በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 በእምነታቸው ምሰሏቸው

“ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ”

“ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ”

ሩት የሞዓብን አምባ እያቋረጠ በሚያልፈው ለነፋስ የተጋለጠ መንገድ ላይ ከኑኃሚን ጋር እየተጓዘች ነው። በተንጣለለው ሜዳ ላይ ብቻቸውን የሚጓዙት እነዚህ ሁለት ሴቶች ከርቀት ሲታዩ ነጥብ ይመስላሉ። ሩት ጀምበሯ እያሽቆለቆለች መሆኗን አስተውላ የዛለውን ጎናቸውን የሚያሳርፉበት ማደሪያ መፈለግ ይሻላቸው እንደሆነ ማሰብ ጀምራለች። ኑኃሚንን በጣም ስለምትወዳት እሷን ለመንከባከብ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ አትልም።

ሁለቱም ሴቶች ከባድ ሐዘን ደርሶባቸዋል። ኑኃሚን ባሏ በመሞቱ መበለት ከሆነች ዓመታት አልፈዋል፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ ሁለቱ ልጆቿ መሐሎንና ኬሌዎን በመሞታቸው ሐዘን ላይ ናት። ሩትም ቢሆን ሟቹ መሐሎን ባሏ ስለነበር ሐዘን ደርሶባታል። ሩት ከኑኃሚን ጋር ሆና በእስራኤል ወደምትገኘው የቤተልሔም ከተማ እየተጓዘች ነው። ሁለቱም ወደ አንድ ቦታ እየሄዱ ቢሆንም የሚጠብቁት ነገር የተለያየ ነበር። ኑኃሚን የምትሄደው ወደ አገሯ ነው። ሩት ግን ወዳጅ ዘመዶቿን፣ የትውልድ አገሯን እንዲሁም የአገሯን አማልክት ጨምሮ የምታውቀውን ባሕልና ወግ ትታ ወደ ባዕድ አገር እየሄደች ነው።​—ሩት 1:3-6

አንዲት ወጣት እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳት ምን ይሆን? ሩት አዲሱን ሕይወት ለመልመድና ኑኃሚንን ለመንከባከብ የሚያስችል ብርታት የምታገኘው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን ሞዓባዊቷን ሩትን በእምነቷ መምሰል የምንችልባቸውን በርካታ መንገዶች ይጠቁመናል። እስቲ በመጀመሪያ እነዚህ ሁለት ሴቶች ወደ ቤተልሔም የሚወስደውን ረጅም መንገድ የተያያዙት ለምን እንደሆነ እንመልከት።

መከራ የበታተነው ቤተሰብ

ሩት ያደገችው ሞዓብ በምትባል ከሙት ባሕር በስተምሥራቅ በምትገኝ ትንሽ አገር ነው። በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች፣ ከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙና እምብዛም ዛፎች የማይታዩባቸው ሜዳዎች ያሉ ሲሆን አምባውን ምድር እያቋረጡ የሚያልፉ ጥልቅ ሸለቆዎችም ይታያሉ። የእስራኤልን ምድር ረሃብ በሚያጠቃው ጊዜም እንኳ በአብዛኛው ‘የሞዓብ’ የእርሻ ቦታዎች ለም ነበሩ። ሩት ከመሐሎንና ከቤተሰቡ ጋር ልትገናኝ የቻለችውም በዚሁ ምክንያት ነበር።​—ሩት 1:1

በእስራኤል የተከሰተው ረሃብ፣ የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ በመጻተኝነት ለመኖር ወደ ሞዓብ እንዲሄድ አስገደደው። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ወደመረጠው ቅዱስ ስፍራ እየሄዱ ዘወትር አምልኳቸውን ማከናወን ያስፈልጋቸው ስለነበር ይህ ቤተሰብ ወደ ሞዓብ መሄዱ የሁሉንም እምነት ፈትኖት መሆን አለበት። (ዘዳግም 16:16, 17) ያም ቢሆን ኑኃሚን እምነቷን ጠብቃ መኖር ችላ ነበር። እርግጥ ነው፣ በይሖዋ ላይ እምነት የነበራት ቢሆንም ባሏ ሲሞት በሐዘን ተደቁሳለች።​—ሩት 1:2, 3

