በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥያቄ 1፦ ሕይወቴ ዓላማ አለው?

ጥያቄ 1፦ ሕይወቴ ዓላማ አለው?

እንግሊዝ ውስጥ ያደገችው ራዝሊንድ ከፍተኛ የእውቀት ጥማት ነበራት። ሰዎችን መርዳትም ትፈልግ ስለነበር የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችንና ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚያስችላት ሥራ ትሠራ ነበር። ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ ጥሩ የሚባል ሥራ ማግኘት ቻለች። ራዝሊንድ የሚያረካ ሥራና የተደላደለ ኑሮ ቢኖራትም “‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?’ እና ‘ሕይወት ዓላማ አለው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ለዓመታት በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር” ብላለች።

ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?

ሰዎች ማሰብ ከማይችሉ እንስሳት የተለየን ነን። ካለፈው የመማርና ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ የማውጣት ችሎታ ያለን ከመሆኑም በላይ የሕይወትን ዓላማ ማወቅ እንፈልጋለን።

አንዳንዶች ምን መልስ ይሰጣሉ?

ብዙዎች የሕይወት ዋነኛ ዓላማ፣ ሀብት በማካበት ወይም ዝነኛ በመሆን ደስታ ማግኘት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

መልሳቸው ምን አንድምታ አለው?

በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን የምንወስነው እኛ ነን። የአምላክን ፈቃድ መፈጸም የራሳችንን ፍላጎት የማሟላትን ያህል አስፈላጊ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ንጉሥ ሰለሞን ከፍተኛ ሀብት ያካበተ ከመሆኑም ሌላ ደስታ ያስገኛሉ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ነበሩት፤ ያም ቢሆን እነዚህ ነገሮች እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት እንደማያስችሉ ተገንዝቧል። ሰለሞን ሕይወት እውነተኛ ዓላማ ያለው እንዲሆን የሚያስፈልገው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።” (መክብብ 12:13) ታዲያ የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

አምላክ በሕይወት እንድንደሰት ይፈልጋል፤ እኛን የፈጠረበት አንዱ ዓላማ ይህ ነው። ሰለሞን እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደሚሰጥ አየሁ።”—መክብብ 2:24

በተጨማሪም አምላክ ቤተሰባችንን እንድንወድና እንድንንከባከብ ይፈልጋል። ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሰጠውን ቀላልና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ተመልከት።

  • “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል።”—ኤፌሶን 5:28

  • “ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።”—ኤፌሶን 5:33

  • “ልጆች ሆይ፣ . . . ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።”—ኤፌሶን 6:1

እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሥራ የምናውል ከሆነ ደስታና እርካታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ልናከናውነው የምንችለው በጣም አስፈላጊ ነገር ስለ ፈጣሪያችን የምንችለውን ያህል ማወቅና ወደ አምላክ በመቅረብ እሱን ወዳጃችን ማድረግ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ” በማለት ይጋብዘናል። ቀጥሎም “እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚል ግሩም ተስፋ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:8) ይህን ግብዣ የምትቀበል ከሆነ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ።

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ራዝሊንድ አሁን የሕይወትን ዓላማ እንዳገኘች ይሰማታል። አመለካከቷን እንድትለውጥ የረዳት ምን እንደሆነ ለማወቅ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ርዕስ ላይ ራሷ የተናገረችውን ሐሳብ ማንበብ ትችላለህ።