በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንት ዘመን የሚኖሩ ሰዎች የሚጠቀሙት ምን ዓይነት ብዕርና ቀለም ነበር?

በግብፅ የተገኙ የመቃ ብዕሮች፣ አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ

ሐዋርያው ዮሐንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆኑት ሦስት ደብዳቤዎቹ የመጨረሻውን ሲደመድም “ብዙ የምጽፍልህ ነገር ነበረኝ፤ ሆኖም ከዚህ በላይ በቀለምና በብዕር ልጽፍልህ አልፈልግም” ብሎ ነበር። የግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ ቃል በቃል ቢተረጎም ዮሐንስ “በጥቁር [ቀለም] እና በመቃ” መጻፍ እንዳልፈለገ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል።—3 ዮሐንስ 13ዘ ኪንግደም ኢንተርሊንየር ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ስክሪፕቸርስ

ጸሐፊዎች ይጠቀሙበት የነበረው ብዕር ረዘም ያለና ጠንካራ የሆነ መቃ ነበር። መቃው በአንዱ በኩል በሰያፍ ከተቆረጠ በኋላ ጫፉ በቀጭኑ ይሰነጠቃል። ጸሐፊው የመቃውን ጫፍ በየጊዜው በመሳያ ድንጋይ ሊያሾለው ይችል ነበር። እንዲህ ያለው መቃ ቅርጹም ሆነ አገልግሎቱ በዘመናችን ካለው የብረት ጫፍ ያለው ብዕር ጋር ይመሳሰላል።

አብዛኛው “ጥቁር [ቀለም]” የሚዘጋጀው ጥላሸትና ሙጫ መሳይ ነገር በመደባለቅ ነበር። ይህ ዓይነቱ ቀለም የሚሸጠው ከደረቀ በኋላ በመሆኑ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በውኃ ተበጥብጦ ትክክለኛ የውፍረት መጠን እንዲኖረው ይደረግ ነበር። ፓፒረስ ወይም ብራና ላይ እንዲህ ባለው ቀለም በሚጻፍበት ጊዜ ቀለሙ ወደ ውስጥ ዘልቆ አይገባም። በመሆኑም ጸሐፊው የተሳሳተ ነገር ከጻፈ በእርጥብ ሰፍነግ ወይም ስፖንጅ በቀላሉ ሊያጠፋው ይችላል፤ አንድ ጸሐፊ ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች አንዱ ሰፍነግ የሆነው ለዚህ ነው። ስለ ጥንታዊው ቀለም ያገኘነው ይህ ዝርዝር መረጃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች፣ የአንዳንድ ሰዎች ስም ከአምላክ የመታሰቢያ መጽሐፍ ስለ መደምሰሱ የገለጹት ከምን አንጻር እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—ዘጸአት 32:32, 33፣ ራእይ 3:5

ሐዋርያው ጳውሎስ የሚሠራው ምን ዓይነት ድንኳኖችን ነበር?

በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛውም መቶ ዘመን የነበሩ የመስፊያ መሣሪያዎች

የሐዋርያት ሥራ 18:3 ሐዋርያው ጳውሎስ ድንኳን ሰፊ እንደነበር ይነግረናል። በጥንት ዘመን የግመል ወይም የፍየል ፀጉር በመሸመን ለድንኳን የሚሆን ጨርቅ ይዘጋጅ ነበር። ከዚያም ጨርቆቹን ገጣጥሞ በመስፋት መንገደኞች የሚጠቀሙበት ድንኳን ይሠራል። ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን በአብዛኛው ድንኳን የሚሠራው ከቆዳ ነበር። ሌሎች ደግሞ ከተልባ እግር ወይም ከሊኖ ጨርቅ ድንኳን ይሠሩ ነበር፤ የጳውሎስ የትውልድ ከተማ በሆነችው በጠርሴስ የተልባ እግር ጨርቅ ይመረት ነበር። ጳውሎስ ድንኳን ሲሠራ ከእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች አንዳንዶቹን ምናልባትም ሁሉንም ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስና አቂላ ይሰፉ የነበሩት የግል ቤቶችን በረንዳ ከፀሐይ የሚከላከል ከተልባ እግር የሚሠራ ዳስ ሳይሆን አይቀርም።

ጳውሎስ ይህን ሙያ የተማረው ታዳጊ ወጣት እያለ ሳይሆን አይቀርም። የግብፃውያን የፓፒረስ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በሮማውያን ግዛት ዘመን በግብፅ ያሉ ልጆች ሙያ መማር የሚጀምሩት በ13 ዓመት ዕድሜያቸው አካባቢ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ዕድሜው ሙያውን መማር ከጀመረ 15 ወይም 16 ዓመት ሲሆነው ጨርቆቹን በተፈለገው መጠንና ቅርጽ አስተካክሎ በመቁረጥ እንዲሁም የተለያዩ ወስፌዎችንና የአሰፋፍ ዘዴዎችን ተጠቅሞ በመስፋት ረገድ ተክኖ ሊሆን ይችላል። ዘ ሶሻል ኮንቴክስት ኦቭ ፖልስ ሚኒስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ጳውሎስ “ሥልጠናውን ሲያጠናቅቅ የራሱ መሣሪያዎች ሳይሰጡት አልቀረም።” ይኸው መጽሐፍ እንደገለጸው “ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች መቁረጫዎችና መስፊያዎች” ብቻ በመሆናቸው “ድንኳን ለመስፋት አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ መሆን አያስፈልግም”፤ ይህም ጳውሎስ የሚስዮናዊነት ሥራውን እያከናወነ ሲያስፈልገው ድንኳን በመስፋት ራሱን ለማስተዳደር አስችሎታል።