ኑኃሚን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሞዓባውያን ሴቶችን ማግባታቸውም ሐዘኗን እጥፍ ድርብ አድርጎት መሆን አለበት። (ሩት 1:4) የእስራኤላውያን ቅድመ አያት የሆነው አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ከራሱ ወገኖች መካከል ይሖዋን የምታመልክ ሚስት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ኑኃሚን ታውቃለች። (ዘፍጥረት 24:3, 4) ከጊዜ በኋላም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወደ ጣዖት አምልኮ እንዳይገቡ ለመጠበቅ ሲል ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ከባዕድ ሰዎች ጋር እንዳያጋቡ የሚያዝዝ ማስጠንቀቂያ በሙሴ ሕግ ውስጥ አካትቶ ነበር።​—ዘዳግም 7:3, 4 *

ያም ቢሆን ግን መሐሎንና ኬሌዎን ሞዓባውያን ሴቶችን  አገቡ። ኑኃሚን ይህ መሆኑ ከማሳሰብም አልፎ ቢያሳዝናትም ለምራቶቿ ለሩትና ለዖርፋ ከልብ የመነጨ ደግነትና ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ እንዳላለች ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ምናልባት እነሱም እንደ እሷ አንድ ቀን የይሖዋ አምላኪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጋ ይሆናል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሩትና ዖርፋ ኑኃሚንን ይወዷት ነበር። ከኑኃሚን ጋር የነበራቸው ጠንካራ ወዳጅነት የደረሰባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል። ሁለቱም ሴቶች ባሎቻቸውን በሞት ያጡት ልጅ እንኳ ሳይወልዱ ገና በወጣትነታቸው ነው።​—ሩት 1:5

ሩት ትከተለው የነበረው ሃይማኖት እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ባጋጠማት ወቅት ማጽናኛ እንድታገኝ ሊረዳት ይችል ይሆን? አይመስልም። ሞዓባውያን ብዙ አማልክትን ያመልኩ የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል ዋነኛው ከሞስ (ካሞሽ) ነበረ። (ዘኍልቍ 21:29) ሕፃናትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ጨምሮ በዚያ ዘመን የተለመደ የነበረው ጭካኔ የሚንጸባረቅበት አሰቃቂ ተግባር በሞዓባውያን ሃይማኖት ውስጥም ይታይ ነበር። ሩት፣ አፍቃሪና መሐሪ ስለሆነው የእስራኤል አምላክ ስለ ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን ከመሐሎን ወይም ከኑኃሚን ሳትማር አትቀርም፤ ይህ ደግሞ በይሖዋ እና በሞዓባውያን አማልክት መካከል ያለው ጉልህ ልዩነት ቁልጭ ብሎ እንዲታያት እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚገዛው በማስፈራራት ሳይሆን በፍቅር ነው! (ዘዳግም 6:5) ሩት በባሏ ሞት ምክንያት የደረሰባት ከባድ ሐዘን ወደ ኑኃሚን ይበልጥ እንድትቀርብና  ይህች አረጋዊት ሴት ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ስለ ይሖዋና ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንዲሁም ሕዝቡን በፍቅርና በምሕረት ስለሚይዝበት መንገድ ስትናገር ልቧን ከፍታ እንድታዳምጥ አነሳስቷት ሊሆን ይችላል።

እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ኑኃሚን እንመለስ፤ ኑኃሚን ከትውልድ ቀዬዋ የመጣ ወሬ ለመስማት እንደምትጓጓ መገመት አያዳግትም። አንድ ቀን፣ በእስራኤል የነበረው ረሃብ እንዳለፈ የሚገልጽ ወሬ ደረሳት፤ ምናልባትም ይህን የሰማችው ከአንድ ተጓዥ ነጋዴ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ሕዝቡን እንደጎበኛቸው ማለትም እንደረዳቸው ሰማች። ቤተልሔም ልክ እንደ ስሟ “የዳቦ ቤት” ሆና ነበር። በመሆኑም ኑኃሚን ወደ አገሯ ለመመለስ ወሰነች።​—ሩት 1:6

