በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ያላትና ስለ አምላክ ለማወቅ ምንም ፍላጎት ያልነበራት አንዲት ሴት እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የቻለችው እንዴት ነው? የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የነበረ አንድ ወጣት አኗኗሩን እንዲቀይር ያደረገው ሞትን በሚመለከት ምን ማወቁ ነው? እንዲሁም የሕይወት ትርጉም ግራ ገብቶት የነበረ አንድ ሰው፣ ክርስቲያን ወንጌላዊ እንዲሆን ያነሳሳው ስለ አምላክ ምን ማወቁ ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚሉ እንስማ።

‘ለዓመታት “የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?” እያልኩ አስብ ነበር።’—ራዝሊንድ ጆን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1963

  • የትውልድ አገር፦ ብሪታንያ

  • የኋላ ታሪክ፦ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ የነበራት

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በደቡባዊ ለንደን በምትገኘው በክሮይደን ሲሆን ዘጠኝ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ስድስተኛ ልጅ ነበርኩ። ወላጆቼ የመጡት ከካሪቢያን ደሴቶች አንዷ ከሆነችው ከሴይንት ቪንሰንት ነው። እናቴ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ነበረች። እኔ ግን ከፍተኛ የእውቀት ጥማት ቢኖረኝም ስለ አምላክ የማወቅ ፍላጎት አልነበረኝም። ትምህርት ቤት ሲዘጋ በአብዛኛው የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው በአካባቢያችን በሚገኝ ሐይቅ ዳር ከቤተ መጻሕፍት የተዋስኳቸውን በርካታ መጻሕፍት በማንበብ ነበር።

ትምህርቴን ከጨረስኩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ረዳት የሌላቸው ሰዎችን ለመርዳት ማሰብ ጀመርኩ። የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችንና ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ሰዎች እረዳ ጀመር። ከዚያም ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የጤና ሳይንስ ተማርኩ። ከተመረቅሁ በኋላ በሚያስገርም ሁኔታ የተለያዩ ጥሩ ሥራዎች ያገኘሁ ሲሆን አኗኗሬም እያደር ቅንጦት የሞላበት እየሆነ ሄደ። በአስተዳደር አማካሪነት እንዲሁም በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ በግሌ እሠራ ስለነበር ሥራዬን ለማከናወን የሚያስፈልገኝ ላፕቶፕ ኮምፒውተርና ኢንተርኔት ማግኘት ብቻ ነበር። ለሥራ ለተወሰኑ ሳምንታት ወደ ሌላ አገር ስሄድ በምወደው ሆቴል አርፋለሁ፤ እዚያም ውብ በሆነው አካባቢ እየተዝናናሁ እንዲሁም ቅርጼን ለመጠበቅ በሆቴሉ የስፖርት ማዘውተሪያና የውበት መጠበቂያ እየተጠቀምኩ እሰነብታለሁ። በእርግጥም ሕይወትን እያጣጣምኩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ለተጨቆኑ ሰዎች መጨነቄ አልቀረም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ለዓመታት ‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?’ እና ‘ሕይወት ዓላማ አለው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ይሁንና የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት ሞክሬ አላውቅም። በ1999 አንድ ቀን፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ታናሽ እህቴ ማርጋሬት የእምነት አጋሯ ከሆነች ጓደኛዋ ጋር ልትጠይቀኝ መጣች፤ የማርጋሬት ጓደኛ ትኩረት ሰጥታ አነጋገረችኝ። እኔም ከእሷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሳላስበው ተስማማሁ፤ ይሁን እንጂ ሥራዬና በሕይወቴ ውስጥ የማከናውናቸው ሌሎች ነገሮች አብዛኛውን ጊዜዬን ይሻሙት ስለነበር በጥናቴ የማደርገው እድገት በጣም አዝጋሚ ነበር።

