በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በፊሊፒንስ የምትኖርና ጠጪ የነበረች አንዲት ሴት ከዚህ ልማዷ ለመላቀቅ ብሎም የቤተሰብ ሕይወቷን ለማሻሻል የረዳት ምንድን ነው? በአውስትራሊያ የሚኖርና ካራቴ የሚወድ አንድ ሰው ሰላማዊ የሆነ ወንጌላዊ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ግለሰቦች የሚሉትን እንስማ።

“ለውጥ ያደረግሁት በአንድ ጀምበር አልነበረም።”​ካርሜን አሌግሬ

የትውልድ ዘመን፦ 1949

የትውልድ አገር፦ ፊሊፒንስ

የኋላ ታሪክ፦ ጠጪ የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በካማሬኔስ ሱር ግዛት በምትገኝ ሳን ፌርናንዶ የምትባል ከተማ ነበር። ካደግሁ በኋላ ግን አብዛኛውን ሕይወቴን ያሳለፍኩት በሪዛል ግዛት ባለችው አንቲፖሎ ነው። አንቲፖሎ የምትገኘው ብዙ ዛፎች ባሉትና በሣር በተሸፈነ ተራራማ አካባቢ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ስሄድ አንቲፖሎ ብዙም ግርግር የሌለባት ትንሽ ከተማ ነበረች። ከመሸ በኋላ መንገድ ላይ እምብዛም ሰው አይታይም ነበር። አሁን ግን አንቲፖሎ አድጋ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ትልቅ ከተማ ሆናለች።

ወደ አንቲፖሎ ከመጣሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤንጃሚን ከሚባል ሰው ጋር ተዋወቅሁና ከጊዜ በኋላ ተጋባን። ይሁንና የትዳር ሕይወት ከጠበቅሁት በላይ ከባድ ሆነብኝ። ያሉብኝን ችግሮች ለመርሳት ስል አልኮል በብዛት መጠጣት ጀመርኩ። ባሕሪዬ መጥፎ እየሆነ መጣ፤ ይህም ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከእነሱ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ ራሴን መቆጣጠር ይከብደኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ትዕግሥት አልነበረኝም። ለባለቤቴ ጨርሶ አክብሮት አልነበረኝም። የቤተሰብ ሕይወታችን አስደሳች እንዳልነበር ግልጽ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? የባለቤቴ እህት፣ ኢዲታ የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች እኔና ቤንጃሚን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና ሐሳብ አቀረበችልን። እኛም መጽሐፍ ቅዱስን ብናጠና የቤተሰብ ሕይወታችን እንዲሻሻል እንደሚረዳን ተስፋ በማድረግ በሐሳቧ ተስማማን።

መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናን ስንሄድ ብዙ አስደሳች እውነቶችን ተማርን። በተለይ በ⁠ራእይ 21:4 ላይ የሚገኙት ቃላት ልቤን ነኩት። ይህ ጥቅስ ወደፊት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ገነት በሆነች ምድር ላይ ለሚኖሩት ሰዎች አምላክ ምን እንደሚያደርግላቸው ሲገልጽ “እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” ይላል። እኔም እነዚህን በረከቶች ከሚያገኙት ሰዎች መካከል ለመሆን ፈለግሁ።

በባሕሪዬና ባሉኝ ልማዶች ረገድ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። በእርግጥ ለውጥ ያደረግሁት በአንድ ጀምበር አልነበረም፤ ቀስ በቀስ ግን ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የነበረብኝን ችግር ማሸነፍ ቻልኩ። ከቤተሰቤ ጋር ባለኝ ግንኙነትም ደግና ታጋሽ መሆንን ተማርኩ። ከዚህም በላይ ባለቤቴን ማክበርና ቤተሰባችንን ለመምራት በሚያደርገው ጥረት ተባባሪ መሆን ጀመርኩ።

እኔና ቤንጃሚን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስንጀምር ያየነው ነገር በጣም አስደነቀን። ከመካከላቸው ቁማርተኛ፣ ከልክ በላይ የሚጠጣ ወይም የሚያዳላ ሰው አልነበረም። የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም ሰው የሚይዙት በአክብሮት ነበር። በመሆኑም እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘን እርግጠኞች ሆንን።​—ዮሐንስ 13:34, 35

