በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

 ከአምላክ ቃል ተማር

እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎች በማንሳት መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በመልሶቹ ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው?

ኢየሱስ ተከታዮቹን ያስተማረው፣ እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ እንደሆነ ነው። ይህ እውነተኛ ሃይማኖት ወደ ሕይወት ከሚወስድ መንገድ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ ይህን መንገድ አስመልክቶ “የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:14) አምላክ የሚቀበለው የእውነት ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተን አምልኮ ብቻ ነው። ሁሉም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አንድ እምነት ያላቸው መሆኑ በመካከላቸው መለያየት እንዳይኖር አድርጓል።​—ዮሐንስ 4:23, 24⁠ን፤ ዮሐንስ 14:6ን እና ኤፌሶን 4:4, 5ን አንብብ።

2. በክርስትና ውስጥ የሐሰት ትምህርቶች እየተስፋፉ የመጡት ለምንድን ነው?

ሐሰተኛ ነቢያት ክርስትናን የበከሉ ከመሆኑም በላይ የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ ተጠቅመውበታል። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የእሱ “በግ” እንደሆኑ አድርገው የሚያቀርቡ ቢሆንም ሥራቸው ግን እንደተራቡ ተኩላዎች ነው። (ማቴዎስ 7:13-15, 21, 23) ሐሰተኛ ክርስቲያኖች እየበዙ የመጡት በተለይ የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ነበር።​—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30ን አንብብ።

3. እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?

እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ይቀበላሉ። በውስጡ ከሚገኙት መመሪያዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። በመሆኑም እውነተኛው ሃይማኖት በሰብዓዊ አስተሳሰብ ላይ ከተመሠረተ ሃይማኖት ይለያል። (ማቴዎስ 15:7-9) እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ከሚሰብኩት ትምህርት ጋር የሚጋጭ አኗኗር አይከተሉም።​—ዮሐንስ 17:17ን እና 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።

እውነተኛው ሃይማኖት ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ከፍ ከፍ ያደርጋል። ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲታወቅ አድርጓል። ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ እንዲሁም ስለ አምላክ ስም መቀደስ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) አንተ በምትኖርበት አካባቢ በአምላክ ስም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስተምረው ሃይማኖት የትኛው ነው?​—ዮሐንስ 17:26ን እና ሮም 10:13, 14ን አንብብ።

  4. እውነተኞቹን የአምላክ አገልጋዮች ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብካሉ። አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ስለ መንግሥቱ እንዲሰብክ ነው። የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ነው። ኢየሱስ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት ይናገር ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ 8:1፤ 23:42, 43) በተጨማሪም ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሰብኩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። አንድ ሰው ስለ አምላክ መንግሥት ሊነግርህ ከመጣ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ?​—ማቴዎስ 10:7ን እና ማቴዎስ 24:14ን አንብብ።

የኢየሱስ ተከታዮች የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል አይደሉም። በፖለቲካ ጉዳዮችም ሆነ በእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። (ዮሐንስ 17:16) በተጨማሪም በዓለም ላይ የሚታዩትን ጎጂ ድርጊቶችና ዝንባሌዎች ለመኮረጅ አይሞክሩም።​—ያዕቆብ 1:27ን እና ያዕቆብ 4:4ን አንብብ።

5. እውነተኛው ክርስትና ተለይቶ የሚታወቅበት ዋነኛው ምልክት ምንድን ነው?

እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ከልብ ይዋደዳሉ። ዘር ሳይመርጡ ሁሉንም ሰዎች ማክበር እንዳለባቸው ከአምላክ ቃል ተምረዋል። ብዙውን ጊዜ የሐሰት ሃይማኖቶች በብሔራት መካከል የሚደረጉ ጦርነቶችን ሙሉ በሙሉ የሚደግፉ ቢሆንም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ግን እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። (ሚክያስ 4:1-4) ከዚህ ይልቅ የእውነተኛው ሃይማኖት አባላት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ምንም ሳይቆጥቡ ሌሎችን ለመርዳትና ለማበረታታት ይጠቀሙበታል።​—ዮሐንስ 13:34, 35ን እና 1 ዮሐንስ 4:20, 21ን አንብብ።

ታዲያ ምንጊዜም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩት፣ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ የሚያደርጉትና የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ የሚያውጁት እነማን ናቸው? እርስ በርስ የሚዋደዱና ፈጽሞ በጦርነት የማይካፈሉ አባላት ያሉት ሃይማኖት የትኛው ነው? ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።​—1 ዮሐንስ 3:10-12

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል።”​—ቲቶ 1:16