በ2002 በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ መኖር ጀመርኩ። እዚያም በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ የድሕረ ምረቃ ትምህርት እከታተል ጀመር፤ ግቤ የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘት ነበር። በዚያ አካባቢ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ከትንሹ ልጄ ጋር አዘውትሬ መሄድ ጀመርኩ። ምንም እንኳ ከፍተኛ ትምህርት የምወድ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የበለጠ ጠቅሞኛል፤ ምክንያቱም ሕይወት በችግር የተሞላ የሆነበትን ምክንያትና መፍትሔውን ማወቅ የቻልኩት መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቴ ነው። ሁለት ጌቶችን ማገልገል የማይቻል ነገር እንደሆነ የሚናገረው በማቴዎስ 6:24 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት እንደሆነ በራሴ ሕይወት ተመልክቻለሁ። ከአምላክና ከገንዘብ አንዱን መምረጥ ግድ ነው። እኔም በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠውን ነገር መምረጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? * (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በቡድን ሆነው ሲያጠኑ ብዙ ጊዜ እገኝ ነበር። ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ ማምጣት የሚችለው ፈጣሪያችን ይሖዋ ብቻ እንደሆነ አመንኩ። ከዚህ በተለየ መልኩ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ በአምላክ ማመን እንደማያስፈልግ ትምህርት ይሰጥ ነበር። ይህን ስማር በጣም ተናደድኩ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርት በጀመርኩ በሁለት ወሬ ትምህርቴን ለመተውና ለመንፈሳዊ ነገሮች ይበልጥ ጊዜ ለመስጠት ወሰንኩ።

አኗኗሬን እንድለውጥ ያነሳሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምሳሌ 3:5, 6 ሲሆን እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያችን መማር የዶክትሬት ዲግሪ ሊያስገኝልኝ ከሚችለው ሀብትና ቦታ የበለጠ እጅግ የሚክስ ነው። ይሖዋ ለምድር ስላለው ዓላማ እንዲሁም ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ሲል መሥዋዕት በማድረግ ስለተጫወተው ሚና ይበልጥ እያወቅሁ በሄድሁ መጠን ሕይወቴን ለፈጣሪያችን የመወሰን ፍላጎቴ እያደገ መጣ። ስለዚህ ሚያዝያ 2003 ተጠመቅሁ። ከዚያ ወዲህ ቀስ በቀስ አኗኗሬን ቀላል አደረግሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ከይሖዋ ጋር በዋጋ ሊተመን የማይችል ወዳጅነት መሥርቻለሁ። እሱን በማወቄ እውነተኛ ውስጣዊ ሰላምና ደስታ አግኝቻለሁ። በተጨማሪም ከሌሎች እውነተኛ የእሱ አምላኪዎች ጋር መቀራረቤ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል።

ከመጽሐፍ ቅዱስና ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የምማረው ነገር ለእውቀት ያለኝን ጥማት እያረካልኝ ነው። ለሌሎች ስለ እምነቴ መናገር ያስደስተኛል። በዚህ ሥራ መሰማራቴ ሰዎች፣ አሁን የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙና በአዲሱ ዓለም ደግሞ ግሩም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸው ለመርዳት አስችሎኛል። ከሰኔ 2008 ጀምሮ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ እያገለገልኩ ነው፤ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ። የሕይወትን እውነተኛ ዓላማ ያገኘሁ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ።

“ጓደኛዬን ማጣቴ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ ትቷል።”—ሮማን ኢርነስቤርገ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1973

  • የትውልድ አገር፦ ኦስትሪያ

  • የኋላ ታሪክ፦ ቁማርተኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግሁት ኦስትሪያ ውስጥ በምትገኝ ብራውናው የተባለች አነስተኛ ከተማ ነው። ነዋሪዎቹ ሀብታሞች ሲሆኑ አካባቢውም ሰላማዊ ነበር። ቤተሰቤ ካቶሊኮች በመሆናቸው እኔም ያደግሁት በዚሁ ሃይማኖት ውስጥ ነው።

ልጅ እያለሁ ያጋጠመኝ ነገር በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1984 የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ የቅርብ ጓደኛዬ በመኪና አደጋ ሞተ፤ ያን ዕለት ጠዋት ከዚህ ልጅ ጋር እግር ኳስ ስጫወት ነበር። ጓደኛዬን ማጣቴ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ ትቷል። ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚለው ጉዳይ ከአደጋው በኋላ ለበርካታ ዓመታት ያሳስበኝ ነበር።