ያገኘሁት ጥቅም፦ የቤተሰባችን ሕይወት ከፍተኛ መሻሻል አሳየ። አሁን እኔና ቤንጃሚን አስደሳች ትዳር ያለን ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች ማስተማር ያስደስተናል። ሁለት ወንዶች ልጆቻችን ከነሚስቶቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። ውሎ አድሮ እነሱም አብረውን ይሖዋን እንደሚያገለግሉ ተስፋ እናደርጋለን። በእርግጥም ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት አግኝተናል።

“የማልበገር ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።”​—ማይክል ብለንድስደን

የትውልድ ዘመን፦ 1967

የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

የኋላ ታሪክ፦ ካራቴ ይወድ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በኒው ሳውዝ ዌልስ በምትገኝ ኦበሪ የተባለች ውብ ከተማ ውስጥ ነው፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ሀብታሞች ናቸው። እንደ አብዛኞቹ ከተሞች ሁሉ በኦበሪም አንዳንድ የወንጀል ድርጊቶች ይፈጸሙ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ግን ኦበሪ የምትታወቀው ሰላማዊ ከተማ በመሆኗ ነው።

ያደግሁት በምቾትና በድሎት ነበር። ወላጆቼ የተፋቱት የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ቢሆንም እኔም ሆንኩ ወንድሜና ሁለቱ እህቶቼ ምንም ነገር እንዳይጎድልብን ጥረት ያደርጉ ነበር። ትምህርቴን የተከታተልኩት በአካባቢው ምርጥ በተባለ የግል ትምህርት ቤት ነው። አባቴ ትምህርቴን ስጨርስ በንግዱ ዓለም እንድሰማራ ይፈልግ ነበር። እኔ ግን ይበልጥ የማደላው ወደ ስፖርት ሲሆን ብስክሌት በመንዳትና በካራቴ ልዩ ችሎታ ነበረኝ። በመሆኑም በስፖርቱ መስክ ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ እንዲያመቸኝ ስል በአንድ የአውቶሞቢል ጥገና ቤት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ።

አቋሜ የተስተካከለና ጥሩ የአካል ብቃት ያለኝ መሆኑ ያኮራኝ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የማልበገር ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። የምፈልገውን ለማግኘት በጉልበቴ መጠቀም እችል ነበር። ይሁን እንጂ የካራቴ አሠልጣኜ ኃይሌን አላግባብ ላለመጠቀም እንደምታገል ሲያውቅ ራሴን እንድቆጣጠርና ጥሩ ሥነ ምግባር እንዳዳብር በደንብ አድርጎ አሠለጠነኝ። የታዛዥነትንና የታማኝነትን አስፈላጊነት ደጋግሞ ይገልጽልኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ይሖዋ ዓመፅን እንደሚጠላ ተማርኩ። (መዝሙር 11:5) መጀመሪያ ላይ ካራቴ ዓመፅ እንዳልሆነና በሌሎች ላይ ጉዳት የማያስከትል ስፖርት እንደሆነ አስብ ነበር። የካራቴ ስፖርት በጎ ምግባርንና የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ማዳበርን ስለሚደግፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር እንደሚጣጣም ይሰማኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩኝ ባልና ሚስት በጣም ታጋሾች ነበሩ። ‘የማርሻል አርት ስፖርትን ማቆም አለብህ’ ብለውኝ አያውቁም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግን ማስተማራቸውን ቀጠሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እያደገና ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ሥር እየሰደደ ሲሄድ ግን ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ ማየት ጀመርኩ። የይሖዋ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ስማር በጣም ተገረምኩ። ኢየሱስ ከፍተኛ ኃይል የነበረው ቢሆንም ኃይሉን የዓመፅ ድርጊት ለመፈጸም ተጠቅሞበት አያውቅም። ኢየሱስ “ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት የተናገራቸው በ⁠ማቴዎስ 26:52 ላይ የሚገኙት ቃላት በጥልቅ ነኩኝ።

ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማርኩ መጠን ለእሱ ያለኝ ፍቅርና አክብሮት እያደገ ሄደ። እጅግ ጠቢብና ኃያል የሆነው ፈጣሪያችን ለእኔ በግል እንደሚያስብልኝ ማወቄ ልቤን ነካው። ይሖዋ፣ እሱን የሚያሳዝን ነገር በማደርግበት ወይም ነገሮች ሁሉ ከአቅሜ በላይ እንደሆኑ ተሰምቶኝ ተስፋ በምቆርጥበት ወቅት እንኳ ጥረት ማድረጌን እስካላቆምኩ ድረስ ፈጽሞ እንደማይተወኝ ማወቄ በጣም አበረታታኝ። “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና” በማለት የሰጠው ተስፋ በእጅጉ አጽናናኝ። (ኢሳይያስ 41:13) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳሳየኝ ስገነዘብ ከፍቅሩ ሳልወጣ ለመኖር ቆረጥኩ።

ካራቴን መተው ከምንም ነገር በላይ እንደሚከብደኝ ገብቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ማድረጌ ይሖዋን እንደሚያስደስተው አውቅ ነበር፤ ከዚህም ሌላ እሱን ማገልገል ማንኛውም መሥዋዕትነት ቢከፈልለት እንደማያስቆጭ እርግጠኛ ነበርኩ። ውሳኔ እንዳደርግ የረዳኝ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም” በማለት ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 6:24 ላይ የተናገረው ሐሳብ ነው። በካራቴ ስፖርት መካፈሌን ሳልተው ይሖዋን በሙሉ ነፍስ አገለግላለሁ ማለት የማይቻል ነገር እንደሆነ ተገነዘብኩ፤ ምክንያቱም ሁለቱንም ለማድረግ ከሞከርኩ ለካራቴ ቅድሚያ መስጠቴ እንደማይቀር አውቅ ነበር። ማንን ማገልገል እንደምፈልግ መወሰን ነበረብኝ።

ካራቴን መተው ቀላል አልነበረም። በውስጤ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ይሰማኝ ነበር። በአንድ በኩል ይህን ውሳኔ ማድረጌ ይሖዋን እንደሚያስደስት ስለማውቅ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኝ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የካራቴ አሠልጣኜን እንደከዳሁት ሆኖ ተሰማኝ። በማርሻል አርት ስፖርት የሚካፈሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ አንድን ሰው መክዳትን ይቅር እንደማይባል ኃጢአት አድርገው ይመለከቱታል። አንዳንዶች በዚህ የተነሳ የሚያጋጥማቸውን ኀፍረት ከመሸከም ይልቅ ራሳቸውን ማጥፋትን ይመርጣሉ።

ለካራቴ አሠልጣኜ፣ ይህን ስፖርት የምተውበትን ምክንያት ማስረዳት በጣም አሳፍሮኝ ነበር። በመሆኑም ምንም ነገር ሳልናገር ከእሱና ከሌሎች የካራቴ ጓደኞቼ ጋር ያለኝን ማንኛውንም ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጥኩ። ካራቴን ማቆሜ ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ አውቅ ነበር። ሆኖም አዲሱን እምነቴን ለሌሎች ማካፈል የምችልበትን አጋጣሚ ሳልጠቀምበት በመቅረቴ በጥፋተኝነት ስሜት ተዋጥኩ። ይሖዋን ማገልገል ገና ሳልጀምር እሱን እንዳሳዘንኩት ሆኖ ተሰማኝ። ይህ ሁሉ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ አስከትሎብኛል። ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ስሞክር በውስጤ ከሚሰማኝ ሥቃይ የተነሳ ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ።

ይሖዋ በውስጤ ጥሩ ነገር እንዳለ ሳያይ አልቀረም፤ ምክንያቱም በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ከጎኔ ሆነው እንዲደግፉኝ አነሳስቷቸዋል። ያሳዩኝ ፍቅር፣ ማጽናኛቸውና ወዳጅነታቸው ከጠበቅሁት በላይ ነበር። በተጨማሪም ስለ ዳዊትና ስለ ቤርሳቤህ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ማጽናኛ አግኝቻለሁ። ዳዊት ከባድ ኃጢአቶችን ቢፈጽምም ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ ምሕረት አድርጎለታል። በዚያ ታሪክ ላይ ማሰላሰሌ ስለ ራሴ ድክመቶች ተገቢ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።

