በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙሴ—የእምነት ሰው

ሙሴ—የእምነት ሰው

እምነት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “እምነት” ስለሚለው ቃል ሲናገር ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ ላይ በተመሠረተ ነገር ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆንን ሊያመለክት ይችላል። በአምላክ ላይ እምነት ያለው ሰው፣ ፈጣሪ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም ይተማመናል።

ሙሴ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

የሙሴ ሕይወት ያተኮረው አምላክ ቃል በገባቸው ተስፋዎች ላይ ነበር። (ዘፍጥረት 22:15-18) በግብፅ የቅንጦት ኑሮ የመምራት አጋጣሚ የነበረው ቢሆንም ይህን አጋጣሚ የተወ ሲሆን “በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ።” (ዕብራውያን 11:25) ሙሴ ይህን ውሳኔ ያደረገው በስሜት ተነሳስቶ ነበር? በኋላስ ባደረገው ውሳኔ ተቆጭቶ ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል” ይላል። (ዕብራውያን 11:27) ሙሴ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ባለው እምነት ተነሳስቶ ባደረጋቸው ውሳኔዎች ፈጽሞ አልተቆጨም።

ሙሴ ከራሱ አልፎ የሌሎችን እምነት ለማጠናከርም ጥረት ያደርግ ነበር። እስራኤላውያን በፈርዖን ሠራዊትና በቀይ ባሕር መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስሉ በነበረበት ጊዜ የሆነውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስራኤላውያን የማያመልጡት እልቂት ከፊታቸው እንደተደቀነ በተሰማቸው ወቅት በጣም ስለፈሩ ወደ ይሖዋና ወደ ሙሴ ጮኹ። ሙሴ ምን ያደርግ ይሆን?

አምላክ ለእስራኤላውያን ማምለጫ መንገድ ለመክፈት ሲል ቀይ ባሕርን ለሁለት ሊከፍል እንደሆነ ሙሴ ላያውቅ ይችላል። ይሁንና ሙሴ፣ አምላክ ሕዝቡን ለማዳን የሆነ ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነበር። ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያንም የእሱ ዓይነት እምነት እንዲኖራቸው ፈልጎ ነበር። ሙሴ ሕዝቡን “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ” አላቸው። (ዘፀአት 14:13) ሙሴ የሕዝቡን እምነት ለማጠናከር ያደረገው ጥረት ተሳክቶለት ይሆን? እንዴታ! ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙሴ ብቻ ሳይሆን ስለ ሁሉም እስራኤላውያን ሲናገር “በደረቅ ምድር እንደሚሄዱ ሆነው ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ” ይላል። (ዕብራውያን 11:29) የሙሴ እምነት የጠቀመው ራሱን ብቻ ሳይሆን በይሖዋ ላይ እምነት ማድረግ የጥበብ እርምጃ መሆኑን የተገነዘቡትን ሁሉ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሕይወታችን አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ሙሴን መምሰል እንችላለን። ለምሳሌ አምላክ፣ በሕይወታችን ውስጥ ለእሱ አምልኮ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን እንደሚያሟላልን ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:33) እውነት ነው፣ በዛሬው ጊዜ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘውን ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት የመስጠት አባዜ መቋቋም ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ ቀላል ሕይወት በመምራት በአምልኳችን ላይ ትኩረት ካደረግን ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያቀርብልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ዋስትና ሰጥቶናል።—ዕብራውያን 13:5

በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በአምላክ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ጥሩ አጋጣሚ እንዳላቸው ይገነዘባሉ። ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አምላክ እንዳለ እንዲሁም ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች መሥፈርቶች እንደሰጠን የሚገልጸው እጅግ አስፈላጊ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ብቻ ሳይሆን የአምላክን መሥፈርቶች መከተል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መንገድ እንደሆነም ሊያምኑ ይገባል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሊሰጧቸው የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ስጦታ አምላክ “መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ” መሆኑን እንዲያምኑ መርዳት ነው።—ዕብራውያን 11:6