በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—እረኛው

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—እረኛው

“መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል።”—ኢሳይያስ 40:11

እረኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመሪያው መጽሐፍ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ይኸውም ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ በርካታ ጊዜ ተጠቅሰዋል። (ዘፍጥረት 4:2፤ ራእይ 12:5) እንደ አብርሃም፣ ሙሴና ንጉሥ ዳዊት ያሉት ታላላቅ ሰዎች እረኞች ነበሩ። መዝሙራዊው ዳዊት አንድ ጥሩ እረኛ ያሉበትን ኃላፊነቶችና የሚያሳስቡትን ነገሮች ማራኪ በሆነ መንገድ ገልጿል። አሳፍ እንደጻፈው በሚታሰብ አንድ መዝሙር ላይም ንጉሥ ዳዊት በጥንት ዘመን ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች እረኛ እንደነበረ ተጠቅሷል።—መዝሙር 78:70-72

ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በኖረበት ዘመንም እረኝነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሙያ ነበር። ኢየሱስም ራሱን “ጥሩ እረኛ” በማለት የጠራ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተማር አንድ ጥሩ እረኛ ያሉትን መልካም ባሕርያት ይጠቀም ነበር። (ዮሐንስ 10:2-4, 11) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክም እንኳ ‘በእረኛ’ ተመስሏል።—ኢሳይያስ 40:10, 11፤ መዝሙር 23:1-4

እረኞች የትኞቹን እንስሳት ይጠብቁ ነበር? ሥራቸው ምን ነገሮችን ይጨምር ነበር? እኛስ ከእነዚያ ታታሪ ሠራተኞች ምን ልንማር እንችላለን?

በጎችና ፍየሎች

በጥንቷ እስራኤል የነበሩ እረኞች ከሚጠብቋቸው መንጎች መካከል የሶሪያ ዝርያ የሆኑ ወፍራም ላትና ጥቅጥቅ ያለ ፀጉር ያላቸው በጎች ሳይገኙ አይቀሩም። የዚህ ዝርያ አውራ በጎች ቀንድ ያላቸው ሲሆን እንስቶቹ ግን ቀንድ አልባ ናቸው። እነዚህን ገራም እንስሳት እረኛው በቀላሉ ወደፈለገው ቦታ ሊነዳቸው ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን ራሳቸውን ከሚያጋጥማቸው አደገኛ ሁኔታም ሆነ ከአዳኞች መከላከል አይችሉም።

 እረኞች ፍየሎችንም ይጠብቁ ነበር። ፍየሎቹ ሙሉ በሙሉ ጥቁር ወይም ቡናማ ቀለም ያላቸው ነበሩ። ፍየሎች ዓለታማ በሆነ ገደላ ገደል ላይ እየተንጠላጠሉ ቁጥቋጦዎችን በሚቀነጣጥቡበት ጊዜ የቁጥቋጦው እሾህ ቀጥ ያለውን ጆሯቸውን ይቀድደዋል።

እረኛው፣ በጎቹና ፍየሎቹ እንዲታዘዙት ለማድረግ እነዚህን እንስሳት ሁልጊዜ ማሠልጠን ያስፈልገው ነበር። እንደዚያም ሆኖ ጥሩ እረኞች በአደራ የተሰጧቸውን እንስሳት በርኅራኄ የሚጠብቁ ከመሆኑም በላይ ሲጠሯቸው ሰምተው ምላሽ መስጠት እንዲችሉ ለእንስሳቱ ስም ያወጡላቸው ነበር።—ዮሐንስ 10:14, 16

ወቅቶችና እረኛው

በጸደይ ወራት እረኛው መንጋውን በቤቱ አጠገብ ካለው ጉረኖ ያወጣና በአቅራቢያ በሚገኘው ለምለምና አረንጓዴ አካባቢ በየቀኑ ለግጦሽ ያሰማራቸዋል። በዚህ ወቅት በጎቹና ፍየሎቹ ስለሚወልዱ የእንስሳቱ ቁጥር ይጨምራል። የቅዝቃዜው ወቅት ስላለፈ ሠራተኞቹ በጎቹን የሚሸልቱትም በዚህ ወቅት ነው፤ ይህ የደስታ ጊዜ ነው!

አንድ በግ አርቢ ያሉት በጎች ትንሽ ከሆኑ በጎቹን ከሌላ መንጋ ጋር ቀላቅሎ የሚጠብቅለት እረኛ ሊቀጥር ይችል ነበር። እርግጥ ነው፣ የቅጥር እረኞች የራሳቸው ላልሆኑት እንስሳት እምብዛም አሳቢነት ስለማያሳዩ መልካም ስም አልነበራቸውም።—ዮሐንስ 10:12, 13

በመንደሩ አቅራቢያ ካሉት ማሳዎች ላይ ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ እረኛው በማሳው ላይ ብቅ ብቅ ያሉትን ቡቃያዎች እንዲግጡና በቆረኑ መካከል የወዳደቀውን ሰብል እንዲለቅሙ በጎቹን ያሰማራቸዋል። የሙቀቱ ወቅት ሲጀምር እረኞች መንጎቻቸውን በከፍታ ቦታ ላይ ወደሚገኙ ቀዝቀዝ ያሉ የግጦሽ አካባቢዎች ይመሯቸዋል። እረኞቹ፣ ቀጥ ባሉ ተረተሮች ላይ ያለውን ለምለም ሣር እንዲግጡ መንጎቻቸውን የሚያሰማሯቸው ሲሆን ሌሊት ላይ ደግሞ መንጋውን እየጠበቁ እዚያው ያድራሉ፤ በዚህ ሁኔታ ለብዙ ቀናት ከቤት ውጭ ይሰነብታሉ። አንዳንድ ጊዜ እረኛው፣ ሌሊት ላይ ከሚመጡት ቀበሮዎችና ጅቦች እንስሳቱን ለመጠበቅ ሲል ዋሻ ውስጥ ሊያሳድራቸው ይችላል። ድቅድቅ ባለው ሌሊት ጅቦች የሚያሰሙት ጩኸትና ማስካካት መንጋውን ካስደነገጠበት እረኛው ድምፁን በማሰማት ያረጋጋቸዋል።

