶ ዓመታት ተጠብቆ የቆየው ይህ በቆዳ የተጠረዘ ኮዴክስ ከዚያ ቦታ ከወጣ በኋላ በፍጥነት መበላሸት ጀመረ። በ1983 የተወሰኑ ምሁራን ኮዴክሱን ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩት ተደርጎ ነበር፤ ይሁን እንጂ የተጠየቀው ዋጋ የማይደፈር በመሆኑ የሚገዛው ሰው አልተገኘም። በቀጣዮቹ ዓመታትም ቢሆን በደንብ ስላልተያዘና በጥሩ ሁኔታ ስላልተቀመጠ ኮዴክሱ በፍጥነት መበላሸቱን ቀጠለ። በ2000 ላይ ደግሞ ጥንታዊ ዕቃዎችን የምትሸጥ አንዲት የስዊስ ነጋዴ ገዛችው። እሷም ከጊዜ በኋላ ይህን ኮዴክስ በማሲናስ ፋውንዴሽን አቭ ኤንሸንት አርት እና በናሽናል ጆኦግራፊክ ሶሳይቲ ሥር ለሚሠራ ከዓለም ዙሪያ ለተውጣጣ የምሁራን ቡድን አስረከበችው፤ ይህ ቡድን ኮዴክሱን ወደ ቀድሞ ይዞታው የመመለስ ፈታኝ ሥራ የተቀበለ ሲሆን በዚህ ወቅት የኮዴክሱ የተወሰነ ክፍል እየተበላሸ በመምጣቱ  ተበጣጥሶ ነበር። በተጨማሪም ይህ ቡድን የኮዴክሱን ዕድሜ ማወቅ እንዲሁም በውስጡ ያለውን ሐሳብ መተርጎምና ማብራራት ይጠበቅበት ነበር።

ካርቦን-14 የሚባለው የዕድሜ መለኪያ፣ ኮዴክሱ የሦስተኛው ወይም የአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ጽሑፍ ሳይሆን እንደማይቀር ማረጋገጫ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ምሁራኑ ከዚህ ጊዜ በጣም ቀደም ብሎ ይህ “የይሁዳ ወንጌል” የተሰኘው ጽሑፍ መጀመሪያ ከተጻፈበት ከግሪክኛ ቋንቋ ወደ ኮፕቲክ እንደተተረጎመ ገምተዋል። “የይሁዳ ወንጌል” የተጻፈበት መቼት ምን ይመስል ነበር?

“የይሁዳ ወንጌል”—የግኖስቲክ ወንጌል

“የይሁዳ ወንጌል” የሚባል ጽሑፍ መኖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ክርስቲያን እንደሆነ ይናገር በነበረውና የሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ደራሲ በሆነው በኢራንየስ ጽሑፍ ላይ ነበር። ኢራንየስ፣ አጌንስት ሄረሲስ (ፀረ መናፍቅነት) በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ትምህርታቸውን ከተቃወማቸው በርካታ ቡድኖች መካከል ስለ አንዱ የሚከተለውን ጽፏል፦ “ከዳተኛው ይሁዳ እነዚህን ነገሮች በደንብ ያውቅ እንደነበረ እንዲሁም ሌሎቹ ያላወቁትን እውነት እሱ ብቻ ስለሚያውቅ ሚስጥራዊ የሆነውን አሳልፎ የመስጠት ድርጊት እንደፈጸመ ይናገራሉ። በእሱ የተነሳ ሁሉም ነገሮች ማለትም ምድራዊና ሰማያዊ ነገሮች ትርምስምሳቸው ወጥቷል። የይሁዳ ወንጌል ብለው የሰየሙትን እንዲህ ያለ የፈጠራ ታሪክ አዘጋጅተዋል።”

“በይሁዳ ዘመን በኖረና እሱን በሚያውቅ ሰው የተጻፈ ወንጌል አይደለም”

የኢራንየስ ዋነኛ ዓላማ ከሌላው የተሰወረ እውነት ተገልጦልናል ብለው ያምኑ የነበሩ ግኖስቲክ ክርስቲያኖች የሚያስተምሯቸው የተለያዩ ትምህርቶች ስህተት መሆናቸውን ማስረዳት ነበር። ግኖስቲሲዝም የሚለው መጠሪያ የክርስትናን “እውነት” በሚመለከት የራሳቸው ግንዛቤ የነበራቸውንና ለዚህም ማብራሪያ የሚሰጡ ብዙ ቡድኖችን በአጠቃላይ ያመለክታል። ግኖስቲኮች በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደ አሸን በፈሉት ጽሑፎቻቸው በመጠቀም ትምህርታቸውን ማስፋፋት ቀጥለው ነበር።