ትምህርት ስጨርስ የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እያስያዝኩ አዘውትሬ ቁማር ብጫወትም የገንዘብ ችግር አልነበረብኝም። በተጨማሪም በስፖርት ብዙ ጊዜ አሳልፍ ነበር፤ ሄቪ ሜታል እና ፐንክ ሮክ የሚባሉትን የሙዚቃ ስልቶችም እወድ ነበር። ሥራዬ በየምሽት ክለቡና ጭፈራ ቤቱ መዞር ሆነ። ሕይወቴ ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረና በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ነበር፤ በሌላ በኩል ግን ባዶነት ይሰማኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ1995 አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር በሬን አንኳኩተው ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ ሰጡኝ። አሳዛኝ የሆነው የጓደኛዬ አሟሟት ይረብሸኝ ስለነበር መጽሐፉን ተቀበልሁ። ከዚያም ስለ ሞት የሚገልጸውን ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን መላውን መጽሐፍ አነበብኩት!

መጽሐፉ ስለ ሞት የነበሩኝን ጥያቄዎች የመለሰልኝ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ነገር አሳወቀኝ። በካቶሊክ ሃይማኖት ውስጥ ስላደግሁ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለኢየሱስ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናቴ ከኢየሱስ አባት ከይሖዋ አምላክም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድመሠርት ረዳኝ። ይሖዋ ሚስጥራዊና የማይቀረብ አምላክ ሳይሆን እሱን ለሚፈልጉት ሁሉ ራሱን በግልጽ የሚያሳውቅ እንደሆነ ማወቄ ትኩረቴን ሳበው። (ማቴዎስ 7:7-11) ይሖዋ ስሜት እንዳለውም ተማርኩ። በተጨማሪም ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ አወቅሁ። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና ፍጻሜያቸውን እንድመረምር አነሳሳኝ። ይህን ሳደርግ ያወቅሁት ነገር በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት አጠናከረው።

ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ከካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሴ ላይ እያወጣሁ አነብ ነበር። ይበልጥ እየመረመርኩ ስሄድ እውነትን እንዳገኘሁ እየተገነዘብኩ መጣሁ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ይሖዋ እሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት እንድኖር እንደሚጠብቅብኝ ተማርኩ። በኤፌሶን 4:22-24 ላይ ያለውን ሐሳብ ሳነብ ‘በቀድሞ አኗኗሬ’ የተቀረጸውን ‘አሮጌውን ስብዕናዬን’ አውልቄ መጣልና “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን . . . አዲሱን ስብዕና መልበስ” እንዳለብኝ መረዳት ቻልኩ። በመሆኑም ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗሬን አስተካከልኩ። በተጨማሪም ቁማር መጫወት ፍቅረ ንዋይንና ስግብግብነትን ስለሚያበረታታ ይህን ልማድ መተው እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) እነዚህን ለውጦች ለማድረግ ግን ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር መገናኘቴን ማቆምና ልመራበት የምፈልገውን የሥነ ምግባር መሥፈርት የሚያከብሩ አዳዲስ ጓደኞች መፈለግ ነበረብኝ።

እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ በመንግሥት አዳራሹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብና ከጉባኤው አባላት መካከል አዳዲስ ጓደኞችን ማፍራት ጀመርኩ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በግሌ በጥልቀት ማጥናቴን ገፋሁበት። እነዚህ እርምጃዎች የሙዚቃ ምርጫዬን እንድለውጥ፣ በሕይወቴ ውስጥ ያሉኝን ግቦች እንድቀይር እንዲሁም አለባበሴንና አበጣጠሬን እንዳስተካክል አነሳሱኝ። በ1995 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ስለ ገንዘብና ንብረት ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ችያለሁ። ከዚህ ቀደም ቁጡ ነበርኩ፤ አሁን ግን ቁጣዬን መቆጣጠር ችያለሁ። በተጨማሪም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ መጨነቄን ትቻለሁ።

ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን ያቀፈው ዓለም አቀፋዊ ማኅበር አባል መሆኔ ያስደስተኛል። በእነሱ መካከል ችግሮች እያሉባቸውም አምላክን በታማኝነት ለማገልገል የሚጥሩ ሰዎች አሉ። በሕይወቴ በጣም ደስተኛ ስለሆንኩ ጊዜዬንና ጉልበቴን በሙሉ የማውለው የራሴን ምኞት ለማርካት ሳይሆን ይሖዋን ለማምለክና ለሌሎች ሰዎች መልካም ለማድረግ ነው።

“በመጨረሻ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ።”—ኢየን ኪንግ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1963

  • የትውልድ አገር፦ እንግሊዝ

  • የኋላ ታሪክ፦ የሕይወትን ትርጉም ይፈልግ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በእንግሊዝ ቢሆንም ሰባት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ቤተሰቦቼ ወደ አውስትራሊያ ሄዱ። በዚያም የጎብኚዎች መዳረሻ በሆነችው በኩዊንስ ላንድ፣ አውስትራሊያ በምትገኘው ጎልድ ኮስት ከተማ መኖር ጀመርን። ቤተሰቦቼ ሀብታሞች ባይሆኑም የሚያስፈልገንን አጥተን አናውቅም።

በልጅነቴ በቁሳዊ ረገድ የሚያስፈልገኝን ሁሉ ባገኝም እውነተኛ ደስታ ግን አልነበረኝም። የሕይወት ትርጉም ግራ ገብቶኝ ነበር። አባቴ ሰካራም ነበር። ጠጪ በመሆኑና እናቴን ይበድላት ስለነበር ለእሱ ምንም ፍቅር አልነበረኝም። አባቴ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው የቻለው በመሌያ (የአሁኗ ማሌዥያ) ወታደር በነበረበት ወቅት ባጋጠመው ነገር የተነሳ እንደሆነ የተረዳሁት ከጊዜ በኋላ ነበር።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ከመጠን በላይ መጠጣት ጀመርኩ። አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ትምህርቴን ትቼ ባሕር ኃይል ውስጥ ገባሁ። እዚያም የተለያዩ ዕፆችን መውሰድ የጀመርኩ ሲሆን የትንባሆ ሱሰኛ ሆንኩ። ከዚህም ሌላ ያለ መጠጥ ኃይል ምንም ማድረግ እያቃተኝ መጣ። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከመጠን በላይ በመጠጣት ብቻ ሳልወሰን በየቀኑ እንዲህ ማድረግ ጀመርኩ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻና በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ እያለሁ አምላክ መኖሩን እጠራጠር ጀመር። ‘በእርግጥ አምላክ ካለ ሰዎች መከራ እንዲደርስባቸውና እንዲሞቱ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። እንዲሁም በዓለም ላይ ላለው መከራ ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ የሚገልጽ ግጥም ጽፌ ነበር።

ሃያ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ ከባሕር ኃይል ወጣሁ። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን እሠራ ነበር፤ እንዲሁም ለአንድ ዓመት ያህል ወደተለያዩ አገሮች ሄጃለሁ። ያም ሆኖ የተስፋ መቁረጥ ስሜቴን ሊያስወግድልኝ የሚችል ነገር አላገኘሁም። ግብ አውጥቼ አንድ ነገር ላይ የመድረስ ፍላጎት አልነበረኝም። ምንም የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። የራሴ ቤትና አስተማማኝ ሥራ ማግኘት እንዲሁም በሥራዬ እድገት ማድረግ ለእኔ ምንም ትርጉም አልነበራቸውም። “መጽናኛ” ማግኘት የምችለው አልኮል ስጠጣና ሙዚቃ ሳዳምጥ ብቻ ነበር።

