በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ትቢያ መሆናችንን ያስባል’

‘ትቢያ መሆናችንን ያስባል’

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ትቢያ መሆናችንን ያስባል’

“ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ሊለኝ ይችላል ብዬ አላስብም ነበር፤ ኃጢአት መሥራት ያስከተለብኝን ሸክም ዕድሜ ልኬን ተሸክሜ እንደምኖር ይሰማኝ ነበር።” ይህ ሐሳብ አንዲት ክርስቲያን ቀደም ሲል የፈጸመቻቸውን ስህተቶች አስመልክታ የጻፈችው ነው። በእርግጥም የሕሊና ወቀሳ ከባድ ሸክም ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የሚሰማቸውን ውስጣዊ ሥቃይ ሊያስታግሥ የሚችል የሚያጽናና ሐሳብ ይዟል። መዝሙራዊው ዳዊት በ⁠መዝሙር 103:8-14 ላይ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት።

ዳዊት “እግዚአብሔር መሓሪ” እንደሆነ እንዲሁም ‘ሁልጊዜ በደላችንን እንደማይከታተል’ ያውቅ ነበር። (ቁጥር 8-10) አምላክ ምሕረት ለማድረግ የሚያስችል መሠረት እስካገኘ ድረስ ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላል፤ እንዲሁም ምሕረት ከማሳየት ፈጽሞ ወደኋላ አይልም። የተዋጣለት ገጣሚ የነበረው ዳዊት አምላክ ለእኛ የሚያሳየንን ታላቅ ምሕረት ለማስረዳት ሦስት አነጻጻሪ ዘይቤዎችን ተጠቅሟል።

“ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት።” (ቁጥር 11) ምሽት ላይ ቀና ብለን ስንመለከት በከዋክብት በተሞላው ሰማይና በምድር መካከል ያለው ርቀት ልንገምተው ከምንችለው በላይ መሆኑን እንረዳለን። ዳዊት ይህን ንጽጽር በማቅረብ የይሖዋ ምሕረት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ እንድንገነዘብ አድርጎናል። አምላክ ይህን ምሕረት የሚያሳየው እሱን “ለሚፈሩት” በሌላ አባባል አንድ ምሑር እንደገለጹት “ትሑት ለሆኑና ሥልጣኑን ከልባቸው ለሚያከብሩ” ሰዎች ነው።

“ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።” (ቁጥር 12) ምሥራቅ ከምዕራብ ምን ያህል ይርቃል? ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር አይቻልም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “ክንፍ እንዳለህ አድርገህ ቁጠርና በሐሳብህ የቻልከውን ያህል ለመብረር ሞክር፤ የምትከንፈው በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ከሆነ በክንፍህ አየሩን በቀዘፍክ ቁጥር የዚያኑ ያህል ከምዕራብ እየራቅህ ትሄዳለህ።” ዳዊት ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲጽፍ መግለጽ የፈለገው አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል የሠራነውን በደል ልናስብ ከምንችለው በላይ ከእኛ እንደሚያርቅልን ነው።

“አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል።” (ቁጥር 13) ዳዊት ራሱ አባት እንደመሆኑ መጠን አንድ አፍቃሪ አባት ለልጆቹ ምን ያህል በጥልቅ እንደሚያስብ ያውቃል። እንዲህ ያለው አባት በተለይ ልጆቹ ችግር ላይ በሚወድቁበት ጊዜ ለእነሱ ርኅራኄ ለማሳየት ይገፋፋል። ዳዊት አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን ለምድራዊ ልጆቹ በተለይ ደግሞ ንስሐ የገቡ ልጆቹ በሠሩት ኃጢአት የተነሳ ልባቸው ‘በሚሰበርበትና በሚዋረድበት’ ጊዜ ምሕረት እንደሚያሳያቸው ማረጋገጫ ሰጥቶናል።​—መዝሙር 51:17

ዳዊት ከላይ ያሉትን ሦስት ዘይቤያዊ አነጋገሮች ከተጠቀመ በኋላ ይሖዋ ፍጽምና ለሌላቸው የሰው ልጆች ምሕረት እንዲያደርግ የሚገፋፋው ምን እንደሆነ ሲገልጽ “እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል” ብሏል። (ቁጥር 14) ይሖዋ ከአፈር እንደተፈጠርን እንዲሁም ድክመቶችና የአቅም ገደቦች እንዳሉብን ያውቃል። ይሖዋ ፍጽምና የጎደለን መሆናችንን ግምት ውስጥ ስለሚያስገባ ልባዊ ንስሐ እስካሳየን ድረስ “ይቅር” ይለናል።​—መዝሙር 86:5

ዳዊት የይሖዋን ምሕረት አስመልክቶ በተናገረው ሐሳብ ልብህ አልተነካም? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሴት አምላክ ይቅር ባይ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነገር ካጠናች በኋላ “በእርግጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ እንደምችል እየተሰማኝ መጥቷል፤ የሆነ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደልኝ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ለመናገር ተገፋፍታለች። * አንተስ ስለ አምላክ ምሕረትና ይህን ምሕረት ማግኘት ስለምትችልበት መንገድ ይበልጥ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አንተም የሆነ ሸክም ከላይህ ላይ እንደወረደልህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል።

በነሐሴ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከመዝሙር 87 እስከ 118

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ወደ ይሖዋ ቅረብ ከተባለው መጽሐፍ ላይ “‘ይቅር ባይ’ አምላክ” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 26⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በእርግጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ እንደምችል እየተሰማኝ መጥቷል፤ የሆነ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደልኝ ሆኖ ይሰማኛል”