በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚሰብኩት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚሰብኩት ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” በማለት ለተከታዮቹ የሰጠውን ትእዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ትእዛዝ ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚመለከት ነው? የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉንም ክርስቲያኖች እንደሚመለከት ያምኑ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለሰዎች እንድንሰብክና የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ [ኢየሱስ] አዘዘን” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42) ሐዋርያው ጳውሎስም “ግዴታ ተጥሎብኛል። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!” በማለት ጽፏል።​—1 ቆሮንቶስ 9:16

ጳውሎስና ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በአጠቃላይ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽመዋል። ስብከት ተለይተው የሚታወቁበት ሥራ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:28-32, 41, 42) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ይጥራሉ። ኢየሱስ የሰበከውን መልእክት ይኸውም ስለ “መንግሥተ ሰማያት” የሚናገረውን ምሥራች ለሰዎች ይሰብካሉ።​—ማቴዎስ 10:7

የመንግሥቱ መልእክት መሰበክ ያለበት ለእነማን ነው? ኢየሱስ በማንኛውም ቦታ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሊሰበክላቸው እንደሚገባ ጠቁሟል። ደቀ መዛሙርቱን “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) እንዲያውም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለሚያውቋቸው ወይም ሃይማኖት ለሌላቸው ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች ለመስበክ ጥረት ያደርጉ ነበር። (ቆላስይስ 1:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ለሁሉም ሰው ለመስበክ ይጥራሉ። *

የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ ከሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነው ዘዴ የትኛው ነው? ኢየሱስ መልእክቱን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ማዳረስ የሚቻልበትን መንገድ ያውቅ ስለነበር ወደ ከተሞችና መንደሮች እንዲሁም ወደ ሰዎች ቤት ሄደው እንዲሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን ልኳቸዋል። (ማቴዎስ 10:7, 11, 12) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ “ከቤት ወደ ቤት” መስበካቸውን ቀጥለው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:42) ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው እነሱም ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ሰብከዋል። (ዮሐንስ 4:7-26፤ 18:20፤ የሐዋርያት ሥራ 17:17) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ሁሉ ለመስበክ የሚጠቀሙበት ዘዴ ተመሳሳይ ነው።

ኢየሱስ፣ መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ የሚሆነው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 10:14፤ 24:37-39) ይህ ታዲያ ክርስቲያኖች መስበካቸውን እንዳይቀጥሉ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይገባል? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በደረሰበት አካባቢ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የሚፈልግ የነፍስ አድን ሠራተኞች ቡድን አባል ነህ እንበል፤ ለተወሰነ ጊዜ ከፈለጋችሁ በኋላ ያገኛችኋቸው ሰዎች ጥቂት ብቻ ስለሆኑ ተስፋ ቆርጠህ ፍለጋውን ታቆማለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው፤ እንዲያውም አንድም ሰው እንኳ ቢሆን በሕይወት ሊገኝ እንደሚችል ተስፋ እስካለ ድረስ ፍለጋህን ትቀጥላለህ። በተመሳሳይም ኢየሱስ፣ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ሰምተው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎችን የማግኘት አጋጣሚ እስካለ ድረስ በጽናት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ደቀ መዛሙርቱን አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 10:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16) የይሖዋ ምሥክሮች እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎችን ለማግኘት ከቤት ወደ ቤት የሚሰብኩ ሲሆን ይህንንም በማድረግ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ፤ እነዚህ ሰዎች በሕይወት መትረፋቸው የተመካው የመንግሥቱን መልእክት ሰምተው እርምጃ በመውሰዳቸው ላይ ነው።​—ማቴዎስ 22:37-39፤ 2 ተሰሎንቄ 1:8

እያነበብክ ያለኸው መጽሔት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘ ነው። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤትህ ሲመጡ አነጋግራቸው፤ አሊያም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት በ236 አገሮች ምሥራቹን እየሰበኩ ነው። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች 1.7 ቢሊዮን ሰዓት በስብከቱ ሥራ ያሳለፉ ሲሆን 8.5 ሚሊዮን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተዋል።