በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ሰው ዋሽቶህ ያውቃል?

አንድ ሰው ዋሽቶህ ያውቃል?

 አንድ ሰው ዋሽቶህ ያውቃል?

የምታምነው ሰው እንደዋሸህ የማወቅን ያህል ስሜት የሚጎዱ ነገሮች ብዙ አይደሉም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ እንደተዋረድህ ሊሰማህ፣ ልትናደድ አልፎ ተርፎም የተከዳህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ውሸት ጓደኝነትንና ትዳርን ያፈርሳል፤ እንዲሁም ሰዎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲያጡ ያደርጋል።

ታዲያ አምላክን በተመለከተ ውሸት እንደተነገረህ ስታውቅማ ምን ሊሰማህ እንደሚችል ገምት። በተለይ ደግሞ ሃይማኖተኛ ሰው ከሆንክ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል፤ ቀጥሎ የተጠቀሱት ሰዎች ምን እንደተሰማቸው ተመልከት፦

● “ቤተ ክርስቲያኑ የከዳኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ።”​—ዲያን

● “በጣም ተናድጄ ነበር። የተሞኘሁ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፤ ተስፋ የጣልኩባቸውና ግብ ያደረግኳቸው ነገሮች መና እንደቀሩ ተገነዘብሁ።”​—ሉዊስ

አምላክን በተመለከተ ውሸት ተነግሮኝ ሊሆን ይችላል የሚለው ሐሳብ ለአፍታ እንኳ ወደ አእምሮህ እንዲመጣ አትፈልግ ይሆናል። የተማርከው ነገር እምነት ከምትጥልበትና ፈጽሞ አንተን የመጉዳት ዓላማ ከሌለው ሰው የሰማኸው ሊሆንና ይህ ሰው ደግሞ ወላጅህ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ፓስተር ወይም የቅርብ ጓደኛህ ሊሆን ይችላል። አንድን ትምህርት በሕይወት ዘመንህ ሁሉ አምነህበት ይሆናል። ይሁንና ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ አንድ ሐሳብ ውሸት የመሆን አጋጣሚ ሊኖረው ይችላል ቢባል አትስማማም? የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ይህ ሊያጋጥም እንደሚችል ያምኑ ነበር፤ ምክንያቱም “አንድ ሐሳብ ተደጋግሞ መነገሩ ውሸት የሆነውን ነገር እውነት አያደርገውም” ይሉ ነበር።

አንተስ ሰው ዋሽቶህ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በአንድ ወቅት ወደ አምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) አዎ፣ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን ከውሸት ለይተን ማወቅ እንድንችል የሚረዳንን ሐሳብ ይዟል።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተመለከተ የሚነገሩ አምስት የተለመዱ ውሸቶችን እንዴት እንደሚያጋልጥ ለምን አትመረምርም? ደግሞም እውነት በሕይወትህ ላይ በጎ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።