ታዲያ ሩትና ዖርፋ ምን ያደርጉ ይሆን? (ሩት 1:7) የደረሰባቸው ሐዘን ከኑኃሚን ጋር ይበልጥ አቀራርቧቸዋል። በተለይም ሩት፣ በኑኃሚን ደግነትና በይሖዋ ላይ ባላት ጽኑ እምነት የተማረከች ይመስላል። ሦስቱም መበለቶች አንድ ላይ ሆነው ወደ ይሁዳ ለመሄድ ተነሱ።

የሩት ታሪክ፣ ክፉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ ሰዎችም አሳዛኝ ነገር እንደሚያጋጥማቸውና የሚወዱትን ሰው በሞት እንደሚያጡ ያስገነዝበናል። (መክብብ 9:2, 11) በተጨማሪም ከዚህ ታሪክ መመልከት እንደምንችለው የምንወደውን ሰው በሞት ስንነጠቅ ከሚሰማን መሪር ሐዘን መጽናናት እና መበርታት እንድንችል ከሌሎች፣ በተለይም እንደ ኑኃሚን ይሖዋን መጠጊያቸው ካደረጉ ሰዎች ጋር መቀራረባችን ብልህነት ነው።​—ምሳሌ 17:17

ሩት ያሳየችው ጽኑ ፍቅር

ሦስቱ መበለቶች በጉዟቸው እየገፉ ሲሄዱ ኑኃሚንን አንድ ነገር ያሳስባት ጀመር። አብረዋት ስላሉት ሁለት ወጣት ሴቶችና ለእሷም ሆነ ለወንዶች ልጆቿ ስላሳዩት ፍቅር አሰበች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በሐዘናቸው ላይ ሌላ ሸክም ሊያጋጥማቸው መሆኑን ስታስበው በጣም ከበዳት። አገራቸውን ጥለው ከእሷ ጋር ወደ ቤተልሔም ከሄዱ በዚያ ምን ልታደርግላቸው ትችላለች?

በመጨረሻም ኑኃሚን ውስጥ ውስጧን ሲያብሰለስላት የነበረውን ሐሳብ አውጥታ ተናገረች፤ “እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፤ ለሞቱ ባሎቻችሁና ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረጋችሁ፣ ለእናንተም እግዚአብሔር እንደዚሁ ያድርግላችሁ” አለቻቸው። በተጨማሪም ይሖዋ ባል እንዲሰጣቸውና ትዳራቸው እንዲሞቅ እንደምትመኝላቸው ገለጸችላቸው። ዘገባው “ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ” በማለት ይተርካል። ሩትና ዖርፋ ይህችን ደግና አሳቢ ሴት ይህን ያህል የወደዷት ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። በመሆኑም ሁለቱም “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” በማለት ከእሷ መለየት እንደማይፈልጉ ገለጹ።​—ሩት 1:8-10

ይሁንና ኑኃሚን በቀላሉ የምትረታ አልሆነችም። የሚያስተዳድራት ባልም ሆነ ለእነሱ ባሎች የሚሆኑ ወንዶች ልጆች እንደሌሏትና ለወደፊቱም ቢሆን ባልም ሆነ ልጅ  እንደሚኖራት ተስፋ እንደማታደርግ በመግለጽ እስራኤል ሲደርሱ ለእነሱ ምንም ልታደርግላቸው እንደማትችል ልታሳምናቸው ሞከረች። ልታደርግላቸው የምትችለው ነገር አለመኖሩም ሐዘኗን ይበልጥ እንደሚያከብደው ነገረቻቸው።​—ሩት 1:11-13

ዖርፋ፣ ኑኃሚን የተናገረችው ነገር እውነት እንደሆነ ተሰማት። ዖርፋ በሞዓብ ብትቀር እናቷና ቤተሰቧ እጃቸውን ከፍተው እንደሚቀበሏት የታወቀ ነው። በእርግጥም በሞዓብ መቅረቱ ይበልጥ ምክንያታዊ ይመስላል። ስለዚህ እያዘነች ኑኃሚንን ስማ ከተሰናበተቻት በኋላ ተመለሰች።​—ሩት 1:14

