በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ቀደም ሲል ብዙ ሚስቶች የነበሩትና የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወም የነበረ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የወሰነው ለምንድን ነው? የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር የነበረ አንድ ሰው እምነቱን እንዲለውጥ የገፋፋው ምንድን ነው? ጥሩ አስተዳደግ ያልነበራት አንዲት ሴት ለራሷ የነበራትን የጥላቻ ስሜት አሸንፋ ወደ አምላክ እንድትቀርብ የረዳት ምንድን ነው? የሄቪ ሜታል ሙዚቃ አፍቃሪ የነበረ አንድ ሰው መንፈሳዊ ሰው ለመሆን የተነሳሳው ለምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚከተሉትን የሕይወት ታሪኮች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

‘የተሻለ ባል መሆን ችያለሁ።’​—ሪጎቤር ኢዩቶ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1941

 • የትውልድ አገር፦ ቤኒን

 • የኋላ ታሪክ፦ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወምና ብዙ ሚስቶች የነበሩት

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት ቤኒን ውስጥ በሚገኘው ኮትኑ የተባለ ትልቅ ከተማ ነው። ያደግኩት በካቶሊክ እምነት ቢሆንም ወደ ቤተ ክርስቲያን የምሄደው አልፎ አልፎ ነበር። በዚያን ጊዜ ከአንድ በላይ ማግባት ሕጋዊ እውቅና ስለነበረው በምኖርበት አካባቢ የነበሩ አብዛኞቹ ካቶሊኮች ብዙ ሚስቶች ነበሯቸው። እኔም ውሎ አድሮ አራት ሴቶችን አገባሁ።

በ1970ዎቹ አብዮት በፈነዳ ጊዜ ለውጡ አገሬን እንደሚጠቅም አስቤ ነበር። አብዮቱን ሙሉ በሙሉ የደገፍኩ ከመሆኑም በላይ ፖለቲካ ውስጥ ገባሁ። የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ረገድ ገለልተኞች ስለነበሩ አብዮተኞቹ አይወዷቸውም ነበር። እኔም የይሖዋ ምሥክሮችን ከሚያሳድዱት ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። የይሖዋ ምሥክር ሚስዮናውያን በ1976 ከአገሪቱ ሲባረሩ ተመልሰው እንደማይመጡ እርግጠኛ ነበርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

የአብዮቱ ሕልውና በ1990 አከተመ። የሚገርመው ነገር፣ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክር ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ ገቡ። እኔም ምናልባት አምላክ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሳይሆን አይቀርም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በዚያው ሰሞን የሥራ ቦታዬን ቀይሬ ነበር። ከአዲሶቹ የሥራ ባልደረቦቼ መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክር ነበር፤ እሱም ስለሚያምንባቸው ነገሮች ለእኔ ለመንገር ጊዜ አልወሰደበትም። ይሖዋ የፍቅርና የፍትሕ አምላክ እንደሆነ የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሳየኝ። (ዘዳግም 32:4፤ 1 ዮሐንስ 4:8) እኔም በእነዚህ ባሕርያት ተማረኩ። ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለማወቅ ስለፈለግሁ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ።

ብዙም ሳልቆይ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። እዚያ ባየሁት እውነተኛ ፍቅር እጅግ ተደነቅኩ፤ ምክንያቱም ከተለያየ ዘርና የኑሮ ደረጃ የመጡ ቢሆንም በመካከላቸው መከፋፈል የለም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተቀራረብኩ መጠን የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች እነሱ መሆናቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።​—ዮሐንስ 13:35

ይሖዋን ማገልገል ከፈለግሁ የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን ለቅቄ መውጣት እንዳለብኝ ተረዳሁ። ሌሎች ምን ይሉኛል የሚለው ነገር አስፈርቶኝ ስለነበር ይህን እርምጃ መውሰድ ለእኔ ቀላል አልነበረም። በይሖዋ እርዳታ ከረጅም ጊዜ በኋላ በድፍረት የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን ለቅቄ ወጣሁ።

ያም ሆኖ ሌላ አንድ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅብኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በማጠናበት ጊዜ አምላክ ከአንድ በላይ ሚስቶች ማግባትን እንደማይፈቅድ ተማርኩ። (ዘፍጥረት  2:18-24፤ ማቴዎስ 19:4-6) በእሱ ፊት ተቀባይነት ያለው የመጀመሪያው ጋብቻዬ እንደሆነ ተረዳሁ። ስለዚህ ይህንን ጋብቻ ሕጋዊ አደረግኩ፤ ከዚያም ሌሎቹን ሚስቶቼን በቁሳዊ የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላላቸው ካደረግሁ በኋላ አሰናበትኳቸው። ከጊዜ በኋላ ከቀድሞ ሚስቶቼ መካከል ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ሚስቴ አሁንም ካቶሊክ ብትሆንም ይሖዋን ለማገልገል ያደረግሁትን ውሳኔ ታከብርልኛለች። እኔም ሆንኩ እሷ የተሻለ ባል መሆን እንደቻልኩ ይሰማናል።

በፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ ያለሁበትን ማኅበረሰብ ማሻሻል እንደምችል አስብ ነበር፤ ይሁን እንጂ ያደረግኋቸው ጥረቶች ከንቱ ሆነው ቀርተዋል። አሁን ለሰው ልጅ ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ ደስታ ያለው እውነተኛ ሕይወት መምራት የምችልበትን መንገድ ስላሳየኝ አመሰግነዋለሁ።

“እነዚህን አስፈላጊ ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም።”​—አልኢክስ ሌሞስ ሲልቨ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1977

 • የትውልድ አገር፦ ብራዚል

 • የኋላ ታሪክ፦ የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግሁት በሳኦ ፖሎ ግዛት ውስጥ ባለችው ኢቱ የምትባል ከተማ ሲሆን መኖሪያችን የሚገኘው በከተማው ዳርቻ ላይ ነበር። ይህ አካባቢ የሚታወቀው ወንጀል በብዛት የሚፈጸምበት በመሆኑ ነበር።

እጅግ ዓመፀኛና መጥፎ ሥነ ምግባር ያለኝ ሰው ነበርኩ። ከዚህም በላይ ዕፅ በማዘዋወር ተግባር ተጠላልፌ ነበር። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ወደ ዘብጥያ አሊያም ወደ መቃብር እንደሚያወርደኝ ተገነዘብኩ፤ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን አኗኗር እርግፍ አድርጌ ተውኩ። ከዚያ በኋላ የጴንጤቆስጤ እምነት ውስጥ በመግባት ውሎ አድሮ ፓስተር ሆንኩ።

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በማቀርበው አገልግሎት አማካኝነት በእርግጥም ሰዎችን መርዳት እንደምችል ተሰምቶኝ ነበር። እንዲያውም በማኅበረሰቡ የሬዲዮ ጣቢያ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞችን አስተላልፍ ስለነበረ በአካባቢው በጣም የታወቅሁ ሆንኩ። ሆኖም በጥቅሉ ሲታይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአባላቷ ደኅንነት ምንም ግድ እንደማይሰጣት፣ ይባስ ብሎም አምላክን የማክበሩ ጉዳይ ያን ያህል እንደማያሳስባት እየተገነዘብኩ መጣሁ። የቤተ ክርስቲያኒቱ ብቸኛ ዓላማ ገንዘብ ማጋበስ እንደሆነ ተሰማኝ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቅቄ ለመውጣት ወሰንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር እነሱ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለዩ እንደሆኑ ለማስተዋል ጊዜ አልፈጀብኝም። ከእነሱ ጋር በተያያዘ በጣም ያስደነቁኝ ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክንና ሰዎችን እንደሚወዱ በቃል ብቻ ሳይሆኑ በተግባርም ያሳያሉ። ሁለተኛ፣ በፖለቲካም ሆነ በጦርነት ውስጥ እጃቸውን አያስገቡም። (ኢሳይያስ 2:4) እነዚህ ሁለት ነገሮች እውነተኛውን ሃይማኖት ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰውን ቀጭን መንገድ እንዳገኘሁ እርግጠኛ እንድሆን አደረጉኝ።​—ማቴዎስ 7:13, 14

