በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

እምነት ለማዳበር የሚጥር ሰው ራሱን እያታለለ ነው?

እምነት ለማዳበር የሚጥር ሰው ራሱን እያታለለ ነው?

አንዳንዶች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እውነታውን ከመጋፈጥና ምክንያታዊ ሆነው ከማሰብ ይልቅ ጊዜያዊ እፎይታ ሊሰጧቸው ወደሚችሉ ነገሮች ዘወር በማለት ራሳቸውን ያታልላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ችግራቸውን ለመርሳት የአልኮል መጠጥ ይጠጣሉ። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ይህን ሲያደርጉ በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንደጨመረና ችግራቸውን ለመፍታት አቅም እንዳገኙ ይሰማቸው ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን አልኮል ለጉዳት እንደሚዳርጋቸው የታወቀ ነው። ከሃይማኖታዊ እምነት ጋር በተያያዘም እንዲህ ማለት ይቻላል?

አንዳንዶች፣ እምነት ያላቸው ሰዎች ሞኞች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሃይማኖታዊ እምነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው አእምሮ ማሰብ እንደማይፈልጉ ወይም እምነታቸው የተመሠረተው በጠንካራ ማስረጃ ላይ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። እንደነዚህ ያሉት ተጠራጣሪ ግለሰቦች፣ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች እውነታውን እንደማያገናዝቡ ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነት ብዙ ጊዜ ይናገራል። ይሁንና ሞኞች ወይም የተነገረንን ሁሉ የምናምን እንድንሆን የሚያበረታታ አንድም ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። አእምሮን ለማሠራት አለመፈለግም ቢሆን የሚበረታታ ነገር እንደሆነ አልተገለጸም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ፣ የተነገራቸውን ሁሉ የሚያምኑ ሰዎች ተላላ ወይም ብስለት የሌላቸው እንደሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። (ምሳሌ 14:15, 18) በእርግጥም አንድ ነገር እውነት መሆኑን በማስረጃ ሳያረጋግጡ ማመን ሞኝነት ነው! ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ዓይናችንን ሸፍነን መኪና የሚበዛበትን መንገድ እንድናቋርጥ ቢነግረን ግለሰቡ ስላለን ብቻ እንዲህ እንደማናደርግ የታወቀ ነው። ማስረጃውን ሳያረጋግጡ አንድ ነገር እውነት እንደሆነ ማመንም ከዚህ የተለየ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ነገሮችን በጭፍን በመቀበል እምነት እንድናዳብር አያበረታታም፤ ከዚህ ይልቅ በቀላሉ እንዳንታለል ያሳስበናል። (ማቴዎስ 16:6) ይህንንም ለማድረግ ‘የማሰብ ችሎታችንን’ መጠቀም ይኖርብናል። (ሮም 12:1) መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን በመመርመር በእውነታው ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያሠለጥነናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸው አንዳንድ ሐሳቦች ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል።

ጳውሎስ በሮም ለሚገኘው ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በዚያ የሚገኙ ክርስቲያኖች እሱ ስለነገራቸው ብቻ አምላክ መኖሩን አምነው እንዲቀበሉ አላበረታታቸውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ እውን የሆነ አካል እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንዲመረምሩ ነግሯቸዋል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም [የአምላክን ሥልጣን አምነው የማይቀበሉ ሰዎች] የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።” (ሮም 1:20) ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይም ተመሳሳይ የማሳመኛ ምክንያት አቅርቧል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በእርግጥ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።” (ዕብራውያን 3:4) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት እምነት መጣል ያለባቸው በሁሉም ነገር ላይ እንዳልሆነ ሲገልጽ “ሁሉንም ነገር መርምሩ” ብሏቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 5:21

እምነት ከጥቃት የሚከላከል ጋሻ ሊሆንልን ይችላል

በጠንካራ ማስረጃ ላይ ያልተመሠረተ እምነት ማዳበር ራስን ማታለል ነው፤ እንዲህ ያለው እምነት ለጉዳት ይዳርጋል። ጳውሎስ በዘመኑ ስለነበሩ አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች ሲጽፍ “በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁ” ብሏል። (ሮም 10:2) ከዚህ አንጻር፣ ጳውሎስ በሮም ለሚገኘው ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ያለውን የሚከተለውን ምክር መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው፦ “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።” (ሮም 12:2) እምነታችን የተመሠረተው ስለ አምላክ በቀሰምነው ትክክለኛ እውቀት ላይ ከሆነ ራሳችንን እያታለልን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለው እምነት መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት እንዳይደርስብን የሚከላከል ‘ትልቅ ጋሻ’ ይሆንልናል።—ኤፌሶን 6:16