ሩትስ ምን ታደርግ ይሆን? ኑኃሚን ያቀረበችው ሐሳብ ለእሷም ቢሆን ይሠራል። ዘገባው “ሩት ግን ልትለያት [አልፈለገችም]” ይላል። ምናልባት ኑኃሚን መንገዷን ስትቀጥል ሩት እየተከተለቻት እንደሆነ አስተውላ ሊሆን ይችላል። ኑኃሚን ጠንከር ባለ አነጋገር “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ አብረሻት ተመለሽ” አለቻት። (ሩት 1:15) ኑኃሚን የተናገረችው ሐሳብ አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር ይዟል። ዖርፋ የተመለሰችው ወደ ሕዝቧ ብቻ ሳይሆን ወደ “አማልክቷ” ጭምር ነበር። ዖርፋ፣ ከሞስንና ሌሎች የሐሰት አማልክትን እያመለከች ለመኖር ፈቃደኛ ነበረች። ሩትም እንደዚህ ይሰማት ይሆን?

ኮሽታ እንኳ በማይሰማበት በዚያ ጭር ያለ መንገድ ላይ ሳሉ ሩት ምን እንደምትፈልግ አሳምራ ታውቅ ነበር። ልቧ ለኑኃሚን እንዲሁም ኑኃሚን ለምታመልከው አምላክ ባላት ፍቅር ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እንዲህ አለቻት፦ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።”​—ሩት 1:16, 17

ሩት የተናገረቻቸው ቃላት በጣም አስደናቂ ናቸው፤ በመሆኑም እሷ ከሞተች 3,000 የሚያህሉ ዓመታት ቢያልፉም የተናገረችው ነገር ዛሬም ድረስ ይታወሳል። እነዚህ ቃላት ሩት ያላትን ግሩም ባሕርይ ይኸውም ጽኑ ፍቅሯን ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። ሩት የነበራት ፍቅር እጅግ ጠንካራና ጽኑ በመሆኑ ኑኃሚን በሄደችበት ሁሉ ከእሷ ላለመለየት ቆርጣለች። ሁለቱን ሊነጣጥላቸው የሚችለው ሞት ብቻ ነው። ሩት የሞዓባውያንን አማልክት ጨምሮ በሞዓብ የነበራትን ሁሉ ትታ ለመሄድ ዝግጁ ስለነበረች የኑኃሚን ሕዝቦች የእሷም ሕዝቦች ይሆናሉ። ከዖርፋ በተለየ መልኩ ሩት የኑኃሚን አምላክ የሆነው ይሖዋ ለእሷም አምላኳ እንዲሆንላት እንደምትፈልግ በሙሉ ልብ መናገር ትችላለች። *

በመሆኑም ሁለቱ ብቻቸውን ወደ ቤተልሔም የሚወስደውን ረጅም መንገድ ተያያዙት። ጉዞው አንድ ሳምንት ያህል እንደሚፈጅ ይገመታል። አብረው መሆናቸው ግን ሁለቱንም ከሐዘናቸው በተወሰነ መጠን እንዳጽናናቸው ጥርጥር የለውም።

የምንኖረው አሳዛኝ ነገሮች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በማለት በሚጠራው በእኛ ዘመን የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ማጣትን ጨምሮ በሐዘን እንድንዋጥ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ስለዚህ ሩት ያሳየችው ባሕርይ ይኸውም ጽኑ  ፍቅር ከምንጊዜውም የበለጠ አስፈላጊ ነው። ከሚወዱት አካል ጋር መጣበቅንና የሙጥኝ ማለትን የሚያመለክተውን ይህን ባሕርይ ማዳበራችን በጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም አለው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በትዳር ውስጥ፣ ከቤተሰባችን ጋር ባለን ግንኙነት፣ በጓደኞች መካከል እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጣም ያስፈልጋል። ይህን ባሕርይ እያዳበርን ስንሄድ ሩት የተወችውን ግሩም አርዓያ እየተከተልን ነው።

ሩትና ኑኃሚን በቤተልሔም

ጽኑ ፍቅርን በቃላት መግለጽ አንድ ነገር ሲሆን እንዲህ ያለውን ፍቅር በተግባር ማሳየት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ሩት ለኑኃሚን ብቻ ሳይሆን አምላኳ እንዲሆን ለመረጠችው ለይሖዋም ጽኑ ፍቅር እንዳላት የምታሳይበት አጋጣሚ ተከፍቶላታል።