አምላክን ማስደሰት ከፈለግሁ አንዳንድ ትልልቅ ለውጦችን ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ለቤተሰቤ የበለጠ ትኩረት መስጠት ያስፈልገኝ ነበር። እንዲሁም ይበልጥ ትሑት መሆን ነበረብኝ። እነዚህን አስፈላጊ ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ተሳክቶልኛል። ባለቤቴ ባደረግኳቸው ለውጦች ተደንቃ ነበር። እርግጥ መጽሐፍ  ቅዱስን ማጥናት የጀመረችው ከእኔ በፊት ነው፤ የእኔን ለውጥ ስታይ ግን በጥናቷ ፈጣን እድገት አደረገች። ብዙም ሳይቆይ እኔም ሆንኩ እሷ የይሖዋ ምሥክር የመሆን ፍላጎት አደረብን። በመሆኑም ሁለታችንም በአንድ ቀን ተጠመቅን።

ያገኘሁት ጥቅም፦

እኔና ባለቤቴ ሦስቱ ልጆቻችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት መቻላችንን እንደ ትልቅ በረከት እንቆጥረዋለን። ቤተሰባችን በጣም ደስተኛ ነው። ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዳውቅ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። እውነት በእርግጥም የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል! ለዚህም እኔ ሕያው ምሥክር ነኝ።

“ንጹሕ እንደሆንኩና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት እንደጀመርኩ ይሰማኛል።”​—ቪክቶሪያ ታግ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1957

 • የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

 • የኋላ ታሪክ፦ ጥሩ አስተዳደግ ያልነበራት

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግሁት በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት በምትገኘው ኒውካስል የተባለች ከተማ ውስጥ ነው። ወላጆቼ ከወለዷቸው ሰባት ልጆች እኔ የመጀመሪያዋ ነኝ፤ አባቴ ኃይለኛ ሰው ከመሆኑም በላይ የወጣለት ጠጪ ነበር፤ እናቴም ብትሆን ኃይለኛ ሴት ነበረች። እናቴ ትደበድበኝ የነበረ ሲሆን ቅስም የሚሰብር ስድብም ትሰድበኝ ነበር። መጥፎ ልጅ እንደሆንኩና በገሃነመ እሳት እንደምሠቃይ በተደጋጋሚ ትነግረኝ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ማስፈራሪያ ያሸብረኝ ነበር።

እናቴ በምትደበድበኝ ጊዜ የሚደርስብኝ አካላዊ ጉዳት ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ያስቀረኝ ነበር። በ11 ዓመቴ ከወላጆቼ ተወስጄ በመጀመሪያ አንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ እንድኖር ተደረገ፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ወደ አንድ የሴቶች ገዳም ገባሁ። ዕድሜዬ 14 ዓመት ሲሞላ ከገዳሙ አምልጬ ሄድኩ። ወደ ወላጆቼ ቤት መመለስ ስላልፈለግሁ ከሲድኒ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኪንግስ ክሮስ የተባለ ቦታ፣ ጎዳና ላይ መኖር ጀመርኩ።

በጎዳና ላይ በምኖርበት ጊዜ አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ፣ አልኮል መጠጣትና የብልግና ምስሎችን ማየት ጀመርኩ፤ እንዲሁም ሴተኛ አዳሪ ሆንኩ። በተለይ በአንድ ወቅት የገጠመኝ ነገር በጣም አስደንግጦኝ ነበር። በወቅቱ የራሱ የምሽት ክበብ ባለው አንድ ግለሰብ አፓርታማ ውስጥ እኖር ነበር። አንድ ቀን ምሽት ሁለት ሰዎች ይህን ሰው ሊጠይቁት መጡ። እሱም ወደ መኝታ ቤቴ እንድሄድ ነገረኝ፤ ይሁን እንጂ እዚያ ሆኜ የሚያወሩትን ነገር እሰማቸው ነበር። የክበቡ ባለቤት ለእነዚህ ሰዎች ሊሸጠኝ እየተነጋገረ ነበር። ሐሳባቸው በጭነት መርከብ ላይ በድብቅ አሳፍረው ወደ ጃፓን ከወሰዱኝ በኋላ በአንድ ቡና ቤት ውስጥ ሊያሠሩኝ ነበር። እኔም በድንጋጤ በመስኮት በኩል ዘልዬ በመውጣት እርዳታ ለማግኘት ሸሸሁ።

