በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች መብት አስከበረ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች መብት አስከበረ

በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም አገር ፓለቲካ ውስጥ እንደማይገቡና በጦርነት እንደማይካፈሉ የታወቀ ነው። “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ” ማድረግ እንደሚገባቸውና ‘ጦርነትን ከእንግዲህ መማር’ እንደማይኖርባቸው አጥብቀው ያምናሉ። (ኢሳይያስ 2:4) እርግጥ ነው፣ የጦር ሠራዊት አባል ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች በሚያደርጉት ምርጫ ጣልቃ አይገቡም። ይሁን እንጂ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው ባይፈቅድለትም በሚኖርበት አገር ይህን ማድረግ ግዴታ ቢሆንስ? ቫሃን ባያትያን የተባለ ወጣት ያጋጠመው እንዲህ ያለ ሁኔታ ነበር።

ጉዳዩ ለአውሮፓ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያደረጉ ሁኔታዎች

ቫሃን በሚያዝያ ወር 1983 በአርሜንያ ተወለደ። በ1996 እሱና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመሩ፤ ከዚያም ቫሃን 16 ዓመት ሲሆነው ተጠመቀ። ቫሃን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ኢየሱስ ላስተማራቸው ትምህርቶች ጥልቅ አክብሮት አዳበረ፤ ከእነዚህ ትምህርቶች መካከል ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የጦር መሣሪያ እንዳያነሱ የሰጠው መመሪያ ይገኝበታል። (ማቴዎስ 26:52) በመሆኑም ቫሃን ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ገጠመው።

በአርሜንያ ሕግ መሠረት 18 ዓመት የሆነው ማንኛውም ወንድ ወታደራዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት። አንድ ሰው ይህን አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል። ቫሃን የአገሩን ዜጎች ማገልገል ቢፈልግም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን የሚያስጥስ ነገር ማድረግ አልፈለገም። ታዲያ ምን አደረገ?

ቫሃን ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት የሚኖርበት ዕድሜ ላይ ከደረሰበት ጊዜ ይኸውም ከ2001 ጀምሮ ለአርሜንያ ባለሥልጣናት ማመልከቻ መጻፍ ጀመረ። በማመልከቻዎቹ ላይ እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት ከሕሊናውና ከእምነቱ ጋር እንደሚጋጭ ይገልጽ ነበር። ያም ቢሆን በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ ሌላ ዓይነት ሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን አሳውቋል።

ቫሃን ባያትያን በአርሜንያ በሚገኘው ኑባራሼን ወኅኒ ቤት ፊት ለፊት

ቫሃን ይህን ማድረግ ከጀመረ ከአንድ ዓመት የሚበልጥ ጊዜ አለፈ፤ በዚህ መሃል ቫሃን በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን  እንዲረዱለት ለባለሥልጣናቱ ማመልከቱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ በመስከረም ወር 2002 ቫሃን የታሰረ ሲሆን ውሎ አድሮም የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት እምቢተኛ እንደሆነ የሚገልጽ ክስ ተመሠረተበት። በዚህም ምክንያት የ18 ወር እስራት ተፈረደበት። አቃቤ ሕጉ ግን ይህ ቅጣት በቂ እንደሆነ አልተሰማውም። ይህ ብይን ከተላለፈ ከአንድ ወር በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ አቃቤ ሕጉ ቅጣቱ እንዲከብድ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቀ። ቫሃን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ “መሠረተ ቢስና አደገኛ” እንደሆነ በመግለጽ አቃቤ ሕጉ ተከራከረ። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕጉን አቤቱታ ተቀብሎ በቫሃን ላይ የተበየነውን ፍርድ ወደ 30 ወር ከፍ አደረገው።

ቫሃን ይህን ውሳኔ በመቃወም ለአርሜንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረበ። በጥር ወር 2003 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጸደቀ። ወዲያውኑ ቫሃን ነፍሰ ገዳዮችና ዕፅ አዘዋዋሪዎች እንዲሁም አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የተፈረደባቸው ሰዎች ወደሚታሰሩበት ወኅኒ ቤት ተዛወረ።

በአውሮፓ ፍርድ ቤት የተከናወኑ ሁኔታዎች

አርሜንያ ከ2001 ጀምሮ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል ሆናለች። በመሆኑም ዜጎቿ በአገራቸው ባሉት ፍርድ ቤቶች በሙሉ ፍትሕ ማግኘት ካልቻሉ ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቤት የማለት መብት አላቸው። ቫሃንም ይህን ለማድረግ መረጠ። ባቀረበው አቤቱታ ላይ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት የተፈረደበት ፍርድ፣ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9 ጋር እንደሚጋጭ የሚገልጽ የመከራከሪያ ሐሳብ አቀረበ። በዚሁ አንቀጽ መሠረት በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት መብቱ እንዲከበርለት ጠየቀ፤ ከዚያ በፊት እንዲህ ያለ አቤቱታ አቅርቦ ጥሩ ብይን የተሰጠው ሰው አልነበረም።

ጥቅምት 27 ቀን 2009 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ። ይህ ፍርድ ቤት፣ ቀደም ሲል በተሰጡ ብይኖች ላይ ተመሥርቶ በረቀቀው ሕግ መሠረት በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9 ላይ የሰፈረው ስለ ሕሊና ነፃነት የሚናገረው ሕግ፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች መብት ለማስከበር ሊውል እንደማይችል ገለጸ።

ባያትያን በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከሕግ አማካሪዎቹ ጋር፣ ኅዳር 24 ቀን 2010

