በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

በአምላክ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ተጽፈሃል?

በአምላክ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ተጽፈሃል?

ይሖዋ አገልጋዮቹ እሱን ለማስደሰት የሚያደርጉትን ጥረት ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታል? አዎን! ይሁንና ይሖዋ የሚመለከተው አገልጋዮቹ እሱን ለማወደስ የሚያከናውኑትንና የሚናገሩትን ነገር ብቻ አይደለም። አገልጋዮቹ ስለ እሱ የሚያስቡትን መልካም ነገርም ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዲሁም ያከናወኑትን ነገር ፈጽሞ አይረሳም። እንደዚህ ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? ነቢዩ ሚልክያስ ያሰፈረው ሐሳብ ይህን ያረጋግጥልናል።—ሚልክያስ 3:16ን አንብብ።

ሚልክያስ ትንቢት በተናገረበት በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በእስራኤል የነበረው ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ሁኔታ በጣም ያዘቀጠ ነበር። ካህናቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ችላ ብለው ነበር፤ ሕዝቡ ደግሞ እንደ መተት፣ ምንዝር እና ማጭበርበር ያሉ አምላክን የሚያቃልሉ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። (ሚልክያስ 2:8፤ 3:5) ይሁንና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉም ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ጥቂት እስራኤላውያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ምን ያደርጉ ነበር?

ሚልክያስ “እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ” ብሏል። አምላክን መፍራት ተገቢ ባሕርይ ነው። ሚልክያስ እዚህ ላይ የጠቀሳቸው ሰዎች ለአምላክ ጥልቅ አክብሮትና ተገቢ ፍርሃት ስለነበራቸው እሱን ላለማሳዘን ይጠነቀቁ ነበር። እነዚህ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች “እርስ በርሳቸው” እንደተነጋገሩ ልብ በል። እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ለማወደስና እርስ በርሳቸው ለመበረታታት አንድ ላይ ይሰባሰቡ የነበረ ይመስላል፤ እንዲህ ማድረጋቸው በወቅቱ የነበረው የዘቀጠ ሁኔታ ተስፋ እንዳያስቆርጣቸውና እንዳይበክላቸው ጠብቋቸዋል።

ታማኞቹ እስራኤላውያን ለይሖዋ አክብሮት እንዳላቸው ያሳዩበት ሌላው መንገድ ደግሞ ‘ስሙን ማክበራቸው’ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ሐሳብ ‘ስሙን የሚያስቡ’ በማለት ተርጉሞታል። እነዚህ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች በሐሳባቸውም እንኳ ይሖዋን አክብረውታል። ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ታላቅ ስሙ በልባቸው በአድናቆት ያስቡ ወይም ያሰላስሉ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ይህን ነገር ትኩረት ሰጥቶ ተመልክቶት ነበር?

ሚልክያስ “እግዚአብሔር አዳመጠ፤ ሰማቸውም” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ የሚኖረው እጅግ ከፍ ባለ ስፍራ ቢሆንም አገልጋዮቹ እሱን ለማወደስ የሚነጋገሩትን ሐሳብ ሁሉ ለመስማት ሲል ጆሮዎቹን ወደ እነሱ የሚያዘነብል ያህል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ብቻቸውን ሲሆኑ የሚያሰላስሉትን ነገር ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታል። (መዝሙር 139:2) ይሖዋ አገልጋዮቹ የተናገሩትንና ያሰቡትን መልካም ነገር ከመመልከት ያለፈ ነገርም አድርጓል።

ሚልክያስ “በእርሱ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ” ብሏል። ይህ መጽሐፍ ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ሰዎችን ሁሉ ስም የያዘ መዝገብ ነው። ይህ መጽሐፍ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” * ተብሎ እንደተጠራ ልብ በል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲሁም በድርጊታቸው፣ በንግግራቸውና በሐሳባቸው እሱን ለማወደስ ያደረጉትን ጥረት ፈጽሞ አይረሳም። አምላክ እነሱን የሚያስታውስበት ምክንያት አለው። በእሱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ ስማቸው በማይፋቅ መንገድ የተጻፉ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። *መዝሙር 37:29

ይሖዋ፣ በሚያስደስተው መንገድ እሱን ለማምለክ የምናደርገውን እያንዳንዱን ጥረት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከት ማወቅ በጣም የሚያጽናና ነው! በ⁠ሚልክያስ 3:16 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከይሖዋ ጋር ስላለን ዝምድና በቁም ነገር እንድናስብ ሊያነሳሳን ይገባል። በመሆኑም ‘ስሜ በአምላክ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ተጽፏል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ይሖዋ ቦታ ሰጥቶ ሊያስታውሰው የሚፈልገው ዓይነት ድርጊት፣ አነጋገር እና አስተሳሰብ እንዲኖረን በየዕለቱ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ስማችን በአምላክ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ ይጻፋል።

በታኅሣሥ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ናሆም 1-3 እስከ ሚልክያስ 1-4

^ စာပိုဒ်၊ 8 “መታሰቢያ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አንድን ነገር ከማስታወስ ያለፈ ነገርን ያመለክታል። ቃሉ አንድን ነገር አስታውሶ ከዚያ ጋር በተያያዘ እርምጃ መውሰድንም ሊያመለክት ይችላል።

^ စာပိုဒ်၊ 8 አምላክ ቃል ስለገባው የዘላለም ሕይወት ሽልማት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።