በዚህ ጊዜ፣ ለጉብኝት ወደ ሲድኒ የመጣ አንድ ሰው አገኘሁ፤ እኔም የተወሰነ ገንዘብ ይሰጠኛል ብዬ በማሰብ ስለ ሁኔታዬ አስረዳሁት። እሱ ግን ገንዘብ በመስጠት ፈንታ ገላዬን መታጠብና ምግብ መብላት እንድችል ወዳረፈበት ቦታ ይዞኝ ሄደ። ሆኖም ነገሮች መልካቸውን ቀየሩና ከሰውየው ጋር ያለኝ ግንኙነት ቀጠለ። ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ ተጋባን።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር የተለያዩ ስሜቶች ተፈራረቁብኝ። የክፋት መንስኤ ሰይጣን መሆኑን ሳውቅ ተናደድኩ፤ ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ ስማር የኖርኩት ሥቃይ የሚያመጣብን አምላክ እንደሆነ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ሰዎችን በገሃነመ  እሳት እንደማይቀጣ ሳውቅ ትልቅ እፎይታ አገኘሁ፤ ምክንያቱም ይህ ትምህርት ከሕፃንነቴ ጀምሮ ያሸብረኝ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች ማንኛውንም ውሳኔ የሚያደርጉት በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ላይ ተመሥርተው መሆኑ አስደነቀኝ። እምነታቸውን በተግባር የሚያሳዩ ናቸው። እኔ አስቸጋሪ ሰው ነበርኩ፤ ይሁን እንጂ ምንም ነገር ልናገር ወይም ላድርግ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፍቅርና በአክብሮት ይይዙኝ ነበር።

ከምንም ነገር በላይ የከበደኝ ግን በውስጤ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት ማሸነፍ ነበር። ራሴን በጣም እጠላው የነበረ ሲሆን ይህ ስሜት ደግሞ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ በኋላም እንኳ ለረጅም ጊዜ ከውስጤ አልወጣ ብሎ ነበር። እኔ ይሖዋን እንደምወደው እርግጠኛ ብሆንም እሱ ግን እንደ እኔ ዓይነቱን ሰው ፈጽሞ ሊወድ አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሼ ነበር።

በዚህ ረገድ እውነተኛ የአመለካከት ለውጥ ያደረግሁት ከተጠመቅሁ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። በይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ንግግር በሚያቀርብበት ጊዜ ተናጋሪው ያዕቆብ 1:23, 24 ጠቀሰ። ይህ ጥቅስ የአምላክን ቃል ከመስታወት ጋር ያመሳስለዋል፤ ይህ ምሳሌያዊ መስታወት ይሖዋ እኛን በሚያይበት መንገድ ራሳችንን እንድናይ ሊረዳን እንደሚችል ተገነዘብኩ። ከዚያም ‘ምናልባት እኔ ራሴን የማይበት መንገድ ይሖዋ እኔን ከሚያይበት መንገድ የተለየ ይሆን እንዴ?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ ይህን አዲስ ሐሳብ መቀበል ከብዶኝ ነበር። ምክንያቱም ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይወደኝ የሚሰማኝ ስሜት ገና ከውስጤ አልወጣም ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ሕይወቴን የለወጠ አንድ ጥቅስ አነበብኩ። ጥቅሱ ኢሳይያስ 1:18 ሲሆን እዚያ ላይ ይሖዋ “ኑና እንዋቀስ፤ . . . ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ እንዲህ ያለኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፦ “ቪኪ፣ እስቲ ነይና እንዋቀስ። አንቺንም ሆነ የሠራሻቸውን ኃጢአቶች እንዲሁም የልብሽን ዝንባሌ አውቃለሁ፤ ደግሞም እወድሻለሁ።”

ያን ቀን ሌሊት እንቅልፍ በዓይኔ አልዞር አለ። ይሖዋ ሊወደኝ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አቃተኝ፤ ይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያም ድንገት አንድ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ፤ ይሖዋ ለረዥም ጊዜ ሲታገሠኝና ለእኔ ያለውን ፍቅር በብዙ መንገዶች ሲገልጽልኝ እንደነበር ተሰማኝ። ለካስ እኔ በተዘዋዋሪ መንገድ ይሖዋን “ፍቅርህ ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን እኔን ግን ልትወደኝ አትችልም። የልጅህ መሥዋዕትም ቢሆን የእኔን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ አይደለም” እያልኩት ነበር። በሌላ አባባል ቤዛውን መልሼ ወደ ይሖዋ የወረወርኩት ያህል ነበር። ሆኖም በዚህ የቤዛ ስጦታ ላይ ማሰላሰሌ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ እንደሚወደኝ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ንጹሕ እንደሆንኩና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት እንደጀመርኩ ይሰማኛል። ትዳሬ ተሻሽሏል፤ እንዲሁም ተሞክሮዬን ተጠቅሜ ሌሎችን መርዳት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ከምንጊዜውም የበለጠ ወደ ይሖዋ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።