ያገኘሁት ጥቅም፦ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናቴ በፊት ስለ ማንም ደንታ ያልነበረኝ ሲሆን ሕይወቴ የሚያጠነጥነው በራሴ ዙሪያ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ከይሖዋና ለሰባት ዓመታት አብራኝ በትዳር ከቆየችው ውድ ባለቤቴ ባገኘሁት እርዳታ አሁን የሰው ችግር የሚገባኝ ሩኅሩኅ ሰው መሆን ችያለሁ። እኔና ባለቤቴ፣ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት መብት በማግኘታችን ተባርከናል። የይሖዋ ፍቅር የሌሎችን ሕይወት ሲለውጥ ማየቴ በካራቴ ውድድር አሸናፊ መሆን ከሚያስገኘው የበለጠ ደስታ አምጥቶልኛል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እጅግ ጠቢብና ኃያል የሆነው ፈጣሪያችን ለእኔ በግል እንደሚያስብልኝ ማወቄ ልቤን ነካው”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

“ለዚህ ግሩም ዓምድ አመሰግናችኋለሁ!”

ከዚህ በፊት ባሉት ገጾች ላይ የቀረቡትን የሕይወት ታሪኮች ወደሃቸዋል? እነዚህ ታሪኮች ከነሐሴ 2008 ጀምሮ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጡ ከቆዩት ከ50 የሚበልጡ የሕይወት ተሞክሮዎች ሁለቱ ብቻ ናቸው። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለው ተከታታይ ርዕስ በአንባቢዎቻችን ዘንድ ተወዳጅነት አትርፏል። ብዙዎች ይህን ዓምድ የሚወዱት ለምንድን ነው?

በእነዚህ ርዕሶች ላይ ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉን ግለሰቦች የተለያየ አስተዳደግና የኋላ ታሪክ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ስለ ይሖዋ አምላክ ከመማራቸው በፊት በሕይወታቸው ውስጥ ስኬታማ የነበሩ ቢሆኑም ሕይወታቸው ዓላማ ቢስ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ እንደ ግልፍተኝነት፣ የዕፅ ሱሰኝነት ወይም ጠጪነት ካሉ ከባድ ድክመቶች ጋር የሚታገሉ ነበሩ። ጥቂቶቹ ስለ ይሖዋ እየተማሩ ያደጉ ቢሆኑም እሱን ማምለክ ትተው የነበሩ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች በሙሉ አምላክን ለማስደሰት ሲባል ለውጥ ማድረግ የሚቻል ነገር መሆኑን ያሳያሉ። ደግሞም እንዲህ ማድረግ ጥቅም እንዳለው ያረጋግጣሉ። ታዲያ እነዚህ ታሪኮች በአንባቢዎቻችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል?

አንዲት አንባቢ በየካቲት 1, 2009 እትም ላይ የወጣው ዓምድ በአንድ የሴቶች እስር ቤት የሚገኙ አንዳንድ የሕግ ታራሚዎችን እንዴት እንደጠቀማቸው ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦

▪ “ብዙዎቹ እስረኞች በዓምዱ ላይ የቀረቡት ግለሰቦች ስሜት ይገባቸዋል። በተለይ ደግሞ ‘የበፊቱን’ እና ‘የአሁኑን’ ሕይወታቸውን የሚያሳዩት ፎቶግራፎች እንዲሁም ስለ ሰዎቹ የቀድሞ ሕይወት የሚናገረው አጭር መግለጫ እስረኞቹን በጣም ነክቷቸዋል። ብዙ እስረኞች ዓምዱ ላይ ከወጡት ሰዎች ጋር የሚመሳሰል አስተዳደግና የኋላ ታሪክ አላቸው። ሁለት እስረኞች እነዚህን ታሪኮች ካነበቡ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።”​—ሲ. ደብሊው.

