በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ

ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ

“ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!”—መዝሙር 133:1

አንዳንዶች ገናን የሚያከብሩበት ምክንያት

እስራኤላውያን በሙሉ የያዕቆብ ወይም የእስራኤል ዝርያዎች በመሆናቸው ‘ወንድማማቾች’ ወይም የአንድ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። በበዓላት ወቅት በኢየሩሳሌም ሲሰበሰቡ የሚኖረው ሁኔታ “መልካም” እና ‘ደስ የሚያሰኝ’ ነበር። ልክ እንደ እነሱ ሁሉ በዛሬው ጊዜም ብዙ ቤተሰቦች አንድ ላይ ተሰባስበው “መልካም” እና ‘ደስ የሚያሰኝ’ ጊዜ ለማሳለፍ የሚችሉበትን የገና በዓል ወቅት በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ይህን ማድረግ ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ክሪስማስ ኤንድ ኒው ይርስ ሴሌብሬሽንስ እንዲህ ይላል፦ “ዓመቱን በሙሉ ተዳፍነው የቆዩ አንዳንድ የቤተሰብ አለመግባባቶች ገንፍለው የሚወጡት አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቡ ለበዓል አንድ ላይ ሲሰባሰብ ነው።”

ሊረዱን የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች

‘ለወላጆቻችሁና ለአያቶቻችሁ የሚገባቸውን ብድራት ክፈሉ።’ (1 ጢሞቴዎስ 5:4) በተቻለ መጠን ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አዘውትራችሁ ተጠያየቁ። ዘመዶቻችሁ የሚኖሩት ሩቅ ቢሆንም እንኳ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስልክ በመደወል፣ የኢ-ሜይል መልእክት በመላክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት በማውራት አዘውትራችሁ ልትገናኙ ትችላላችሁ። በየጊዜው የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችሁ አለመግባባቶችን ለመቀነስ ይረዳል።

“ጥልቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ ልባችሁን አጥብባችሁብናል። . . . ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።” (2 ቆሮንቶስ 6:12, 13) በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገናኙ ዘመዳሞች በተለይም ልጆች እንደ ባዕድ ሊተያዩ ይችላሉ። አንዳንድ ልጆች ከአያቶቻቸው ወይም ከሩቅ ዘመዶቻቸው ጋር እምብዛም አይቀራረቡም። እንግዲያው ልጆቻችሁ ለአረጋውያን ዘመዶቻቸውም ጭምር ፍቅር በማሳየት ‘ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ’ አበረታቷቸው። * ልጆች ከአረጋውያን ጋር አዘውትረው ጊዜ ማሳለፋቸው በዕድሜ ለሚበልጧቸው ሰዎች አሳቢነት እንዲያሳዩና ለእነሱ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።

“ተገቢውን ቃል በተገቢው ጊዜ መናገር በጣም ያስደስታል።” (ምሳሌ 15:23 ኒው ሴንቸሪ ቨርዥን) ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ወይም አለመግባባት በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት እንዳይፈጥሩ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ያሳሰቧችሁን ጉዳዮች ለመወያየት ‘ተገቢውን ጊዜ’ መምረጥ ነው። ከቤተሰባችሁ አባላት ጋር አዘውትራችሁ የመወያየት ልማድ ካላችሁ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በግለሰብ ደረጃ በመነጋገር ችግሩን መፍታት ቀላል ይሆንላችኋል፤ ይህም አንድ ላይ ስትሰባሰቡ “መልካም” እና ‘ደስ የሚያሰኝ’ ጊዜ ለማሳለፍ ያስችላችኋል።

^ စာပိုဒ်၊ 9 በይሖዋ ምሥክሮች በሚዘጋጀው ንቁ! መጽሔት የግንቦት እና የሰኔ 2001 እትሞች ላይ የወጡትን “አያቶቼን በቅርብ ላውቃቸው የሚገባኝ ለምንድን ነው?” እንዲሁም “ከአያቶቼ ጋር ይበልጥ መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።