እንደዚህ ያሉት የግኖስቲክ ወንጌሎች፣ ብዙውን ጊዜ ዋነኞቹ የኢየሱስ ሐዋርያት የእሱን መልእክት እንዳልተረዱትና ኢየሱስ የተመረጡ ጥቂቶች ብቻ ሊያስተውሏቸው የሚችሉ ሚስጥራዊ ትምህርቶችን እንዳስተማረ ይናገራሉ። * ከእነዚህ ግኖስቲኮች መካከል አንዳንዶቹ ይህ ዓለም የሰዎችን ነፍስ ጠፍሮ የሚይዝ እስር ቤት እንደሆነ ያምኑ ነበር። በዚህም የተነሳ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸው “ፈጣሪ አምላክ” እነሱ ከሚያምኑባቸው ፍጹም የሆኑ የተለያዩ አማልክት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ደረጃ እንዳለው ይናገራሉ። እንደነሱ አባባል ከሆነ የእውነተኛ “እውቀት” ባለቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ይህን “ሚስጥር” ስለሚገነዘብ ከሥጋዊ አካሉ ነፃ መውጣት ይፈልጋል።

“በይሁዳ ወንጌል” ውስጥ የተንጸባረቀው እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ነው። ወንጌሉ የሚጀምረው በሚከተለው ሐሳብ ነው፦ “ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ከማክበሩ ከሦስት ቀናት በፊት ለስምንት ቀናት ከአስቆሮቱ ይሁዳ ጋር ባደረገው ጭውውት ለእሱ የነገረው ሚስጥር።”

ይህ ኮዴክስ ኢራንየስ በጽሑፉ ላይ የጠቀሰውና ለብዙ ዘመናት እንደጠፋ ይታሰብ የነበረው ሰነድ ይሆን? ኮዴክሱን ለመጀመሪያ ጊዜ የመረመረውና የተረጎመው ቡድን አባል የነበረው ማርቪን ሜየር እንደተናገረው ኢራንየስ የሰጠው “አጭር መግለጫ የይሁዳ ወንጌል የሚል ርዕስ ከተሰጠው የኮፕቲክ ጽሑፍ ጋር በጣም ይስማማል።”

ይሁዳ የተገለጸበት መንገድ—ምሁራንን ያወዛገበ ጉዳይ

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን ነገር መረዳት ሲያቅታቸው በንቀት እንደሚስቅባቸው “በይሁዳ ወንጌል” ውስጥ ተገልጿል። እንዲሁም ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል ግን የኢየሱስን እውነተኛ ማንነት የተረዳው ይሁዳ ብቻ እንደሆነ ተጠቅሷል። በመሆኑም ኢየሱስ “የመንግሥቱን ሚስጥሮች” ለእሱ ብቻ እንደገለጠለት ተገልጿል።

ኢራንየስ ስለ ወንጌሉ የሰጠው መግለጫ የመጀመሪያውን ጽሑፍ በተረጎመው የምሁራን ቡድን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በምሁራኑ ትርጉም ውስጥ ይሁዳ በኢየሱስ እንደሚወደድ እንዲሁም ሚስጥሮችን የተረዳና ወደ ‘መንግሥቱ’ የሚገባ ብቸኛው ደቀ መዝሙር እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ይህ ወንጌል እንደሚናገረው የተሳሳቱት ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው ቢመርጡም እሱ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ‘በሙሉ የሚልቅ’ “አሥራ ሦስተኛ መንፈስ” ይሆናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ይሁዳን አስመልክቶ ሲናገር “ከላዬ ላይ ያለውን ሰብዓዊ አካል መሥዋዕት ታደርጋለህ” ብሏል።

 የጥንት ክርስትናና የግኖስቲሲዝም እውቅ ምሁራን የሆኑትና ከፍተኛ ሽያጭ ያገኙ መጻሕፍትን ያሳተሙት ባርት አርማን እና ኢሌን ፔጀልዝ “የይሁዳን ወንጌል” ከተረጎመው የመጀመሪያው ቡድን ጋር የሚመሳሰል ትንተናና ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ ወዲያውኑ አሳተሙ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እንደ ኤፕሪል ደኮኒክ እና ቢሪየር ፒርሰን ያሉ ሌሎች ምሁራን ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገለጹ። እነዚህ ምሁራን፣ ናሽናል ጆኦግራፊክ ሶሳይቲ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ለማግኘት ብቻ ብሎ የጥንቱን ጽሑፍ በችኮላ እንዳሳተመ ተናግረዋል። በተጨማሪም የቡድኑ አባላት ሥራቸውን ሚስጥር አድርገው ለመያዝ መስማማታቸውን በፊርማቸው ስላረጋገጡ፣ ጽሑፉ የተለመደውን አሠራር የተከተለ እንዳልሆነ ማለትም ከመታተሙ በፊት ሌሎች ምሁራን ሂስ እንዳልሰጡበትና ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር እንዳልተደረገበት ገልጸዋል።

