በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

አምላክ ይቅር ሲለን በደላችንን አያስታውስም ማለት ነው?

አምላክ ይቅር ሲለን በደላችንን አያስታውስም ማለት ነው?

መልሱ በአጭሩ ‘አዎን’ የሚል ነው። ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም [“አላስታውስባቸውም፣” የ1980 ትርጉም]።” (ኤርምያስ 31:34) ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ሲል በደላቸውን መልሶ እንደማያስታውስ በዚህ መንገድ አረጋግጦልናል። ይሁንና ይህ ሲባል የግዙፉ ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ፣ የሠራናቸውን በደሎች ይቅር ካለን በኋላ መልሶ ማስታወስ አይችልም ማለት ነው? ሕዝቅኤል ያሰፈረው ሐሳብ አምላክ ይቅር የሚለውና የሚረሳው እንዴት እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል።​—ሕዝቅኤል 18:19-22ን አንብብ።

ይሖዋ፣ ታማኝ ባልነበሩት የይሁዳ እና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት የፍርድ መልእክት አስተላልፎ ነበር። ብሔሩ በአጠቃላይ የይሖዋን አምልኮ የተወ ከመሆኑም ሌላ ምድሪቱ በዓመፅ ተሞልታ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ፣ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እንደምትጠፋ አስቀድሞ ተናገረ። ይሁንና ይሖዋ ይህን የፍርድ መልእክት ባስተላለፈበት ወቅት ተስፋ የሚፈነጥቅ ሐሳብም ተናግሯል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ምርጫ ማድረግ የሚችል ከመሆኑም ሌላ ለሚያደርገው ነገር ተጠያቂ ነው።​—ቁጥር 19 እና 20

አንድ ሰው መጥፎ ድርጊቱን ትቶ መልካም ነገር ማድረግ ቢጀምርስ? ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ ተመልሶ ሥርዐቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።” (ቁጥር 21) በእርግጥም ይሖዋ ከመጥፎ መንገዱ በመመለስ እውነተኛ የንስሐ ዝንባሌ የሚያሳይን ኃጢአተኛ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ ነው።​—መዝሙር 86:5

ይህ ግለሰብ ቀደም ሲል የሠራቸውን በደሎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ “በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም” ወይም አይታወስበትም በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 22) ንስሐ የገባው ኃጢአተኛ የሠራው በደል “አይታሰብበትም” ወይም አይታወስበትም እንደተባለ አስተውል። ይህ ሐሳብ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ማሰብ’ ወይም ‘ማስታወስ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ያለፈን ታሪክ መልሶ ከማሰብ የበለጠ ትርጉም አለው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ [ይህ ቃል] እርምጃ መውሰድን ያመለክታል፤ አሊያም ድርጊትን ከሚገልጹ ግሦች ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል።” ስለዚህ ‘ማሰብ’ ወይም ‘ማስታወስ’ እርምጃ መውሰድን ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ የፈጸመው በደል ‘እንደማይታሰብበት’ ሲናገር አንድ ጊዜ ይቅር ካለው በኋላ በዚያ በደል ምክንያት በግለሰቡ ላይ እርምጃ እንደማይወስድ መግለጹ ነው፤ ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ግለሰብ የይሖዋን ይቅርታ ካገኘ በኋላ ይሖዋ ያንን በደል አስታውሶ አይወቅሰውም ወይም አይቀጣውም። *

በ⁠ሕዝቅኤል 18:21, 22 ላይ ያለው፣ ይሖዋ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ የሚናገረው ሐሳብ ልብ ይነካል። ይሖዋ አንድ ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በኋላ ድጋሚ በእነዚያ ኃጢአቶች አይጠይቀንም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ በደላቸውን ወደኋላው የሚጥለው ያህል ነው። (ኢሳይያስ 38:17) ይህም ሲባል የፈጸሙትን ኃጢአት ይደመስስላቸዋል እንደ ማለት ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 3:19

ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ምሕረት ማግኘት ያስፈልገናል። ደግሞም ብዙ ጊዜ ኃጢአት እንሠራለን። (ሮም 3:23) ይሁንና ይሖዋ፣ እውነተኛ ንስሐ ከገባን እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ እንድናውቅ ይፈልጋል። ይቅር ሲለን ደግሞ የሠራነውን በደል ይረሳል፤ በሌላ አባባል የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች እንደ አዲስ እያነሳ ዳግመኛ አይወቅሰንም ወይም አይቀጣንም። ይህ እንዴት የሚያጽናና ሐሳብ ነው! ታዲያ የአምላክ ምሕረት ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ አያነሳሳህም?

በሐምሌ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከ⁠ሕዝቅኤል 6 እስከ 20

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በተመሳሳይም ‘በደልን ማሰብ’ ሲባል ኃጢአተኞችን መቅጣትን ሊያመለክት ይችላል።​—ኤርምያስ 14:10