በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

“ኮከቡን” የላከው ማን ነው?

“ኮከቡን” የላከው ማን ነው?

▪ ሦስት ነገሥታት ወይም ጠቢባን አራሱን ኢየሱስን በግርግም ውስጥ ሲጎበኙት የሚያሳዩ ከኢየሱስ ልደት ጋር የተያያዙ ተውኔቶችን ወይም ፊልሞችን አይተህ ታውቃለህ? በዚህ ታሪክ መሠረት፣ አምላክ በኮከብ ተጠቅሞ እነዚህን ነገሥታት በቤተልሔም ወደሚገኝ ጋጣ መርቷቸዋል። ሜልኪዮር፣ ካስፓር እና ባልታዛር የተባሉትን የእነዚህን ሦስት ነገሥታት ስም በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ልጆች በቃላቸው አጥንተውታል። ሆኖም ይህ በሰፊው የሚታወቅ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል? በፍጹም። እንዲያውም በብዙ አቅጣጫዎች ስንመለከተው ታሪኩ ትክክል እንዳልሆነ ማየት ይቻላል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነሱ ሲናገር የተጠቀመው የግሪክኛ ቃል ነገሥታትንም ሆነ ጠቢባንን አያመለክትም። እነዚህ ሰዎች ሰብአ ሰገል ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች ነበሩ። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች ከዋክብትን እያዩ የሚጠነቁሉ አረማውያን ናቸው። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የእነዚህን ሰዎች ስምም ሆነ ብዛት አይገልጽም።

ሁለተኛ፣ ሰበአ ሰገል ወደ ኢየሱስ የመጡት መቼ ነበር? ሰዎቹ የመጡት ኢየሱስ አራስ እያለ በግርግም ውስጥ ተኝቶ በነበረበት ወቅት አይደለም። ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ “ወደ ቤትም ሲገቡ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት” በማለት ዘግቧል። (ማቴዎስ 2:11) ኢየሱስ በዚህ ወቅት በግርግም ውስጥ ሳይሆን ከወላጆቹ ጋር ቤት ውስጥ እንደነበር ልብ በል። ከዚህም ሌላ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከምሥራቅ ተነሥተው እዚያ እስኪደርሱ የተወሰኑ ወራት ሳይፈጅባቸው አይቀርም። በመሆኑም ቤተልሔም ሲደርሱ ኢየሱስ አራስ ሕፃን እንደማይሆን ግልጽ ነው።

ሦስተኛ፣ ኮከብ ቆጣሪዎቹን እንዲመራቸው “ኮከቡን” የላከው ማን ነው? አብዛኛውን ጊዜ የሃይማኖት አስተማሪዎች “ኮከቡን” የላከው አምላክ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና በእርግጥ “ኮከቡን” የላከው አምላክ ነው? “ኮከቡ” ሰዎቹን በመጀመሪያ የመራቸው ወደ ቤተልሔም እንዳልሆነ አስታውስ። ከዚህ ይልቅ ንጉሥ ሄሮድስ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም መራቸው። በዚያም እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች፣ ቀናተኛና ነፍሰ ገዳይ ለሆነው ለዚያ ንጉሥ ስለ ኢየሱስ መወለድ ነገሩት፤ ይባስ ብሎም “የአይሁድ ንጉሥ” እንደሚሆን በመናገር ሄሮድስ ሕፃኑን አጥብቆ እንዲጠላው አደረጉ። (ማቴዎስ 2:2) ተንኮለኛው ሄሮድስ፣ እሱም ለሕፃኑ ሊሰግድለት ስለሚፈልግ ያለበትን ትክክለኛ ቦታ እንዲያሳውቁት ጠየቃቸው። ከዚህ በኋላ “ኮከቡ” ሰብአ ሰገልን እየመራ ዮሴፍ እና ማርያም ወደሚገኙበት ቦታ ወሰዳቸው። በመሆኑም አምላክ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች ኢየሱስ እንዲገደል ምክንያት ይሆኑ ነበር። ደስ የሚለው ግን አምላክ በጉዳዩ ጣልቃ ገብቷል። ሄሮድስ፣ ኮከብ ቆጣሪዎቹ የጠየቃቸውን ነገር ሳያሳውቁት በዚያው እንደተመለሱ ሲረዳ በጣም ስለተናደደ በቤተልሔምና በአካባቢዋ የሚገኙ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ።​—ማቴዎስ 2:16

ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ኢየሱስን “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ” ብሎታል። (ማቴዎስ 3:17) እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦ አፍቃሪና ጻድቅ የሆነው ይህ አባት እሱ ራሱ የሰጠው ሕግ የሚከለክለውን መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ አረማዊ ኮከብ ቆጣሪዎችን እንደ መልእክተኞቹ አድርጎ ይጠቀማል? (ዘዳግም 18:10) የያዙት መልእክት ሄሮድስ በቅናት እንዲያብድ እንደሚያደርገው እያወቀ በአካባቢው በጣም አደገኛ ወደሆነው ነፍሰ ገዳይ በኮከብ ተጠቅሞ ይመራቸዋል? ከዚያም ራሱን መከላከል የማይችለው ልጁ ያለበትን ቦታ ለመግለጽ ያንኑ ኮከብ እና እነዚያኑ መልእክተኞች ይጠቀማል?

ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ጥሩ ወታደራዊ አዛዥ፣ የላቀ ችሎታ ያለውን ወታደሩን በጠላት ክልል ውስጥ አንድ አደገኛ ተልዕኮ እንዲፈጽም ይልከው ይሆናል። በዚህ ጊዜ አዛዡ፣ ወታደሩ ያለበትን ቦታ ለጠላት ያሳውቃል? እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ ልጁን ወደዚህ አደገኛ ዓለም ልኮታል። ታዲያ ራሱን መከላከል በማይችልበት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጁ ያለበትን ቦታ ለክፉው ንጉሥ ለሄሮድስ ያሳውቃል? በፍጹም ይህን አያደርግም!

ታዲያ “ኮከቡን” ወይም ኮከብ የሚመስለውን ነገር የላከው ማን ነው? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦ ኢየሱስ አድጎ በምድር የተሰጠውን ተልእኮ ሳይፈጽም በሕፃንነቱ እንዲሞት የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ማን ነው? ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ የሚመራው እንዲሁም ውሸትንና ዓመፅና የሚያስፋፋው ብሎም ነፍስ ማጥፋትን የሚያበረታታው ማን ነው? “ውሸታምና የውሸት አባት” እንዲሁም “በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ተናግሯል።​—ዮሐንስ 8:44