በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሴቶችን በአክብሮትና በአሳቢነት ይይዛቸዋል

አምላክ ሴቶችን በአክብሮትና በአሳቢነት ይይዛቸዋል

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በሰማይ ያለውን አባቱን ባሕርይና ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ። . . . ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]።” (ዮሐንስ 8:28, 29፤ ቆላስይስ 1:15) በመሆኑም ኢየሱስ ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነትና ለእነሱ የነበረውን አመለካከት መመርመራችን አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት እንዲሁም ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅ ለመረዳት ያስችለናል።

በርካታ ምሁራን በወንጌል ዘገባዎች ላይ ከተመዘገበው ነገር በመነሳት ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው አመለካከት፣ በወቅቱ ከነበረው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል። የኢየሱስ አመለካከት የተለየ የነበረው እንዴት ነው? ደግሞስ፣ የኢየሱስ ትምህርቶች በዛሬው ጊዜ ያሉት ሴቶችም ነፃነት እንዲያገኙ ይረዳሉ?

ኢየሱስ ሴቶችን የያዘበት መንገድ

ኢየሱስ፣ ሴቶች የተፈጠሩት የወንዶችን የፆታ ፍላጎት ለማርካት እንደሆነ አድርጎ አላሰበም። አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ አንድ ሰው ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለው ማንኛውም ግንኙነት የፆታ ስሜቱ እንዲቀሰቀስ ማድረጉ እንደማይቀር ይሰማቸው ነበር። ሴቶች ለወንዶች ፈተና  እንደሚሆኑ ስለሚታሰብ በአደባባይ ወንዶችን እንዲያነጋግሩ ወይም ራሳቸውን ሳይሸፍኑ ከቤት እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም ነበር። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ፣ ሴቶችን ከማኅበራዊ ግንኙነት ከማግለል ይልቅ ወንዶች የራሳቸውን ሥጋዊ ምኞቶች እንዲቆጣጠሩና የሴቶችን ክብር እንዲጠብቁ መክሯል።—ማቴዎስ 5:28

በተጨማሪም ኢየሱስ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእሷ ላይ ያመነዝራል” ብሏል። (ማርቆስ 10:11, 12) ኢየሱስ ይህን ማለቱ ወንዶች “በማንኛውም ምክንያት” ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱ የሚፈቅደውን በወቅቱ የነበረውን የረቢዎች ትምህርት እንደማይቀበለው ያሳያል። (ማቴዎስ 19:3, 9) አንድ ባል በሚስቱ ላይ ያመነዝራል የሚለው ሐሳብ ለአብዛኞቹ አይሁዳውያን እንግዳ ነገር ነበር። ረቢዎቻቸው፣ አንድ ባል በሚስቱ ላይ እንዳመነዘረ ተደርጎ ሊቆጠር እንደማይችልና ለባሏ ያላትን ታማኝነት ልታጓድል የምትችለው፣ ሴት ብቻ እንደሆነች ያስተምሯቸው ነበር! በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው “ኢየሱስ፣ ለባልም ሆነ ለሚስት ተመሳሳይ የሥነ ምግባር ደንብ መስጠቱ ሴቶች ከፍ ተደርገው እንዲታዩና እንዲከበሩ አድርጓል።”

የኢየሱስ ትምህርት በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥቅም፦ በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ጉባኤዎች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በነፃነት አብረው ይሰበሰባሉ። ክርስቲያን ወንዶች “አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች [አድርገው] በፍጹም ንጽሕና” ለመያዝ ስለሚጥሩ ሴቶች፣ ጨዋነት በጎደለው መንገድ የሚመለከተን ወይም ክብር በሚነካ መንገድ የሚይዘን ወንድ ይኖራል ብለው አይሰጉም።—1 ጢሞቴዎስ 5:2

ኢየሱስ ጊዜ ወስዶ ሴቶችን ያስተምር ነበር። በዘመኑ ተንሰራፍቶ ከነበረው የሴቶችን የመማር መብት የሚነፍግ የረቢዎች አመለካከት በተለየ መልኩ ኢየሱስ፣ ሴቶችን ያስተማረ ከመሆኑም ሌላ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ያበረታታቸው ነበር። ኢየሱስ፣ ማርያም ቁጭ ብሎ የመማር አጋጣሚ እንዲያመልጣት ባለመፍቀድ ‘የሴት ቦታ ኩሽና ውስጥ መሥራት ብቻ ነው’ ብሎ እንደማያምን አሳይቷል። (ሉቃስ 10:38-42) የማርያም እህት ማርታም ብትሆን ከኢየሱስ ትምህርት ቀስማለች፤ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ላቀረበላት ጥያቄ የሰጠችው ብስለት የተንጸባረቀበት መልስ ይህን በግልጽ ያሳያል።—ዮሐንስ 11:21-27