በመጨረሻም ሁለቱ ሴቶች ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ወደምትገኘው የቤተልሔም ከተማ ደረሱ። ኑኃሚንና ቤተሰቧ በአንድ ወቅት በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ ታዋቂ የነበሩ ይመስላል፤ የከተማው ሕዝብ ሁሉ የሚያወራው ስለ ኑኃሚን መመለስ ነው። የቤተልሔም ሴቶች ኑኃሚንን ትክ ብለው እያዩዋት “ይህች ኑኃሚን ናትን?” ይባባሉ ነበር። ኑኃሚን በሞዓብ ያሳለፈችው ሕይወት ብዙ ሳይለውጣት አልቀረም፤ ገጽታዋና የተጎሳቆለው ሰውነቷ ለዓመታት መከራና ሐዘን እንደተፈራረቀባት ይጠቁማል።​—ሩት 1:19

ኑኃሚን ከዓመታት በፊት ለተለየቻቸው ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ፣ ሕይወት ምን ያህል መራራ እንደሆነባት ገለጸችላቸው። እንዲያውም “ደስታዬ” የሚል ትርጉም ያለው ኑኃሚን የሚለው ስሟ ተለውጦ “መራራ” የሚል ትርጉም ባለው ማራ በሚለው ስም ሊተካ እንደሚገባ ተሰምቷት ነበር። ምስኪን ኑኃሚን! ከእሷ በፊት እንደኖረው እንደ ኢዮብ ሁሉ የደረሰባትን መከራ ያመጣው ይሖዋ እንደሆነ ተሰምቷታል።​—ሩት 1:20, 21፤ ኢዮብ 2:10፤ 13:24-26

ሁለቱ ሴቶች የቤተልሔምን ሕይወት ሲጀምሩ ሩት ራሷንም ሆነ ኑኃሚንን እንዴት እንደምታስተዳድር ሐሳብ ሆነባት። ይሖዋ በእስራኤል ለሚኖሩ ሕዝቦቹ በሰጠው ሕግ ውስጥ ድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት እንዳለ አወቀች። አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት ድሆች ወደ ሌሎች ማሳ በመሄድ አጫጆቹን እየተከተሉ ከኋላ የወዳደቀውንና ከማሳው ዳርና ዳር  የበቀለውን እንዲቃርሙ ይፈቀድላቸው ነበር። *​—ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19-21

ጊዜው ገብስ የሚታጨድበት ወቅት ሲሆን በዘመናዊ የጊዜ አቆጣጠር መሠረት ወሩ ሚያዝያ ሳይሆን አይቀርም፤ ሩት በሕጉ ውስጥ በሰፈረው ዝግጅት መሠረት በማሳው ላይ እንድታቃርም የሚፈቅድላት ሰው ካለ በሚል ወደ እርሻው ቦታ ሄደች። እንዳጋጣሚ ሆኖ የሄደችበት እርሻ ባለቤት፣ የኑኃሚን ባል የሆነው የሟቹ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነ ቦዔዝ የተባለ ሀብታም ባለርስት ነበር። ምንም እንኳ ሩት በሕጉ መሠረት የመቃረም መብት ቢኖራትም ፈቃድ ሳትጠይቅ ሥራዋን አልጀመረችም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ አጫጆቹ አለቃ ቀርባ መቃረም ትችል እንደሆነ ጠየቀችው። እሱም እንድትቃርም ሲፈቅድላት ወዲያውኑ ሥራዋን ጀመረች።​—ሩት 1:22 እስከ 2:3, 7

