በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ከግሪክ የተላከ ደብዳቤ

በአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ መስበክ

በአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ መስበክ

ጀልባችን በሜድትራንያን ባሕር ላይ ወደምትገኝ አንዲት አነስተኛ አምባ ስታቀና በቀርጤስ ደሴት ላይ ያሉት ግርማ ሞገስ የተላበሱ የሌፍካ ተራሮች ከዓይናችን እየተሰወሩ ሄዱ። በጀልባዋ ላይ የተሳፈርነው 13 ሰዎች በአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ በምትገኘው በጋቭደስ ደሴት ላይ ለመስበክ ጓጉተናል፤ ይህች ደሴት በጣም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ካርታ ላይ ስትታይ ነጥብ ትመስላለች።

ጉዟችንን ስንጀምር ቀኑ ሞቅ ያለ ስለነበር ምንም እንከን ያጋጥመናል ብለን አልጠበቅንም። ብዙም ሳይቆይ ግን ከየት መጣ ሳይባል ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ባሕሩን ያናውጠው ጀመር፤ ማዕበሉ ጀልባችንን ከወዲያ ወዲህ ሲያንገላታት ውስጤ ርብሽብሽ አለ። በዚህ ጊዜ፣ ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት ይኸውም ይህች ደሴት ቄዳ ተብላ ትጠራ በነበረበት ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ባሕር ላይ ሲጓዝ ኃይለኛ ማዕበል እንዳጋጠመው የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትዝ አለኝ። (የሐዋርያት ሥራ 27:13-17) ‘እኛስ በደህና ወደ ጋቭደስ እንደርስ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ።

ትሬፒቲ ኬፕ፣ የአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ

በመጨረሻ፣ የጉዟችን መዳረሻ የሆነችውን ደሴት አየናት፤ በባሕሩ ላይ ጉብ ብላ የምትታየው ይህቺ ድንጋያማ ደሴት ወደ ባሕሩ ጠልቀው በሚገቡ አለቶች የተከበበች ናት። ደሴቷ ከባሕር ጠለል በላይ ያላት ከፍታ ከ300 ሜትር አይበልጥም፤ በአንፃራዊ ሁኔታ ጠፍጣፋ በመሆኗ ከፍ ብሎ የሚታይ ቦታ የላትም። በግምት 26 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት የዚህች ደሴት አብዛኛው ክፍል ጥቅጥቅ ባሉ የፓይን ዛፎችና በቁጥቋጦ የተሸፈነ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ባሕሩ ዳርቻ ድረስ ያለው መሬት በጥድ ዛፎች ተሸፍኗል።

በአንድ ወቅት በደሴቷ ውስጥ 8,000 ያህል ነዋሪዎች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን በደሴቷ ላይ በቋሚነት የሚኖሩት ሰዎች 40 እንኳ አይሆኑም። ዘመናዊው ሥልጣኔ ወደ ጋቭደስ የደረሰ አይመስልም። የጭነት መርከቦችና የነዳጅ ጫኝ መርከቦች በደሴቷ አቅራቢያ የሚያልፉ ቢሆንም ነዋሪዎቿ ከቀርጤስ ሰዎች ጋር የሚገናኙት በትንንሽ ጀልባዎች ተጠቅመው ነው፤ በእነዚህ ጀልባዎች የሚደረገው ጉዞም በመጥፎ የአየር ጠባይ ሳቢያ ሊጓተት ወይም ጭራሹኑ ሊሰረዝ ይችላል።

ወደ ጋቭደስ የመጣነው በዚያ ለሚኖሩት ሰዎች አስደሳችና መንፈሳቸውን የሚያድስ ምሥራች ልናበስራቸው ነው፤ ይህ ምሥራች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣና ሰዎች ፍጹም የሆነ ጤንነት አግኝተው ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጽ ነው። ጀልባችን ወደ ወደቡ ስትደርስ ሁላችንም ይህን ምሥራች ለደሴቲቱ ነዋሪዎች ለማካፈል ጓጉተን ነበር።

ለአራት ሰዓት ተኩል ያህል ማዕበሉ ሲያንገላታን ስለቆየ ጉዟችን አድካሚ እንደነበር ፊታችን ያሳብቃል። ይሁንና ጥቂት ካሸለብንና ቡና ከጠጣን በኋላ ድካማችን ለቀቀን። ከዚያም  ሐዋርያው ጳውሎስ ስላደረገው ጉዞ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በአጭሩ ከከለስንና ልባዊ ጸሎት ካቀረብን በኋላ ሥራችንን ጀመርን።

የአካባቢው ሰዎች በቀላሉ የሚቀረቡና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ወደ ቤታቸው ገብተን ሻይ ቡና እንድንል ይጋብዙን ነበር። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች ከማካፈል በተጨማሪ የምንችለውን ያህል እርዳታ በማበርከት ለተደረገልን ነገር አድናቆታችንን ለማሳየት ጥረት አድርገናል። ለምሳሌ ከአንዲት ሴት ጋር እየተነጋገርን ሳለ አብሮን የነበረ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ የሆነ ወንድም በሴትየዋ የንግድ ቤት ውስጥ የተበላሸ የኤሌክትሪክ ዕቃ መኖሩን አስተዋለ፤ ከዚያም የተበላሸውን ዕቃ ጠገነላት። ሴትየዋም በዚህ ልቧ ተነካ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ የተቀበለች ሲሆን ለእኛም ሆነ ለምናከናውነው የስብከት ሥራ ያላትን አድናቆት ገለጸች። አንዲት ሌላ ሴት ደግሞ “የምታከናውኑት ሥራ የአምላክ እንጂ የሰው አይደለም፤ ለመስበክ ስትሉ ሩቅ ወደሆነው ወደዚህ ደሴት መምጣታችሁ ይህን በግልጽ ያሳያል” በማለት በአድናቆት ተናግራለች።

