በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙሴ—አፍቃሪ ሰው

ሙሴ—አፍቃሪ ሰው

ፍቅር ምንድን ነው?

ፍቅር ምንድን ነው? ፍቅር፣ ጥልቅ የመውደድ ስሜት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ፍቅር ያለው ሰው የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ቢጠይቅበትም እንኳ ለሚወዳቸው ሰዎች ያለውን ስሜት በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ያሳያል።

ሙሴ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

ሙሴ ለአምላክ ፍቅር እንደነበረው አሳይቷል። በምን መንገድ? አንደኛ ዮሐንስ 5:3 “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው” እንደሚል አስታውስ። ሙሴም አምላክን ስለሚወድ እሱ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ፈጽሟል። ሙሴ አምላክ የጠየቀውን ነገር ሁሉ አድርጓል፤ በቀይ ባሕር ላይ በትሩን እንዲዘረጋ የተሰጠውን ቀላል ትእዛዝ ጨምሮ ኃያል በሆነው ፈርዖን ፊት እንዲቀርብ የተሰጠውን አስፈሪ ተልእኮ ፈጽሟል። ሙሴ የሚሰጠው ትእዛዝ ቀላልም ይሁን ከባድ ምንጊዜም አምላክን ይታዘዝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” ይላል።—ዘፀአት 40:16

ሙሴ ወገኖቹ ለሆኑት እስራኤላውያንም ፍቅር እንደነበረው አሳይቷል። ሕዝቡ ይሖዋ እነሱን ለመምራት በሙሴ እንደሚጠቀም ስለተገነዘቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ይዘው ወደ እሱ ይመጡ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ” ይላል። (ዘፀአት 18:13-16) የእስራኤላውያንን ችግር ቀኑን ሙሉ ሲያዳምጡ መዋል ለሙሴ ምን ያህል አድካሚ ሊሆን እንደሚችል አስብ! ሆኖም ሙሴ ሕዝቡን ይወድ ስለነበር እነሱን በመርዳቱ ደስተኛ ነበር።

ሙሴ የሕዝቡን ችግር ከማዳመጥ አልፎ ስለ እነሱ ጸልዮአል። ላሳዘኑት ሰዎች ጭምር ጸልዮአል! ለምሳሌ የሙሴ እህት ማርያም በሙሴ ላይ ስታጉረመርም ይሖዋ በለምጽ መትቷት ነበር። ሙሴ፣ ማርያም ላይ በደረሰው ቅጣት ከመደሰት ይልቅ ወዲያውኑ “አምላክ ሆይ፤ እባክህ ፈውሳት” በማለት ጸልዮላታል። (ዘኍልቍ 12:13) ሙሴ እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ስሜት የተንጸባረቀበት ጸሎት እንዲያቀርብ ያነሳሳው ከፍቅር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ምን ትምህርት እናገኛለን?

ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር በማዳበር የሙሴን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እንዲህ ያለው ፍቅር አምላክን “ከልብ” እንድንታዘዘው ያነሳሳናል። (ሮም 6:17) ይሖዋን ከልባችን ስንታዘዝ ልቡ ደስ ይለዋል። (ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም እንዲህ ማድረጋችን ለራሳችን ጥቅም ያስገኝልናል። አምላክን ከልብ በመነጨ ፍቅር ተነሳስተን ስናገለግል ትክክል የሆነውን ነገር እናደርጋለን፤ በተጨማሪም ይህን በማድረጋችን ደስታ እናገኛለን!—መዝሙር 100:2

ሙሴን የምንመስልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ማዳበር ነው። ለወዳጆቻችን ወይም ለቤተሰባችን አባላት ፍቅር ካለን የሚያሳስባቸውን ነገር ሲነግሩን (1) ከልብ ትኩረት ሰጥተን እናዳምጣቸዋለን፤ (2) ችግራቸውን እንደራሳችን ችግር አድርገን እንመለከታለን፤ እንዲሁም (3) እንደምናስብላቸው እንገልጽላቸዋለን።

እንደ ሙሴ ሁሉ እኛም ለምንወዳቸው ሰዎች መጸለይ እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ችግራቸውን ሲያዋዩን ልንረዳቸው ባለመቻላችን እናዝን ይሆናል። እንዲያውም “ልረዳህ ባለመቻሌ በጣም ነው የማዝነው። በጸሎቴ ግን አስብሃለሁ” እንል ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘የጻድቅ ሰው ጸሎት ታላቅ ኃይል እንዳለው’ ፈጽሞ አትዘንጋ። (ያዕቆብ 5:16) መጸለያችን ይሖዋ ምናልባት ባንጸልይ ኖሮ ለግለሰቡ የማያደርገውን ነገር እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል። ታዲያ ለምንወዳቸው ሰዎች፣ ከመጸለይ የበለጠ ምን ነገር ልናደርግላቸው እንችላለን? *

ታዲያ ከሙሴ ብዙ ነገር መማር እንችላለን ቢባል አትስማማም? ሙሴ እንደ ማናችንም ዓይነት ሰው ቢሆንም እምነት፣ ትሕትናና ፍቅር በማሳየት ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ ይሆነናል። እሱ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ በመከተል ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በተሻለ መንገድ መጥቀም እንችላለን።—ሮም 15:4

^ စာပိုဒ်၊ 8 አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን ከመሥፈርቶቹ ጋር ተስማምተን ለመኖር ልባዊ ጥረት ማድረግ አለብን። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።