ይህን ጽሑፍ ከመረመሩት ምሁራን መካከል . . . አንዳቸውም ቢሆኑ ጽሑፉ ትክክለኛ ታሪካዊ መረጃ እንደያዘ አልተናገሩም

ዴኮኒክ እና ፒርሰን በየፊናቸው ምርምር ካደረጉ በኋላ ቀደም ሲል የነበሩት ምሁራን፣ ቁርጥራጭ ከሆኑት የኮዴክሱ ያልተሟሉ ክፍሎች ውስጥ ዋና ዋና የሆኑትን በተሳሳተ መንገድ እንደተረጎሟቸው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ዴኮኒክ ባዘጋጀችው ትርጉም መሠረት ኢየሱስ ይሁዳን የጠራው “አሥራ ሦስተኛ መንፈስ” ብሎ ሳይሆን “አሥራ ሦስተኛ ጋኔን” ብሎ ነው። * በተጨማሪም ኢየሱስ ይሁዳ ወደ ‘መንግሥቱ’ እንደማይገባ በማያሻማ መንገድ ነግሮታል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ለይሁዳ የነገረው ከሌሎቹ ሐዋርያት ‘እንደሚልቅ’ ሳይሆን እንዲህ በማለት ነው፦ “አንተ ከሁሉም የከፋ ጥፋት ትሠራለህ። ምክንያቱም ከላዬ ላይ ያለውን ሰብዓዊ አካል መሥዋዕት ታደርገዋለህ።” እንደ ዴኮኒክ አመለካከት “የይሁዳ ወንጌል” የጥንቶቹ ግኖስቲኮች በሐዋርያት ላይ ለማሾፍ ያዘጋጁት ታሪክ ነው። ዴኮኒክ እና ፒርሰን በደረሱበት መደምደሚያ መሠረት “በይሁዳ ወንጌል” ውስጥ ይሁዳ ጀግና ተደርጎ አልተገለጸም።

“ከይሁዳ ወንጌል” ምን ትምህርት እናገኛለን?

ይህን ጽሑፍ ከመረመሩት ምሁራን መካከል አንዳንዶቹ ይሁዳን የተመለከቱት እንደ ጀግና ሌሎቹ ደግሞ እንደ ጋኔን ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ ጽሑፉ ትክክለኛ ታሪካዊ መረጃ እንደያዘ አልተናገሩም። ባርት አርማን እንዲህ ብለዋል፦ “በይሁዳ የተጻፈ ወንጌል አይደለም፤ ወይም ደግሞ በወንጌሉ ውስጥ በይሁዳ እንደተጻፈ የሚናገር ሐሳብ የለም። . . . እንዲሁም በይሁዳ ዘመን በኖረና እሱን በሚያውቅ ሰው የተጻፈ ወንጌል አይደለም። . . . በመሆኑም በኢየሱስ የሕይወት ዘመን ስለተፈጸሙ ነገሮች ተጨማሪ መረጃ የሚሰጥ መጽሐፍ አይደለም።”

“የይሁዳ ወንጌል” በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በግሪክኛ ቋንቋ የተጻፈ የግኖስቲኮች ጽሑፍ ነው። በቅርቡ የተገኘው “የይሁዳ ወንጌል” ኢራንየስ የጠቀሰው ጽሑፍ መሆን አለመሆኑን ምሁራን ገና እየተከራከሩበት ነው። ይሁንና “የይሁዳ ወንጌል” የሐሰት ክርስቲያኖች የራሳቸውን የውሸት ትምህርት በክርስትና ውስጥ በማስገባታቸው ምክንያት ክርስትና በተለያዩ ኑፋቄዎች የተከፋፈለበት ወቅት እንደነበረ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። በመሆኑም “የይሁዳ ወንጌል” በቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኝነት ላይ ጥያቄ የሚፈጥር ሳይሆን በሐዋርያት ሥራ 20:29, 30 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ያሉ ሐዋርያት የሰጧቸው ማስጠንቀቂያዎች መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ከሄድኩ በኋላ . . . ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ” ብሏል።

^ စာပိုဒ်၊ 11 እነዚህ ወንጌሎች የተሰየሙት የኢየሱስን እውነተኛ ትምህርቶች በተሻለ መንገድ ተረድተዋል ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ስም ነው፤ ለምሳሌ “የቶማስ ወንጌል” እና “የመግደላዊት ማርያም ወንጌል” ተብለው የሚጠሩ ጽሑፎች አሉ። በአጠቃላይ 30 የሚያህሉ እንዲህ ዓይነት ጥንታዊ ጽሑፎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

^ စာပိုဒ်၊ 18 “በይሁዳ ወንጌል” ውስጥ ይሁዳ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በተሻለ መንገድ የኢየሱስን ማንነት ለይቶ ያወቀ ጋኔን እንደሆነ የሚሰማቸው ምሁራን ይህ ሁኔታ አጋንንት የኢየሱስን ማንነት በትክክል እንደገለጹ ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ የወንጌል ዘገባዎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።—ማርቆስ 3:11፤ 5:7