በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ለምን አስፈለገ?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ለምን አስፈለገ?

 በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ለምን አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰጠው ሐሳብ ጊዜ ያለፈበትና የማያፈናፍን ነው? አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችን ከሚከተሉት ችግሮች ይጠብቀናል፦

ከአባለዘር በሽታዎች

ከጋብቻ ውጭ ከሚከሰት እርግዝና

የትዳር መፍረስ ከሚያስከትለው ሥቃይ

ከሕሊና ወቀሳ

የሌሎች መጠቀሚያ መሆን ከሚያስከትለው ለራስ አክብሮት የማጣት ስሜት

ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ * በሰጠን ስጦታ እንድንደሰትና ጥቅም እንድናገኝ ይፈልጋል። አምላክ ‘የሚበጅህ ምን እንደሆነ ያስተምርሃል።’ (ኢሳይያስ 48:17) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ሕይወቱን የሚመራ ሰው የሚያገኛቸው ጥቅሞች፦

የአምላክን ሞገስ

የአእምሮ ሰላም

ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር

መልካም ስም

ለራስ አክብሮት ማትረፍ

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እየተመራህ ካልሆነስ? አኗኗርህን ማስተካከል ትችላለህ? አምላክ ለቀድሞው አኗኗርህ ይቅር ይልሃል?

እስቲ አስበው፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ሴሰኞች፣ አመንዝሮችና ግብረ ሰዶማውያን ነበሩ። ሆኖም የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለመቀየር የመረጡ ሲሆን ይህን በማድረጋቸውም በእጅጉ ተጠቅመዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) በዛሬው ጊዜም በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች  ተመሳሳይ ምርጫ አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች ልቅ የሆነ አኗኗራቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ ሲሆን ሕይወታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በማስማማታቸው ጥቅም አግኝተዋል። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችውን ሣራን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

“ወዲያው እፎይታ ተሰማኝ”

ሣራ፣ ልቅ የሆነው አኗኗሯ የምትጓጓለትን ነፃነትና እርካታ እንዳላስገኘላት ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “ሕሊናዬ በጋለ ብረት እንደተተኮሰ ያህል ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። በኃፍረት የተዋጥኩ ከመሆኑም ሌላ አርግዤ ወይም አሰቃቂ በሽታ ይዞኝ እንዳይሆን እጨነቅ ነበር። አምላክ መኖሩን ተጠራጥሬ አላውቅም፤ የተከተልኩት ጎዳና ስሜቱን እንደሚጎዳው አውቅ ነበር። በመሆኑም ርካሽ እንደሆንኩ የተሰማኝ ሲሆን ይህ ደግሞ ውስጤን ያንገበግበኝ ነበር።”

ውሎ አድሮ ሣራ ሕይወቷን ለመለወጥ የሚያስችል ውስጣዊ ጥንካሬ አገኘች። የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ወላጆቿን እንዲረዷት ጠየቀቻቸው። በተጨማሪም በአካባቢዋ በሚገኘው ጉባኤ የነበሩ የጎለመሱ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቀች። ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼና የጉባኤ ሽማግሌዎች ያሳዩኝ ደግነትና ፍቅር ከጠበቅሁት በላይ ነበር። ወዲያው እፎይታ ተሰማኝ።”

በአሁኑ ወቅት ሣራ ሁለት ልጆች ወልዳለች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ስለተከተልኩት ጎዳና ለልጆቼ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። የአምላክን መሥፈርቶች ችላ ማለቴ ያስከተለብኝን መዘዝ እንዲረዱ እፈልጋለሁ። ዓላማዬ አምላክ ስለ ፆታ ግንኙነት ያወጣውን መሥፈርት መከተል የሚያስገኛቸውን አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጥቅሞች እንዲያውቁ መርዳት ነው። አምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሰጠን ስንጎዳ ሊያየን ስለማይፈልግ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።”

አንተም ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን የአምላክ መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም መቅመስ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጣል፦ “የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል። . . . እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።”​—መዝሙር 19:8, 11 *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።

^ አን.20 መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ጠቃሚ ምክር ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግራቸው። አሊያም ደግሞ በዚህ መጽሔት ገጽ 4 ላይ ካሉት አድራሻዎች ለአንተ አመቺ ወደሆነው መጻፍ ወይም www.watchtower.org የሚለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ የሚሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የስሜት ቀውስ ያጋጥማቸዋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች የሚከተሉ ሰዎች ንጹሕ ሕሊና እና ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ይኖራቸዋል