በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ’

‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ’

ባልሠራኸው ጥፋት ወንጀለኛ ተብለህ ብትከሰስ ምን ይሰማሃል? የተከሰስክበት ወንጀል ደግሞ በሌሎች በተለይም በንጹሐን ሰዎች ላይ መከራና ሥቃይ ያስከተለ ቢሆንስ? ስምህን ለማደስ እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም! ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደገጠመው አስበህ ታውቃለህ? በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በዓለም ላይ ለሚታየው የፍትሕ መጓደልና መከራ ተጠያቂው ማን እንደሆነ በትክክል ስለማያውቁ ጣታቸውን የሚቀስሩት በአምላክ ላይ ነው። ታዲያ ይሖዋ ስሙን ከነቀፋ የማንጻቱ ጉዳይ ያሳስበዋል? አዎን፣ ያሳስበዋል! በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ ይህን አስመልክቶ የሰፈረውን ሐሳብ ልብ በል።—ሕዝቅኤል 39:7ን አንብብ።

ይሖዋ “ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም” በማለት ተናግሯል። የሰው ልጆች በዛሬው ጊዜ ለሚታየው የፍትሕ መጓደል ተጠያቂው እሱ እንደሆነ ሲናገሩ ስሙን እያቃለሉ ማለትም እያረከሱ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስም ብዙውን ጊዜ፣ ሌሎች ስለ አንድ ግለሰብ ያላቸውን አመለካከት ለመግለጽ ይሠራበታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደተናገረው የአምላክ ስም “ስለ እሱ የሚታወቀውን ማለትም እሱ ስለ ራሱ የገለጣቸውን ነገሮች እንዲሁም ዝናውንና ክብሩን ይወክላል።” የይሖዋ ስም፣ ሌሎች ለእሱ ያላቸውን ጥሩ አመለካከትም ያመለክታል። ከፍትሕ መጓደል ጋር በተያያዘ ስለ ይሖዋ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ይጠላል! እንዲሁም የፍትሕ መጓደል ለደረሰባቸው ሰዎች ይራራል። * (ዘፀአት 22:22-24) ሰዎች፣ አምላክ አጥብቆ የሚጸየፈውን ድርጊት እሱ እንደፈጸመው አድርገው ሲናገሩ ስሙን እያቃለሉ ነው። በመሆኑም ‘በስሙ ላይ እያላገጡ’ ነው ሊባል ይችላል።—መዝሙር 74:10

ይሖዋ በዚህ ጥቅስ ላይ ‘ቅዱስ ስሜ’ የሚለውን አገላለጽ ሁለት ጊዜ እንደተጠቀመበት ልብ በል። (ቁጥር 7) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም ብዙ ቦታዎች ላይ ከቅድስና ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። “ቅዱስ” የሚለው ቃል የተለዩ መሆንን ያመለክታል፤ በተጨማሪም ቃሉ ንጹሕ ወይም የጠሩ መሆንንም ለመግለጽ ያገለግላል። ይሖዋ ቅዱስ በሌላ አባባል ከኃጢአትና ርኩስ ከሆነ ከማንኛውም ነገር የራቀ ነው፤ በመሆኑም ስሙ ቅዱስ ነው። ታዲያ በዓለማችን ላይ ለሚታየው ክፋት ይሖዋን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሰዎች ‘በቅዱስ ስሙ’ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ እየከመሩ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ ተገነዘብክ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ጭብጥ፣ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ስሙን ለማስቀደስ ያለውን ዓላማ የሚገልጽ ነው። ይህ ጭብጥ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል፤ በመጽሐፉ ላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ’ የሚለው ሐሳብ ይህን ያሳያል። (ሕዝቅኤል 36:23፤ 37:28፤ 38:23፤ 39:7 NW) ጥቅሱ፣ ይሖዋን ማወቅ ወይም አለማወቅ ለብሔራት የተተወ ምርጫ መሆኑን እንደማይናገር ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ብሔራት የይሖዋን ማንነት እንዲያውቁ ይደረጋሉ። በሌላ አባባል ይሖዋ፣ የምድር ብሔራት ሳይወዱ በግዳቸው ስለ ስሙ እንዲያውቁ የማድረግ ዓላማ አለው። ይኸውም ይሖዋ፣ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ብሎም ስሙ እንደሚያመለክተው ቅዱስ፣ የጠራና ንጹሕ መሆኑን እንዲሁም ስለ ራሱ የተናገረው ነገር እውነት እንደሆነ እንዲያውቁ ይገደዳሉ ማለት ነው።

‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ’ የሚለው በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ሐሳብ የፍትሕ መጓደልና መከራ የሚወገድበትን ጊዜ ለሚናፍቁ ሁሉ ምሥራች ነው። ይሖዋ በቅርቡ ይህን ቃሉን በመፈጸም ስሙን ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ ያደርጋል። ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙትንና ክፋትን የሚያጠፋ ሲሆን ለስሙና ስሙ ለሚወክለው ነገር አክብሮት ያላቸውን ሰዎች ግን ከጥፋት ያድናቸዋል። (ምሳሌ 18:10) ይህን ማወቅህ ቅዱስ እና ‘ፍትሕን የሚወድ’ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ስለምትችልበት መንገድ እውቀት እንድትቀስም አያነሳሳህም?—መዝሙር 37:9-11, 28

በመስከረም ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከሕዝቅኤል 39-48ዳንኤል 1-3

^ አን.4 ኅዳር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወደ አምላክ ቅረብ—ፍትሕን የሚወድ አምላክ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።