በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስን ማስታወስ

ኢየሱስ ክርስቶስን ማስታወስ

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”—ሉቃስ 22:19

አንዳንዶች ገናን የሚያከብሩበት ምክንያት

አንዳንዶች ገና የሚከበረው ኢየሱስን ለማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ገናን የሚያከብሩት ልደቱን ለማስታወስ ነው።

ይህን ማድረግ ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ተወዳጅ የሆኑ የገና ሙዚቃዎችና ከገና ጋር የተያያዙ ብዙ ልማዶች ሰዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያስቡ የሚያደርጉ አይደሉም። በዓሉን የሚያከብሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእሱ አያምኑም፤ እንዲያውም አንዳንዶች በምድር ላይ እንደኖረ እንኳ ይጠራጠራሉ። በንግዱ ዓለም ደግሞ ገና፣ ስለ ኢየሱስ የሚታሰብበት ወቅት መሆኑ ቀርቶ ሸቀጦች የሚተዋወቁበት ጊዜ እየሆነ ነው።

ሊረዱን የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች

“የሰው ልጅ . . . የመጣው በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት [ነው]።” (ማርቆስ 10:45) ኢየሱስ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ የተናገረው በልደቱ ቀን ሳይሆን ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚያ ምሽት ኢየሱስ ሞቱን ለማሰብ የሚያስችል በዓል ያቋቋመ ሲሆን ስለ አከባበሩም ቀላል የሆነ መመሪያ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከልደቱ ይልቅ ሞቱን እንዲያስታውሱ የፈለገው ለምን ነበር? ምክንያቱም ኢየሱስ ያቀረበው ቤዛዊ መሥዋዕት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ይናገራል። (ሮም 6:23) በመሆኑም የኢየሱስ ተከታዮች በየዓመቱ የሞቱን መታሰቢያ ያከብራሉ፤ በዚህ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስቡት እንደ አንድ አራስ ሕፃን ሳይሆን “የዓለም አዳኝ” እንደሆነ አድርገው ነው።—ዮሐንስ 4:42

“ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል።” (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስን ማክበርና ማስታወስ እንድትችል እሱ ፍጹምና አስተዋይ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲኖር የተወውን ምሳሌ መማር ይኖርብሃል። በተጨማሪም ኢየሱስ ርኅራኄና ትዕግሥት እንዲሁም ትክክል የሆነውን ለማድረግ ድፍረት በማሳየት ረገድ በተወው አርዓያ ላይ አሰላስል። እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ እሱን መምሰል የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ።

“የዓለም መንግሥት የጌታችንና የመሲሑ መንግሥት ሆነ፤ እሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።” (ራእይ 11:15) ኢየሱስ ክርስቶስን በምታስታውስበት ጊዜ አሁን ምን እያደረገ እንዳለ አስብ። ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው። የአምላክ ቃል ኢየሱስን አስመልክቶ “ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 11:4) እነዚህን ማራኪ ባሕርያት ሊያንጸባርቅ የሚችለው አንድ ኃያል ገዢ እንጂ አራስ ሕፃን አይደለም።