ኢየሱስ ለሴቶች አመለካከት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ ሐሳባቸውን ለማወቅ ይፈልግ ነበር። በዚያ ዘመን አብዛኞቹ አይሁዳዊ ሴቶች ለደስታ ቁልፉ፣ የሚያኮራ ከተቻለም ነቢይ የሚሆን ልጅ መውለድ እንደሆነ ያምኑ ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ጮክ ብላ “አንተን የተሸከመ ማህፀን [ደስተኛ ነው]!” ስትለው ኢየሱስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳለ ገልጾላታል። (ሉቃስ 11:27, 28) ኢየሱስ፣ መንፈሳዊነት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ በማመልከት በባሕሉ መሠረት የሴቶች ድርሻ እንደሆነ ተደርጎ ከሚታሰበው ነገር የሚበልጥ ጉዳይ እንዳለ ገለጸላት።—ዮሐንስ 8:32

የኢየሱስ ትምህርት በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥቅም፦ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚያስተምሩ ወንዶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሴቶች የሚሰጡትን ሐሳብ በደስታ ይቀበላሉ። የጎለመሱ ሴቶች ከሌሎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜም ሆነ በግል ሕይወታቸው ምሳሌ በመተው “ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ” በመሆናቸው ክርስቲያን ወንዶች ያከብሯቸዋል። (ቲቶ 2:3) በተጨማሪም እነዚህ ወንዶች፣ ክርስቲያኖች ያለባቸውን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለሕዝብ  የመናገር ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወጡት ሴቶች እንደሆኑ ይገነዘባሉ።—መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም፤ በገጽ 9 ላይ የሚገኘውን  “ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶች ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ከልክሏል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ኢየሱስ ለሴቶች እንደሚያስብ አሳይቷል። በጥንት ዘመን ሴት ልጆች የወንዶች ልጆችን ያህል ተፈላጊነት አልነበራቸውም። “ወንዶች ልጆች የወለደ ሰው ደስተኛ ነው፤ ሴቶች ለወለደ ግን ወዮለት” የሚለው በታልሙድ ላይ የሚገኘው ሐሳብ በዘመኑ የነበረውን አመለካከት ያንጸባርቃል። አንዳንድ ወላጆች፣ ለሴት ልጃቸው ባል ፈልገው መዳርና ጥሎሽ መስጠት ስላለባቸው እንዲሁም በስተርጅናቸው እንደምትጦራቸው ሊተማመኑባት እንደማይችሉ ስለሚሰማቸው ሴት ልጅ መውለድን እንደ ትልቅ ሸክም ይቆጥሩት ነበር።

ኢየሱስ የአንዲት ትንሽ ልጅ ሕይወት የወንድ ልጅን ያህል ውድ እንደሆነ አሳይቷል፤ የናይን ከተማ ነዋሪ የሆነችውን መበለት ወንድ ልጅ እንዳስነሳ ሁሉ የኢያኢሮስንም ሴት ልጅ ማስነሳቱ ለዚህ ማስረጃ ነው። (ማርቆስ 5:35, 41, 42፤ ሉቃስ 7:11-15) ኢየሱስ፣ “በጋኔን ተጽዕኖ ለአሥራ ስምንት ዓመት” ስትማቅቅ የኖረችን አንዲት ሴት ከፈወሰ በኋላ ስለ እሷ ሲናገር “የአብርሃም ልጅ” ብሏል፤ እንዲህ ያለው አገላለጽ በአይሁዳውያን ጽሑፎች ውስጥ ከሴቶች ጋር በተያያዘ ፈጽሞ አልተሠራበትም ማለት ይችላል። (ሉቃስ 13:10-16) ኢየሱስ የተጠቀመበት አክብሮትና ደግነት የተንጸባረቀበት ይህ አገላለጽ፣ ሴትየዋን እንደ ማንኛውም ሰው አስፈላጊ የማኅበረሰቡ አባል እንደሆነች እንዲሁም ታላቅ እምነት እንዳላት አድርጎ እንደሚቆጥራት የሚያሳይ ነው።—ሉቃስ 19:9፤ ገላትያ 3:7

የኢየሱስ ትምህርት በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥቅም፦ “ሴት ልጅ ማሳደግ የጎረቤትን አትክልት ውኃ እንደ ማጠጣት ነው” የሚል አንድ የእስያ አባባል አለ። አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን አባቶች ግን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ፈጽሞ አይፈቅዱም፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆቻቸውን በእኩል ደረጃ ይንከባከባሉ። ክርስቲያን ወላጆች፣ ሁሉም ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ትምህርትና የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋሉ።