ሩት አጫጆቹን እየተከተለች ስትቃርም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አጫጆቹ ገብሱን ከባልጩት በተሠራ ማጭዳቸው ሲያጭዱ የወዳደቀውን ወይም የተውትን እየለቀመች በየነዶው ታስርና በኋላ ልትወቃበት ወደምትችለው ቦታ ተሸክማ ትወስዳለች። ሥራው አድካሚ ከመሆኑም ሌላ ቶሎ ቶሎ ሠርታ የማትጨርሰው ዓይነት ነው፤ ፀሐዩ እየበረታ ሲሄድ ደግሞ የባሰውን እየከበደ ይሄዳል። ያም ቢሆን ሩት መቃረሟን ቀጠለች፤ ትንሽ ፋታ የምታገኘው አልፎ አልፎ ላቧን ከግምባሯ ላይ ለመጥረግ ቆም በምትልበት እንዲሁም ለሠራተኞቹ ወደተዘጋጀው “መጠለያ” ሄዳ ቀለል ያለ ምሳ በምትበላበት ጊዜ ብቻ ነው።

ሩት የሌሎች ዓይን ውስጥ እገባለሁ ብላ አላሰበች ይሆናል፤ ሆኖም ያስተዋላት ሰው ነበር። ቦዔዝ፣ ሩትን ሲያያት የአጫጆቹን አለቃ ስለ እሷ ጠየቀው። ግሩም ባሕርይ ያለውና የእምነት ሰው የሆነው ቦዔዝ፣ ሠራተኞቹን ሰላም ያላቸው ‘ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሁን’ በማለት ነበር፤ ከአጫጆቹ መካከል አንዳንዶቹ የቀን ሠራተኞች ወይም የባዕድ አገር ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሰላም አሉት። ይሖዋን የሚወደው ይህ ጠና ያለ ሰው ሩትንም እንደ ልጁ ቆጥሮ ትኩረት ሰጣት።​—ሩት 2:4-7

ቦዔዝ ሩትን “ልጄ ሆይ” ብሎ የጠራት ሲሆን ወደ እርሻው እየመጣች እንድትቃርምና ወንዶቹ አጫጆች እንዳያስቸግሯት የቤተሰቡ አባላት ከሆኑ ወጣት ሴቶች ጋር እንድትሆን መከራት። በምሳ ሰዓትም የምትበላው ምግብ እንድታገኝ አደረገ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ላደረገችው ነገር አመስግኗታል እንዲሁም አበረታቷታል። ይህን ያደረገው እንዴት ነበር?​—ሩት 2:8, 9, 14

ሩት የባዕድ አገር ሰው እንደመሆኗ ለእሷ ይህን ያህል ደግነትና ሞገስ ለማሳየት ያነሳሳው ምን እንደሆነ ቦዔዝን ስትጠይቀው ለአማቷ ለኑኃሚን ያደረገችውን ነገር በሙሉ እንደሰማ ገለጸላት። ኑኃሚን፣ የምትወዳትን ሩትን በተመለከተ ለቤተልሔም ሴቶች መልካም ነገር ሳትናገር አልቀረችም፤ ያም ሆነ ይህ ስለ ሩት የሚገልጽ መልካም ወሬ ቦዔዝ ጆሮ ደርሷል። በተጨማሪም ቦዔዝ “ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ” በማለት ስለተናገረ ሩት ጣዖት ማምለኳን ትታ ይሖዋን ማምለክ እንደጀመረችም አውቋል።​—ሩት 2:12

እነዚህ ቃላት ሩትን ምንኛ አበረታተዋት ይሆን! በእርግጥም አንዲት የወፍ ጫጩት በወላጆቿ ክንፍ ሥር ስትሆን ደኅንነት እንደሚሰማት ሁሉ ሩትም በይሖዋ አምላክ ክንፎች ሥር ለመጠለል ወስና ነበር። ሩት በሚያጽናና መንገድ ስላናገራት ቦዔዝን አመሰገነችው። ከዚያም እስኪመሽ ድረስ መሥራቷን ቀጠለች።​—ሩት 2:13, 17

ሩት ያሳየችው በተግባር የተደገፈ እምነት በዛሬው ጊዜ አስቸጋሪ ከሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር ለምንታገል ሁሉ ግሩም ምሳሌ ነው። ሩት ሌሎች ድጋፍ ሊያደርጉላት እንደሚገባ አልጠበቀችም፤ በዚህም ምክንያት ለተደረገላት ነገር ሁሉ አመስጋኝ ነበረች። ሩት ያከናወነችው ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ቢሆንም የምትወዳትን አማቷን ለመንከባከብ ስትል ስትለፋ መዋል አላሳፈራትም። ለደኅንነቷ በማያሰጋት ሁኔታ ከጥሩ ሰዎች ጋር ሆና መሥራት ስለምትችልበት መንገድ የተሰጣትን ጥበብ ያዘለ ምክር በአመስጋኝነት ተቀብላ ሥራ ላይ አውላለች። ከሁሉ በላይ ደግሞ እውነተኛ መጠጊያ የምታገኘው በክንፉ ጥላ ሥር ካደረጋት ከአባቷ ከይሖዋ አምላክ እንደሆነ አልዘነጋችም።