እረኛው በየምሽቱ በጎቹን የሚቆጥር ከመሆኑም በላይ ጤንነታቸውን ያጣራል። ማለዳ ላይ ተነስቶ መንጋውን ሲጣራ እንስሳቱ ወደሚወስዳቸው የግጦሽ ስፍራ ተከትለውት ይሄዳሉ። (ዮሐንስ 10:3, 4) እኩለ ቀን ላይ እረኞች መንጎቻቸውን ቀዝቃዛ ኩሬ ወዳለበት ቦታ ይወስዷቸዋል። ኩሬዎቹ ሲደርቁ ደግሞ መንጎቹን የውኃ ጉድጓድ ወዳለበት ቦታ በመውሰድ ውኃ እየቀዱ ያጠጧቸዋል።

ደረቁ ወቅት ወደማለቁ ሲቃረብ እረኛው መንጋውን በባሕር ዳርቻ  ወደሚገኙ ሜዳዎችና ሸለቆዎች ይወስዳቸው ይሆናል። ከዚያም ቀዝቃዛ የሆነው የዝናብ ወቅት ሲጀምር ክረምቱን ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ በጎቹን ወደ ጉረኗቸው ይመልሳቸዋል። እንዲህ ካላደረገ በውጭ ያለው ኃይለኛ ዝናብና ዶፍ እንዲሁም በረዶ እንስሳቱን ሊጨርሳቸው ይችላል። ከኅዳር ጀምሮ እስከ ጸደይ ድረስ እረኞች መንጎቻቸውን ለግጦሽ ከቤት ውጭ አያሰማሯቸውም።

ለሥራ የታጠቀ

የእረኛው ልብስ ሲያዩት ቀላል ቢመስልም ጠንካራ ነው። ዝናቡንና የሌሊቱን ቁር ለመከላከል ከበግ ቆዳ የተሠራ ደበሎ ሳይለብስ አይቀርም፤ እንዲህ ዓይነቱ ደበሎ የበጉ ፀጉር ከውስጥ በኩል እንዲሆን ተደርጎ ይሠራል። እረኛው ከውስጥ እጀ ጠባብ ይለብሳል። እግሮቹን የሾሉ ድንጋዮችና እሾህ እንዳይወጋው ክፍት ጫማ የሚያደርግ ሲሆን ከሱፍ የተሠራ ጨርቅ ጭንቅላቱ ላይ ይጠመጥም ነበር።

እረኛው አብዛኛውን ጊዜ የሚከተሉትን ዕቃዎች ይይዛል፦ እንደ ዳቦ፣ የወይራ ፍሬ፣ ደረቅ ፍራፍሬና አይብ የመሳሰሉትን ምግቦች ሰንቆ የሚይዝበት ኮሮጆ፤ በጣም አስፈላጊ መሣሪያ የሆነውና ሰፋ ባለው ጫፉ ላይ ሹል ድንጋዮች የተሰኩበት እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሜትር ርዝማኔ ያለው በትር፤ ቢላ፤ እረኛው ሲራመድና አቀበት ሲወጣ የሚመረኮዝበት ዘንግ፤ የሚጠጣውን ውኃ የሚይዝበት እርኮት፤ ከጥልቅ ጉድጓድ ውኃ የሚቀዳበት ተጣጥፎ ሊያዝ የሚችል ከቆዳ የተሠራ መቅጃ፤ ከመንጋው ተለይተው የሚሄዱ በጎችን ወይም ፍየሎችን አስደንብሮ ወደ መንጋው ለመመለስ አሊያም አድፍጠው የሚያደቡ አውሬዎችን ለማባረር የሚጠቀምበት ወንጭፍ እንዲሁም ራሱን ለማዝናናትና መንጋውን ለማረጋጋት የሚጫወተው ከሸምበቆ የሚሠራ ዋሽንት።

እረኛው እንደ ወተትና ሥጋ የመሳሰሉትን ጠቃሚ ምርቶች ከእንስሳቱ ስለሚያገኝ ልፋቱ ይካሳል። የበጎቹ ፀጉርና ቆዳ ለመገበያያነት የሚውል ከመሆኑም ሌላ ልብስና የፈሳሽ ነገር መያዣ ይሠራበት ነበር። የፍየል ፀጉርም ተፈትሎ ልብስ ሊሆን ይችላል፤ ከዚህም ሌላ በጎችም ሆኑ ፍየሎች መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ ነበር።

ጥሩ አርዓያ

ጥሩ እረኞች ታታሪ፣ እምነት የሚጣልባቸውና ደፋር ነበሩ። መንጋቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የራሳቸውን ሕይወትም እንኳ ለአደጋ ያጋልጡ ነበር።—1 ሳሙኤል 17:34-36

ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እረኞችን ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጋር ማመሳሰላቸው ምንም አያስደንቅም። (ዮሐንስ 21:15-17፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28) በጥንት ዘመን ከነበረ ጥሩ እረኛ ጋር በሚመሳሰል መልኩ በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችም “በአደራ [የተሰጣቸውን] የአምላክ መንጋ . . . በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት” ተንከባክበው ለመያዝ ይጥራሉ።—1 ጴጥሮስ 5:2