ኢየሱስ፣ መግደላዊት ማርያምን ስለ ትንሣኤው ለሐዋርያት እንድትናገር መብት በመስጠት አክብሯታል

ኢየሱስ በሴቶች ላይ እምነት ነበረው። በአይሁድ ሸንጎዎች ውስጥ አንዲት ሴት የምትሰጠው ምሥክርነት አንድ ባሪያ ከሚሰጠው ምሥክርነት ጋር እኩል እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ “ሴቶች በተፈጥሯቸው ቁም ነገረኛ ስላልሆኑና አጉል ድፍረት ስለሚታይባቸው ከእነሱ ምንም ዓይነት ማስረጃ መቀበል አይገባም” የሚል ምክር ሰጥቷል።

ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ ኢየሱስ ስለ ትንሣኤው ምሥክር እንዲሆኑ የመረጠው ሴቶችን ነበር። (ማቴዎስ 28:1, 8-10) እነዚህ ታማኝ ሴቶች ጌታቸው ሲገደልና ሲቀበር በቦታው ተገኝተው የተመለከቱ የዓይን ምሥክሮች ቢሆኑም ሐዋርያቱ የሴቶቹን ቃል ማመን ከብዷቸው ነበር። (ማቴዎስ 27:55, 56, 61፤ ሉቃስ 24:10, 11) ክርስቶስ ግን ትንሣኤ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ ለሴቶቹ በመገለጥ እነሱንም የወንዶች ደቀ መዛሙርቱን ያህል ምሥክርነት ለመስጠት ብቁ አድርጎ እንደሚቆጥራቸው አሳይቷል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8, 14

የኢየሱስ ትምህርት በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥቅም፦ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች፣  ሴቶች የሚሰጡትን አስተያየት ከግምት በማስገባት ለእነሱ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ክርስቲያን ባሎችም ቢሆኑ ሚስቶቻቸውን በጥሞና በማዳመጥ ‘ክብር ይሰጧቸዋል።’—1 ጴጥሮስ 3:7፤ ዘፍጥረት 21:12

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሴቶች ደስታ ያመጣሉ

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚከተሉ ሰዎች ሴቶችን ያከብራሉ

ወንዶች ክርስቶስን የሚመስሉ ከሆነ ሴቶች፣ አምላክ በመጀመሪያ ለእነሱ አስቦት የነበረውን አክብሮትና ነፃነት ያገኛሉ። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ክርስቲያን ባሎች፣ ወንዶች የሴቶች የበላይ እንደሆኑ አድርገው እንደሚያስቡ የሚጠቁም ነገር ከማድረግ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይመራሉ፤ ይህም የትዳር ጓደኞቻቸው ደስተኛ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ኤፌሶን 5:28, 29

ዬሌና፣ ባሏ ጥቃት ቢያደርስባትም ለማንም ሳትናገር እየተሠቃየች ትኖር ነበር፤ በዚህ መሃል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ባለቤቷ ያደገው ጠለፋና በሚስት ላይ ጥቃት መሰንዘር የተለመዱ ነገሮች በሆኑበት ዓመፀኛ አካባቢ ነበር። ዬሌና “ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር ብርታት ሰጠኝ” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በጣም የሚወደኝና ከፍ አድርጎ የሚመለከተኝ እንዲሁም የሚያስብልኝ አካል እንዳለ ተረዳሁ። በተጨማሪም ባሌ መጽሐፍ ቅዱስን ቢያጠና ለእኔ ያለው አመለካከት ሊቀየር እንደሚችል ተገነዘብኩ።” ከጊዜ በኋላ ይህ ሕልሟ እውን ሆነ፤ ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማ ሲሆን ውሎ አድሮም ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ዬሌና ስለ ባለቤቷ ስትናገር “ራስን በመግዛት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሰው ሆነ” ብላለች። “አንዳችን ሌላውን በነፃ ይቅር ማለትን ተማርን።” ዬሌና ተሞክሮዋን ስትቋጭ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ በትዳሬ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆንኩ እንዲሰማኝና መብቴ ተከብሮልኝ እንድኖር በጣም ረድተውኛል።—ቆላስይስ 3:13, 18, 19

የዬሌና ዓይነት ተሞክሮ ያላቸው ብዙዎች ናቸው። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያን ሴቶች፣ ከባሎቻቸው ጋር ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚጥሩ ደስተኞች መሆን ችለዋል። እነዚህ ሴቶች ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ሲሆኑም ክብር ያገኛሉ፤ ስጋት አያድርባቸውም እንዲሁም ነፃነት ይሰማቸዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ‘ለከንቱነት እንደተገዙ’ እና በዚህም ምክንያት ከኃጢአትና ከአለፍጽምና ነፃ እንዳልሆኑ ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። ይሁን እንጂ አፍቃሪ አምላካቸውና አባታቸው ወደሆነው ወደ ይሖዋ በመቅረባቸው “ከመበስበስ ባርነት ነፃ [የመውጣት]” እና “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” የማግኘት ተስፋ ሊኖራቸው ችሏል። በአምላክ አመራር ሥር የሚኖሩ ወንዶችም ሆነ ሴቶች የተሰጣቸው ተስፋ እንዴት ግሩም ነው!—ሮም 8:20, 21