በአንድ ወቅት ‘የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?’ የሚለው ጉዳይ በጣም እንዲያሳስበኝ የሚያደርግ ነገር አጋጠመኝ። በወቅቱ በፖላንድ አስከፊውን የኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ እየጎበኘሁ ነበር። በዚህ ቦታ ስለተፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊቶች ከዚያ በፊት አንብቤ ነበር። ሆኖም በቦታው ሆኜ ግዙፍ የሆነውን ማጎሪያ ካምፕ ስመለከት ስሜቴ በጥልቅ ተነካ። የሰው ልጆች በመሰሎቻቸው ላይ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ መፈጸም መቻላቸውን ሳስበው በጣም ዘገነነኝ። ካምፑን እየተዘዋወርኩ ስጎበኝ ዓይኖቼ እንባ አቅርረው ነበር፤ ‘ለምን?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ1993 ከጉዞዬ ስመለስ ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ስል መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ መጥተው በአቅራቢያችን በሚገኝ ስታዲየም ውስጥ በሚካሄድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። እኔም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ወሰንኩ።

ከጥቂት ወራት በፊት፣ ግጥሚያ ሲካሄድ ለማየት ወደዚህ ስታዲየም መጥቼ ነበር፤ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ አሁን ካየሁት ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው። በቦታው የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ትሑቶችና ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸው ሲሆኑ ልጆቻቸውም መልካም ምግባር ነበራቸው። በምሳ ሰዓት ያየሁት ነገርም በጣም አስገርሞኛል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምሳቸውን የበሉት ሜዳው ላይ ቢሆንም ወደ መቀመጫቸው ሲመለሱ ሜዳው ላይ ምንም ቆሻሻ አልነበረም! ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች አጥብቄ የምፈልገው ነገር ይኸውም ውስጣዊ ሰላምና እርካታ እንዳላቸው በግልጽ ይታይ ነበር። በዚያን ዕለት ከቀረቡት ንግግሮች አንዱም ትዝ አይለኝም፤ ሆኖም ምግባራቸው በጥልቅ ነክቶኛል።

ያን ዕለት ምሽት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያነብና የተለያዩ ሃይማኖቶችን ይመረምር የነበረ አንድ የአክስቴ ልጅ ትዝ አለኝ። ይህ ዘመዴ ከዓመታት በፊት፣ እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የሚቻለው በፍሬው እንደሆነ ኢየሱስ መግለጹን ነግሮኝ ነበር። (ማቴዎስ 7:15-20) በመሆኑም ሌላው ቢቀር የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች ይህን ያህል የተለዩት ለምን እንደሆነ መመርመር እንዳለብኝ ተሰማኝ። በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስፋ ጭላንጭል ታየኝ።

ስብሰባው ላይ እንድገኝ የጋበዙኝ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በቀጣዩ ሳምንት ተመልሰው መጡ። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የጋበዙኝ ሲሆን እኔም ተስማማሁ። ከዚህም በተጨማሪ ከእነሱ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ስለ አምላክ የነበረኝ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ክፋትንና መከራን ያመጣው አምላክ እንዳልሆነና ሰዎች መጥፎ ነገር ሲፈጽሙ እሱም እንደሚያዝን ተማርኩ። (ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:40, 41) ይሖዋን የሚያሳዝን ምንም ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። የእሱን ልብ የማስደሰት ፍላጎት አደረብኝ። (ምሳሌ 27:11) ከመጠን በላይ መጠጣትና ትንባሆ መጠቀም አቆምኩ፤ እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች መፈጸሜን ተውኩ። ከዚያም መጋቢት 1994 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

እውነተኛ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ። እንደቀድሞው ለችግሬ ለመሸሽ ስል አልጠጣም። ከዚህ ይልቅ የከበደኝን ነገር በይሖዋ ላይ መጣልን ተምሬያለሁ።—መዝሙር 55:22

ካረን ከተባለች ቆንጆ የይሖዋ ምሥክር ጋር ትዳር ከመሠረትሁ አሥር ዓመት አልፎኛል፤ ኔላ የተባለች የእንጀራ ልጅም አግኝቻለሁ። ሦስታችንም በክርስቲያናዊው አገልግሎት ረዘም ያለ ጊዜ በማሳለፍ ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያውቁ መርዳት ያስደስተናል። በመጨረሻ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ።

^ አን.11 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።