የደሴቲቱ ነዋሪዎች፣ ለያዝናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ከፍተኛ አድናቆት ነበራቸው። አንድ ሰው መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን የወሰደ ሲሆን የቅዝቃዜው ወቅት ሲመጣ የሚያነባቸው ተጨማሪ ጽሑፎች እንደሚፈልግ ገለጸ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ደንበኞቹ እንዲያነቡት በሱቁ ውስጥ የሚያስቀምጣቸው ጽሑፎች እንደሚፈልግ ነገረን። ይህ ሰው መጽሔቶቹን በየወሩ እንድንልክለት አድራሻውን ሰጠን። ለአንድ ቤተሰብ፣ የሚኖሩባት ትንሽ ደሴት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰች ስናሳያቸው በጣም ተገረሙ። እንዲሁም መጽሔቶቻችንን በደስታ ተቀበሉ።

ሳራኪኒኮ የባሕር ወሽመጥ፣ በግዞት ወደ ደሴቲቱ የተወሰዱ ሰዎች የነበሩበት ሕንፃ እና እነሱን ለማስታወስ የተሠራ ሐውልት

እንዲህ ዓይነት ምላሽ ማግኘታችን በጣም ቢያበረታታንም ወደ ጋቭደስ ያደረግነው ጉዞ ለአንዳንዶቻችን አሳዛኝ ትዝታዎችን ቀስቅሶብናል። በሳራኪኒኮ የባሕር ወሽመጥ አቅራቢያ በአንድ ወቅት የፖለቲካ እስረኞች ይታሰሩበት የነበረ አንድ ሕንፃ አለ። ኢማኑኤል ሊዮኑዳኪስ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ በስብከት ሥራው ምክንያት እዚህ ሕንፃ ውስጥ ታስሮ ነበር። * በዚያን ጊዜ ስለነበረችው ጋቭደስ አንድ ምንጭ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ገዳይ የሆኑ ጊንጦች ብቻ የሚገኙባት እንዲሁም [ብዙዎች] . . . በረሀብ፣ በችጋርና በበሽታ የረገፉባት ጠፍ ደሴት በመሆኗ የሞት ደሴት መባሏ ተገቢ ነው።” ወንድም ሊዮኑዳኪስ፣ የሚበላው ለማግኘት ዓሣ ያጠምድ ነበር፤ በእርግጥ በዚያ የነበረው የይሖዋ ምሥክር እሱ ብቻ በመሆኑ ለሌሎች እስረኞች በመስበኩ ሥራም ተጠምዶ ነበር። ወንድም ሊዮኑዳኪስ 70 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት የታሰረበትን ቦታ ሴት ልጁ፣ አማቹና የልጅ ልጁ ሲያዩ ስሜታቸው ተነካ። የወንድም ሊዮኑዳኪስ ምሳሌነት እኛም ታማኝ እንድንሆንና በአገልግሎታችን በትጋት እንድንካፈል የሚያነሳሳ ነው።

ጋቭደስ፣ ወደ ደሴቲቱ በግዞት ለተላኩት ሰዎች አስደሳች ቦታ እንዳልነበረች ግልጽ ነው። እኛ ግን በደሴቲቱ ላይ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል፤ በዚያ በቆየንባቸው የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በእያንዳንዱ የደሴቲቱ ክፍል የሰበክን ሲሆን እንግዳ ተቀባይ ለሆኑት ነዋሪዎቿ 46 መጽሔቶችንና ዘጠኝ ብሮሹሮችን አበርክተናል። በዚያ ያፈራናቸውን ወዳጆቻችንን እንደገና ለማየት በጣም እንናፍቃለን!

ደሴቷን ለቀን የምንሄድበት ጊዜ ሳይታወቀን ደረሰ። ይሁን እንጂ አሁንም አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ስላጋጠመን እንዳሰብነው ከምሽቱ በ11 ሰዓት ላይ ጉዞ መጀመር አልቻልንም። ለሌላ አስቸጋሪ ጉዞ ራሳችንን አዘጋጅተን እኩለ ሌሊት ሲሆን ጀልባዋ ላይ ተሳፈርን። በመጨረሻም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጉዞ ጀመርን፤ ለአምስት ሰዓታት ያህል በማዕበል በሚናወጠው ባሕር ላይ ስንንገላታ ከቆየን በኋላ ቀርጤስ ደረስን። ለበርካታ ሰዓታት በመጓዛችን ሰውነታችን ስለዛለ ከጀልባዋ ወርደን መሬቱን ስንረግጥ መራመድ አቅቶን ነበር፤ ይሁን እንጂ በጋቭደስ ደሴት ላይ የይሖዋን ስም ማሳወቅ በመቻላችን ተደስተናል። (ኢሳይያስ 42:12) በቡድናችን ውስጥ ያሉት ሁሉ ልፋታችን ከንቱ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል። በጉዞው ላይ ያጋጠመንን መንገላታት ለመርሳት ብዙ ጊዜ አይፈጅብንም፤ ያሳለፍነው አስደሳች ጊዜ ትዝታ ግን በልባችን ጽላት ተቀርጾ እንደሚኖር እርግጠኞች ነን።

^ አን.11 የወንድም ኢማኑኤል ሊዮኑዳኪስ የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 25-29 ላይ ይገኛል።