ፍርድ ቤቱ ይህን ብይን በሰጠበት ወቅት ቫሃን ከእስር የተፈታ ከመሆኑም ሌላ ትዳር መሥርቶ የአንድ ልጅ አባት ሆኖ ነበር። ቫሃን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አዘነ። በዚህ ወቅት ጉዳዩን እርግፍ አድርጎ ለመተው አሊያም ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በላይ ላለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት መምረጥ ነበረበት። ቫሃን ጉዳዩን ይግባኝ ለማለት መረጠ። ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚመለከተው ለየት ያሉ ጉዳዮችን ብቻ በመሆኑ ቫሃን ጉዳዩ እንዲታይ እንደተወሰነ ሲያውቅ በጣም ተደሰተ።

በመጨረሻም በስትራዝቡርግ፣ ፈረንሳይ የተሰየመው ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በላይ ያለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 7 ቀን 2011 ብይን ሰጠ። ፍርድ ቤቱ የአርሜንያ መንግሥት፣ ቫሃን ባያትያን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንዲወነጀልና እንዲታሰር በማድረጉ የዚህን ግለሰብ  የሕሊና ነፃነት እንደተጋፋ በመግለጽ 16 ለ1 በሆነ ድምፅ ውሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔውን የተቃወሙት ከአርሜንያ የመጡት ዳኛ ብቻ ነበሩ።

ባያትያን ከባለቤቱ ከዞቪናር እና ከልጁ ከቫሄ ጋር

ይህ ብይን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ብይን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9⁠ን መሠረት በማድረግ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን መብት ሙሉ በሙሉ የሚያስከብር ነው፤ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ታሪክ ውስጥ አንቀጽ 9⁠ን መሠረት በማድረግ እንዲህ ያለ ብይን ሲሰጥ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ብይን አንጻር ፍርድ ቤቱ፣ በዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለትን ሰው ማሰርን መሠረታዊ መብቶችን እንደ መጋፋት አድርጎ ይመለከተዋል።

ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ያላቸውን አቋም በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ፍርድ ቤቱ፣ አመልካቹ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነው በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት እንደሆነ የሚጠራጠርበት አንዳች ምክንያት የለም፤ ግለሰቡ ከልቡ የሚያምንባቸው እነዚህ ሃይማኖታዊ መመሪያዎች ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ካለበት ግዴታ ጋር በጥብቅ ይጋጫሉ።”

ለውሳኔው የተሰጠው ምላሽ

ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ከ450 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ስላልፈቀደላቸው በአርሜንያ እስራት ተፈርዶባቸዋል። ይህ መጽሔት በተዘጋጀበት ወቅት በሃይማኖታዊ ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ያልፈቀደላቸው በአርሜንያ የሚገኙ 58 ወጣቶች ታስረዋል። ከእነዚህ መካከል አምስቱ ግለሰቦች የታሰሩት በባያትያንና በአርሜንያ መንግሥት መካከል ከነበረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ ከተሰጠው ታሪካዊ ብይን በኋላ ነው። * ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ፣ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተነሳ የቀረበበት ክስ እንዲነሳለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፤ አቃቤ ሕጉ ግን አቤቱታውን ሳይቀበለው ቀርቷል። አቃቤ ሕጉ በጽሑፍ ባቀረበው መልስ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የአውሮፓ ፍርድ ቤት በባያትያንና በአርሜንያ መንግሥት መካከል ከነበረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 7 ቀን 2011 የሰጠው ብይን አሁን ለተነሳው ጉዳይ ሊጠቀስ አይችልም፤ ምክንያቱም ሁለቱ ጉዳዮች ምንም ተመሳሳይነት እንደሌላቸው ግልጽ ነው።”

አቃቤ ሕጉ እንዲህ የተሰማው ለምን ነበር? ቫሃን ባያትያን በተከሰሰበት ወቅት በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ ሌላ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ዝግጅት አልነበረም። ከዚያ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ያለ ዝግጅት እንዲኖር የሚያስችል ሕግ በመውጣቱ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት የማይፈልጉ ሰዎች የሲቪል አገልግሎት የመስጠት አማራጭ እንዳላቸው የአርሜንያ መንግሥት ገልጿል። ይሁን እንጂ በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሚሰጠው አማራጭ አገልግሎት፣ ከጦር ሠራዊቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ለውትድርና አገልግሎት የሚጠሩት የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች የሚቀበሉት ዓይነት አማራጭ አይደለም።

ቫሃን ባያትያን፣ በተሰጠው ታሪካዊ ብይን በጣም ተደስቷል። ይህ ብይን የአርሜንያ መንግሥት፣ በጥብቅ በሚከተሉት ሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች ለፍርድ ማቅረቡንና ማሰሩን እንዲያቆም ያስገድዳል።

የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም አገር የሕግ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ የማምጣት ዓላማ የላቸውም። ይሁን እንጂ ቫሃን ባያትያን እንዳደረገው የሚኖሩባቸው አገሮች በሚተዳደሩባቸው ሕጎች በመጠቀም ሕጋዊ መብታቸውን ለማስከበር ጥረት ያደርጋሉ። ለምን? ምንጊዜም በሰላም መኖር እንዲሁም የመሪያቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዛት በሙሉ ያለምንም እንቅፋት መታዘዝ ስለሚፈልጉ ነው።

^ አን.17 ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ወጣቶች የተፈረደባቸው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔውን በሰጠበት ዕለት ይኸውም ሐምሌ 7 ቀን 2011 ነው።