በዚህ ዓምድ ላይ የቀረቡት ተሞክሮዎች በተለይ የአንዳንድ ሰዎችን ልብ በጥልቅ ነክተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያዝያ 1, 2011 እትም ይሖዋን ለማገልገል ሲል የግብረ ሰዶማዊነትን ሕይወት የተወውን የጓዋዳሉፔ ቪላሪልን ተሞክሮ ይዞ ወጥቷል። ይህን ተሞክሮ አስመልክቶ ከተላኩልን በርካታ ደብዳቤዎች መካከል ሁለቱን ብቻ እንመልከት፦

▪ “የጓዋዳሉፔ ተሞክሮ በጥልቅ ነክቶኛል። አንድ ሰው ለይሖዋና ለቃሉ ያለው ፍቅር ሕይወቱን ምን ያህል ሊለውጠው እንደሚችል ማየት በጣም ያስደስታል!”​—ኤል. ኤፍ.

▪ “ቀደም ሲል ግብረ ሰዶማውያንን ጨምሮ ለሁሉም ሰው እምነቴን ለማካፈል እጥር ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንዲህ ያሉትን ግለሰቦች ችላ እንደምል እንዲያውም እንደምርቃቸው አስተውያለሁ። ይህ ተሞክሮ አመለካከቴን ለማስተካከል ረድቶኛል። እንዲህ ዓይነቶቹን ግለሰቦች ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ማለትም የእሱ አምላኪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርጌ እንድመለከት ረድቶኛል።”​—ኤም. ኬ.

የብዙ አንባቢያንን ስሜት የኮረኮረው ሌላው ተሞክሮ ደግሞ በነሐሴ 1, 2011 እትም ላይ የወጣው የቪክቶሪያ ታግ ታሪክ ነው። ቪክቶሪያ ጥሩ አስተዳደግ እንዳልነበራት በተሞክሮዋ ላይ ገልጻለች። ይሖዋን ለዓመታት ስታገለግል ከኖረች በኋላም እንኳ እሱ እንደሚወዳት ለማመን ይቸግራት እንደነበር ተናግራለች። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚወዳት ቀስ በቀስ እንድታምን የረዳት ምን እንደሆነ ተርካለች። አንዳንድ አንባቢያን የእሷን ታሪክ በተመለከተ ምን እንዳሉ እንመልከት፦

▪ “ቪክቶሪያ የእኔን ተሞክሮ የተናገረች ያህል ነው የተሰማኝ። እኔም በሕይወቴ ውስጥ ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ደርሰውብኛል። ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ ዓመታት ቢያልፉም አሉታዊ ከሆኑ ሐሳቦች ጋር ሁልጊዜ እታገላለሁ። የቪክቶሪያ ተሞክሮ ግን ይሖዋ እኔን በሚያየኝ መንገድ ራሴን ለማየት እንድጥር አነሳስቶኛል።”​—ኤም. ኤም.

▪ “ወጣት ሳለሁ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የማየት ሱስ ስለነበረብኝ ይህን ልማድ ለማሸነፍ እታገል ነበር። በቅርቡ ይህ ልማድ አገረሸብኝ። ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲረዱኝ የጠየቅሁ ሲሆን ችግሬን በማሸነፍ ረገድ መሻሻል እያሳየሁ ነው። ሽማግሌዎቹም አምላክ እንደሚወደኝና ምሕረት እንደሚያደርግልኝ አረጋገጡልኝ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ፣ ይሖዋ ሊወደኝ እንደማይችል ስለማስብ የዋጋ ቢስነት ስሜት ያድርብኛል። የቪክቶሪያን ተሞክሮ ማንበቤ በጣም ረድቶኛል። አምላክ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል ማሰብ የልጁ መሥዋዕት የእኔን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ አይደለም የማለት ያህል እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ስለዚህ በዋጋ ቢስነት ስሜት በምዋጥበት ጊዜ ሁሉ ይህን ተሞክሮ እያነበብኩ ማሰላሰል እንድችል ገጹን ቆርጬ በማውጣት በቅርብ አስቀምጬዋለሁ። ለዚህ ግሩም ዓምድ አመሰግናችኋለሁ!”​—ኤል. ኬ.