እኛም እንደ ሩት ጽኑ ፍቅር የምናሳይ እንዲሁም ትሑት፣ ታታሪና አመስጋኝ በመሆን ረገድ ምሳሌነቷን የምንከተል ከሆነ በእምነታችን ለሌሎች ግሩም አርዓያ እንሆናለን። ይሁንና ይሖዋ ለሩትና ለኑኃሚን የሚያስፈልጋቸውን ያሟላላቸው እንዴት ነበር? ይህንን ወደፊት በዚህ ዓምድ በሚወጣ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.22 እስራኤላዊ ያልሆኑ ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሩት “አምላክ” የሚለውን የማዕረግ ስም ብቻ አለመጠቀሟ ትኩረት የሚስብ ነው፤ በበኩረ ጽሑፉ ላይ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን የግል ስምም ተጠቅማለች። ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል እንደሚከተለው የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “የሩት መጽሐፍ ጸሐፊ ይህች የባዕድ አገር ሴት የእውነተኛው አምላክ አምላኪ መሆኗን በዚህ መንገድ ጎላ አድርጎ ገልጿል።”

^ አን.29 ይህ፣ ሩት በትውልድ አገሯ ከምታውቀው ፈጽሞ የተለየ ግሩም ዝግጅት ነበር። በዚያ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች የሚኖሩ መበለቶች በደል ይደርስባቸው ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “አንዲት ሴት ባሏ ከሞተ በኋላ በአብዛኛው ደጋፊና ጧሪ የሚሆኗት ወንዶች ልጆቿ ነበሩ፤ ወንዶች ልጆች ከሌሏት ግን ያላት አማራጭ ራሷን ለባርነት መሸጥ ወይም ዝሙት አዳሪ መሆን ነበር፤ አለዚያ ግን ትሞት ነበር።”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እጥር ምጥን ያለ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ

የሩት መጽሐፍ ውድ የሆነ ትንሽ ዕንቁ እንዲሁም እጥር ምጥን ያለ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ እንደሆነ ተነግሮለታል። በእርግጥ የሩት መጽሐፍ የሚሸፍነው ታሪክም ሆነ ርዝመቱ ከእሱ ቀደም ከተጻፈውና የሩትን መጽሐፍ መቼት ለመረዳት ከሚያስችለን ከመሳፍንት መጽሐፍ ያነሰ ነው። (ሩት 1:1) የሁለቱም መጻሕፍት ጸሐፊ ነቢዩ ሳሙኤል ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የሩት መጽሐፍ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግሩም በሆነ ቦታ ላይ መቀመጡን እንደምትስማማ አያጠራጥርም። በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡትን ስለ ጦርነቶች፣ ወረራዎችና የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎች የሚገልጹ ታሪኮች ስናነብ ከቆየን በኋላ ወደ ሩት መጽሐፍ ስንሄድ ይሖዋ በየዕለቱ ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር የሚታገሉ ሰላማዊ ሰዎችንም ፈጽሞ እንደማይረሳ ያስታውሰናል። የአንድን ቤተሰብ ሕይወት የሚቃኘው ይህ አጭር ታሪክ ከፍቅር፣ ከእምነትና ከታማኝነት እንዲሁም የሚወዱትን ሰው በሞት ከማጣት ጋር በተያያዘ ሁላችንንም የሚጠቅም ግሩም ትምህርት ይዟል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩት ሐዘን በደረሰባት ወቅት ከኑኃሚን ጋር በመቀራረብ የጥበብ እርምጃ ወስዳለች

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል”

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩት ለራሷና ለኑኃሚን የሚያስፈልገውን ለማሟላት ስትል አድካሚና ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበረች