በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ትንባሆ የሚያመርት አንድ ገበሬ ሥራውን ብቻ ሳይሆን አጥብቆ የሚከተለውን ሃይማኖቱንም ጭምር ለመቀየር ያነሳሳው ምንድን ነው? አንዲት የአልኮል ሱሰኛ አኗኗሯን ለመለወጥ የሚያስችል ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚሉ እንስማ።

“የዚህ ትልቅ ቤተሰብ አባል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።”​ዲኖ አሊ

የትውልድ ዘመን፦ 1949

የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

የኋላ ታሪክ፦ ትንባሆ አምራች የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ወላጆቼ በ1939 ከአልባኒያ ተሰደው ወደ አውስትራሊያ የመጡ ሲሆን በኩዊንስላንድ ግዛት ውስጥ በምትገኝ መሪባ የምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ሰፈሩ። በዚህ አካባቢ በርካታ ሰርቢያውያን፣ ቦስኒያውያን፣ ግሪኮች ጣሊያናውያንና ሌሎችም ሰፍረዋል፤ እነዚህ ሰዎች የየራሳቸውን የሥነ ምግባር እሴቶች እንዲሁም ባሕልና ልማዳቸውን ይዘው መጥተው ነበር። መሪባ ትንባሆ የሚመረትባት አካባቢ ስለነበረች ወላጆቼም ይህንኑ ተክል ማልማት ጀመሩ።

ወላጆቼ እዚያ ከመጡ ብዙም ሳይቆይ ትልቋ እህቴ ተወለደች፤ ከዚያም ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼና እኔ ተከታትለን ተወለድን። የሚያሳዝነው ነገር ገና የአንድ ዓመት ሕፃን ሳለሁ አባቴ በልብ ሕመም ምክንያት ሞተ። እናቴም ሌላ ባል አግብታ አራት ወንዶች ልጆችን ወለደች። ሁላችንም ያደግነው በእንጀራ አባቴ የትንባሆ እርሻ ላይ ነው።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ከቤት ወጣሁ። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ሳይሚ ከተባለች ወጣት ጋር ትዳር መሠረትኩ፤ ሁለታችንም ሙስሊሞች ስለነበርን የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችን የተከናወነው በአካባቢው በሚገኝ መስጊድ ውስጥ ነበር። ዘመዶቼ በጠቅላላ ሙስሊሞች ነበሩ። ቁርዓንንና የነቢዩ መሐመድን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ እንዲሁም አንዲት ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤያለሁ። ቁርዓን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ነቢያት ስለሚናገር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ እነዚያ ነቢያት ስለኖሩበት ዘመን ለማወቅ ረድቶኛል።

ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ ይመጡ ነበር፤ እኔና ሳይሚ እነዚህ ሰዎች አዘውትረው የሚያመጡልንን መጽሔቶችና መጻሕፍት ማንበብ ያስደስተን ነበር። በተለያዩ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከእነሱ ጋር ጥሩ ውይይት አደርግ እንደነበር አስታውሳለሁ። በእያንዳንዱ ውይይታችን ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቼ መልስ ሲሰጡኝ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሱ ነበር እንጂ የግል አመለካከታቸውን አይናገሩም። ይህም በጣም ያስደንቀኝ ነበር።

 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን አብሬያቸው እንዳጠናና ስብሰባዎቻቸውም ላይ እንድገኝ ይጋብዙኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበርኩም። በሕይወቴ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር የራሴ እርሻ እንዲኖረኝ ማድረግና ትልቅ ቤተሰብ መመሥረት ነበር። የራሴ እርሻ እንዲኖረኝ የነበረኝ ምኞት ባይሳካም ውሎ አድሮ የአምስት ልጆች አባት መሆን ችያለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጀመሪያ ከተገናኘሁ ዘጠኝ ዓመታት ቢያልፉም ሃይማኖቴን ግን አልለወጥኩም። ያም ሆኖ የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ሁሉ ወስጄ ማንበብ ያስደስተኝ ነበር። ሁልጊዜ እሁድ እሁድ እኔና ሳይሚ ጽሑፎቹን ለማንበብ ጊዜ እንመድብ ነበር። በእነዚህ ዓመታት የተቀበልናቸውን መጽሔቶች በሙሉ አስቀምጠናቸዋል። ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣውን እምነቴን መፈታተን በጀመሩ ጊዜ ከእነዚህ መጽሔቶች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች አግኝቻለሁ።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ እንድቀበል ጫና ሊያደርግብኝ የሞከረ አንድ የኢቫንጀሊካን እምነት ሰባኪ አጋጥሞኝ ነበር። ይህ ሰው የሳይሚን ወንድምና ታናሽ ወንድሜን የእሱ እምነት ተከታይ እንዲሆኑ ማሳመን ችሎ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው የማውቃቸው ሰዎች ወደየራሳቸው ሃይማኖት ሊያስገቡኝ ይጥሩ ጀመር። አንዳንዶቹም የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያጣጥሉ ጽሑፎች ሰጡኝ። እነዚህ ተቺዎች፣ ለሚያስተምሩት ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡልኝ ብጠይቃቸውም ጥያቄዎቼን ሊመልሱልኝ አልቻሉም።

ይህ ሁሉ ተቃውሞ ቢደርስብኝም ወደኋላ አላልኩም፤ እንዲያውም ተቃውሞው ከይሖዋ ምሥክሮች በተቀበልኳቸው ጽሑፎች ተጠቅሜ መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ በጥልቀት እንድመረምርና እንዳጠና አድርጎኛል። በመጨረሻም የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በግሌ አላጠናሁም፤ ስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ግን ጀመርኩ። ዓይናፋር በመሆኔ መጀመሪያ ላይ ስብሰባ ስሄድ በጣም ፈርቼ ነበር፤ ይሁን እንጂ እዚያ ያገኘኋቸው ሰዎች ወዳጃዊ አቀባበል ያደረጉልኝ ከመሆኑም በላይ ትምህርቱን ወደድኩት። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰንኩ፤ ራሴን ለአምላክ ወስኜ በ1981 ተጠመቅሁ።

ባለቤቴ እየተታለልኩ እንዳይሆን አንዳንድ ጊዜ ስጋት ቢያድርባትም ውሳኔዬን ግን አልተቃወመችም። እንዲያውም ስጠመቅ ለማየት መጥታ ነበር። እኔም ብሆን የምማራቸውን እውነቶች ለእሷ ማካፈሌን አላቆምኩም። ከተጠመቅሁ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ለእረፍት ወጣ ብለን በመኪናችን ወደ ቤት እየተመለስን ሳለ ሳይሚ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ይህ ነገር ያልጠበቅሁት በመሆኑ እንዲህ ስትለኝ መንገዱን ስቼ ልወጣ ነበር! ሳይሚ በ1982 ተጠመቀች።

በአኗኗራችን ላይ አስፈላጊዎቹን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ፣ ትንባሆ ማምረት ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ስለሚጋጭ ይህን ሥራ መተው ነበረብኝ። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ያዕቆብ 2:8) ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይጋጭ ቋሚ ሥራ ለማግኘት የተወሰነ ጊዜ ወስዶብናል። ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክር ከሆንን በኋላ ለብዙ ዓመታት ያህል አንዳንዶቹ ዘመዶቻችን ርቀውን  ነበር። እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ለእነሱ ፍቅር ለማሳየት ጥረት አድርገናል። ውሎ አድሮ አመለካከታቸው ስለተቀየረ ግንኙነታችን ተሻሽሏል።

ያገኘሁት ጥቅም፦ እንደ ዓይናፋርነት፣ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮችና የቤተሰብ ተቃውሞ ያሉ የተለያዩ ፈተናዎችን ማለፌ ይሖዋ አምላክ እኔን በመርዳት ረገድ ምን ያህል ታጋሽ እንደሆነ አስተምሮኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አሁን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ እያገለገልኩ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከመድረክ ማስተማር አለብኝ። ይህን ማድረግ ለእኔ አሁንም ተፈታታኝ ነው፤ ምክንያቱም በጣም ስለምፈራ አንደበቴ ይተሳሰራል። ይሁን እንጂ ሳላሰልስ በመጸለይና በይሖዋ እርዳታ ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ችያለሁ።

እኔና ባለቤቴም ይበልጥ ተቀራርበናል፤ በመካከላችን ያለው የጠበቀ ወዳጅነት በምንም ነገር ሊተመን አይችልም። ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ ስህተቶችን የፈጸምን ቢሆንም እኛ የተማርናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በውስጣቸው ለመቅረጽ የቻልነውን ሁሉ ጥረናል። (ዘዳግም 6:6-9) በአሁኑ ጊዜ የበኩር ልጄና ባለቤቱ ሚስዮናውያን ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ በቤተሰብ ሆነን መገኘት ከጀመርን ብዙም ሳይቆይ ያስተዋልኩት አንድ ሁኔታ ከአእምሮዬ አይጠፋም። አዳራሹ አጠገብ መኪናዬን ካቆምኩ በኋላ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ተመለከትኳቸው። ከዚያም ቤተሰቤን “ምን ይታያችኋል?” ብዬ ጠየቅኋቸው። በአዳራሹ ውስጥ ያሉት ሰዎች አልባኒያውያን፣ አቦርጂኖች፣ አውስትራሊያውያን እና ክሮኤሽያውያን ስለነበሩ የተለያየ ባሕል፣ አስተዳደግና ቋንቋ ነበራቸው፤ ይሁንና እነዚህ ሰዎች ደስ የሚል ኅብረት እንዳላቸው በግልጽ ማየት ይቻላል። በአውስትራሊያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድማማቾችንና እህትማማቾችን ያቀፈው የዚህ ትልቅ ቤተሰብ አባል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።​—1 ጴጥሮስ 5:9

“እህቴ በእኔ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም።”​ኤሌና ቭላዲሚሮቭና ሴዮሚና

የትውልድ ዘመን፦ 1952

የትውልድ አገር፦ ሩሲያ

የኋላ ታሪክ፦ የአልኮል ሱሰኛ የነበረችና ራሷን ለመግደል የሞከረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በሞስኮ አቅራቢያ በምትገኝ ክራስነጎርስክ በምትባል ሰላማዊ የሆነች ትንሽ ከተማ ነበር። ወላጆቼ መምህራን ሲሆኑ እኔም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። የሙዚቃ ትምህርትም ተከታትዬ ነበር። ጥሩ ሕይወት የሚኖረኝ ይመስል ነበር።

ትዳር ከመሠረትኩ በኋላ ግን ከባለቤቴ ጋር የምንኖርበትን አካባቢ ቀየርን፤ በሄድንበት አካባቢ መሳደብ፣ መስከርና ማጨስ የተለመደ ነበር። በወቅቱ ባይገባኝም የምንኖርበት አካባቢ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። መጀመሪያ ላይ ወደ ጭፈራ ቤቶች የምሄደው ለመዝፈንና ጊታር ለመጫወት ብቻ ነበር። እዚያ ከገባሁ በኋላ ግን ሰዎቹ አብሬያቸው እንዳጨስና እንድጠጣ ይጋብዙኛል። ብዙም ሳይቆይ የአልኮል ሱሰኛ ሆንኩ።

ያለብኝ ሱስ ሕይወቴን ያበላሸው ጀመር። ከጊዜ በኋላ ይህ ሱስ በጣም እየባሰብኝ ሄዶ የመጨረሻው መጥፎ ደረጃ ላይ ደረስኩ፤ በዚህ ወቅት ምግብ እንኳ መብላት አቅቶኝ ነበር። መሞት ተመኝቼ የነበረ ሲሆን ራሴን ለመግደልም ሞከርኩ። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ሙከራዬ ባለመሳካቱ ደስተኛ ነኝ።

በዚህ ሁሉ ጊዜ እህቴ አዘውትራ እየመጣች ትጠይቀኝ ነበር። እህቴ የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳኝ እንደሚችል ልታስረዳኝ ትጥር ነበር። እኔ ግን  ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ስላልነበረኝ መጀመሪያ ላይ ፊት ነሳኋት። ይሁን እንጂ እህቴ በእኔ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም። ያሳየችኝ ትዕግሥትና ፍቅር ስለማረከኝ በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ መጠጥ ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። በዚያው ጊዜ አካባቢ አንድ የሰከረ ጎረቤቴ ደበደበኝ። ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰብኝ ሆስፒታል ገባሁ። አራት የጎድን አጥንቶቼ ተሰብረውና አንደኛው ዓይኔ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት ሆስፒታል ውስጥ መሆኔ መጠጥ ማቆሜ ያስከተለውን የሕመም ስሜት ለመቋቋም ረድቶኛል።

በዚያን ጊዜ አዘውትሬ እጸልይ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ⁠ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:55, 56 (NW) ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም አጽናንቶኛል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። በእርግጥ ድምፄን ትሰማለህ። እኔን ከማዳንና ለእርዳታ ከማሰማው ጩኸት ፊትህን አትመልስ።”

ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ እርግጠኛ ነኝ። ወደ ቀድሞ ሕይወቴ እንዳልመለስ የሚረዳኝ ብርታት ሰጥቶኛል። እርግጥ ነው፣ እንደገና መጠጣት ለመጀመር የተፈተንኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ በዚህ ፈተና ፈጽሞ ባለመሸነፌ ደስተኛ ነኝ።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ስቀጥል ባለቤቴ የቤተሰብ ራስ የመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ልደግፈው እንደሚገባ ተማርኩ። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ባለቤቴን እንደፈለግኩ ማዘዝ ስለለመድኩ ይህን ማድረግ ለእኔ ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። በአንድ ጀምበር መለወጥ ባልችልም እያደር የተሻልኩና ባለቤቴን ይበልጥ የምደግፍ ሚስት ሆኛለሁ።

ውዱ ባለቤቴ ያደረግኋቸውን ለውጦች ሲመለከት በጣም ተገረመ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ምንም ፍላጎት አልነበረውም። ይሁን እንጂ ማጨስ ለማቆም ስወስን “አንቺ ማጨስ ካቆምሽ እኔ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እጀምራለሁ!” አለኝ። ሁለታችንም በአንድ ቀን ማጨስ አቆምን።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ባለቤቴ ቃሉን አክብሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አብረን እናነባለን፣ ባነበብነው ነገር ላይ እናሰላስላለን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን።

እኔ በግል ያገኘሁትን ጥቅም ሳላነሳ የቤተሰባችን ሕይወት ብቻ እንኳ ምን ያህል እንደተሻሻለ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። ይሖዋ ወደ ራሱ ስለሳበኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። (ዮሐንስ 6:44) እህቴም በእኔ ፈጽሞ ተስፋ ባለመቁረጧ አመስጋኝ ነኝ። እህቴ ትዕግሥት ስላሳየችኝ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የሰዎችን ሕይወት እንደሚለውጥ በራሴ ሕይወት ማየት ችያለሁ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እህቴ ያሳየችኝ ትዕግሥትና ፍቅር ስለማረከኝ በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