“ይህ የጸሎቴ መልስ መሆን አለበት።”​—ሰርጌ ቦታንኪን

 • የትውልድ ዘመን፦ 1974

 • የትውልድ አገር፦ ሩሲያ

 • የኋላ ታሪክ፦ የሄቪ ሜታል ሙዚቃ አፍቃሪ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት የዝነኛው ሙዚቃ አቀናባሪ ፒዮተር ኢልዪች ቻይኮቭስኪ የትውልድ ቦታ በሆነችው በቮትኪንስክ ነው። ቤተሰባችን ድሃ ነበር። አባቴ በጣም ብዙ ጥሩ ባሕርያት ያሉት ቢሆንም የመጠጥ ሱስ ስለነበረበት በቤተሰባችን ውስጥ ሁልጊዜ ውጥረት እንደነገሠ ነበር።

በትምህርቴ ያን ያህል ጎበዝ የምባል ልጅ አልነበርኩም፤ በዚህም ምክንያት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የበታችነት ስሜት እያደረብኝ መጣ። ራሴን ማግለልና ሰዎችን መጠራጠር ጀመርኩ። ትምህርት ቤት መሄድ በጣም ያስጨንቀኝ  ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ክፍል ውስጥ ሪፖርት በማቀርብበት ወቅት በሌላ ጊዜ ቢሆን በቀላሉ ልገልጸው የምችለውን ሐሳብ እንኳ መናገር ብዙ ጊዜ ያቅተኝ ነበር። ስምንተኛ ክፍልን ሳጠናቅቅ ሰርተፊኬቴ ላይ “የሚያውቃቸው ቃላት በጣም ውስን ናቸው፤ ሐሳቡን መግለጽም አይችልም” የሚል አስተያየት ተጽፎ ነበር። ይህ አስተያየት ቅስሜን የሰበረው ከመሆኑም ባሻገር ከበፊቱ ይበልጥ የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲሰማኝ አደረገኝ። በዚህ ጊዜ የመኖሬ ትርጉም ምን እንደሆነ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ጀመርኩ። መጠጣት የጀመርኩ ሰሞን መጠጥ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኝ ነበር። ሆኖም እያደር ከመጠን በላይ መጠጣት ስጀምር ሕሊናዬ እረፍት ነሳኝ። ሕይወቴ ትርጉም የለሽ ሆነብኝ። ጭንቀቴ በጣም እየጨመረ ከመሄዱ የተነሳ ለብዙ ቀናት ከቤት ሳልወጣ የምቆይባቸው ጊዜያት ነበሩ። በመሆኑም ራሴን ስለ ማጥፋት ማሰብ ጀመርኩ።

ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ለጊዜውም ቢሆን ፋታ የሚሰጥ አንድ አዲስ ነገር አገኘሁ። የሄቪ ሜታል ሙዚቃ ማዳመጥ ጀመርኩ። ሙዚቃውን ሳዳምጥ ውስጣዊ ብርታት እያገኘሁ መጣሁ፤ እንዲሁም የሄቪ ሜታል ሙዚቃ አድናቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ፀጉሬን አሳደግሁ፤ ጆሮዬን ተበሳሁ፤ እንዲሁም የማደንቃቸው ሙዚቀኞች የሚለብሱት ዓይነት ልብስ መልበስ ጀመርኩ። ውሎ አድሮም ለምንም ነገር ግድ የለሽና ግልፍተኛ ሰው ሆንኩ፤ ብዙ ጊዜም ከቤተሰቤ ጋር እጋጭ ነበር።

የሄቪ ሜታል ሙዚቃን መስማት ደስተኛ እንደሚያደርገኝ አስቤ የነበረ ቢሆንም እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። ባሕርዬ ተቀይሮ ሌላ ዓይነት ሰው ሆንኩ! በተጨማሪም ትልቅ ቦታ ስለምሰጣቸው ኮከብ ሙዚቀኞች አንዳንድ መጥፎ ነገሮችን ስሰማ እንደተታለልኩ ተሰማኝ።

አሁንም እንደገና ራሴን ስለ ማጥፋት ማሰብ ጀመርኩ፤ በዚህ ጊዜ ግን አምርሬ ነበር። ይህን እርምጃ እንዳልወስድ የያዘኝ ነገር ቢኖር ራሴን ባጠፋ እናቴ ምን ያህል እንደምትጎዳ ማሰቤ ነው። ምክንያቱም እናቴ በጣም ትወደኛለች፤ ደግሞም ለእኔ ስትል ብዙ ነገር አድርጋለች። ሁኔታው ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከትቶኝ ነበር። በሕይወት መቀጠል አልፈለግሁም፤ ይሁን እንጂ ራሴን ማጥፋትም አልቻልኩም።

ነገሮችን ለመርሳት ስል በሩሲያ ቋንቋ የተዘጋጁ ምርጥ የሥነ ጽሑፎች ሥራዎችን ማንበብ ጀመርኩ። ካነበብኳቸው ታሪኮች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል ስለነበር አንድ ጀግና ሰው የሚገልጽ ነበር። ከዚያም ለአምላክና ለሌሎች ሰዎች የሆነ ነገር እንዳደርግ የሚገፋፋ ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ። ወዲያውኑም ከዚያ በፊት ፈጽሞ አድርጌው የማላውቀውን ነገር አደረግኩ፤ የልቤን አውጥቼ ለአምላክ በጸሎት ነገርኩት። ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የምችልበትን መንገድ እንዲያሳየኝ አምላክን ለመንኩት። በምጸልይበት ወቅት በሚገርም ሁኔታ የእፎይታ ስሜት ተሰማኝ። ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ደግሞ ከዚያ በኋላ የተከሰተው ነገር ነው። ከሁለት ሰዓት ቆይታ በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤቴ መጥታ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ግብዣ አቀረበችልኝ። ‘መቼም ይህ የጸሎቴ መልስ መሆን አለበት’ ብዬ አሰብኩ። ደስተኛ የሆነ ሕይወት ሀ ብዬ መኖር የጀመርኩበት ያን ቀን ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ምንም እንኳ በጣም ከባድ ቢሆንም ከሄቪ ሜታል ሙዚቃ ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሙሉ አውጥቼ ጣልኩ። ሆኖም ሙዚቃው ከአእምሮዬ ሳይወጣ ለረዥም ጊዜ ቆየ። የሄቪ ሙዚቃ በተከፈተበት አካባቢ በአጋጣሚ ካለፍኩ ወዲያውኑ የቀድሞ ሕይወቴ ትዝ ይለኛል። እነዚያ መጥፎ ትዝታዎች አሁን በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ ሥር እየሰደዱ ባሉት መልካም ነገሮች ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ አልፈለግሁም። ስለዚህ እንዲህ ካሉት ስፍራዎች ለመራቅ ጥረት አደርግ ነበር። ደግሞም ስለ ቀድሞው ነገር ለማሰብ በምፈተንበት ጊዜ አጥብቄ እጸልይ ነበር። እንዲህ ማድረጌ ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ እንዳገኝ ረድቶኛል።​—ፊልጵስዩስ 4:7

መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ ስሄድ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለሌሎች የማካፈል ግዴታ እንዳለባቸው ተማርኩ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህን ፈጽሞ ላደርገው እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እየተማርኳቸው የነበሩት አዳዲስ ነገሮች ከፍተኛ ደስታና ውስጣዊ ሰላም አስገኝተውልኛል። ሌሎችም እነዚህን እውነቶች መማር እንደሚያስፈልጋቸው አውቅ ነበር። ምንም እንኳ ፍርሃት ቢያድርብኝም የተማርኳቸውን ነገሮች ለሌሎች መናገር ጀመርኩ። በጣም የሚያስገርመው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች ሰዎች መናገሬ በራስ የመተማመን ስሜቴን ከፍ አደረገልኝ። እንዲሁም የማምንባቸው አዳዲስ እውነቶች በልቤ ውስጥ ሥር እንዲሰዱ አደረጋቸው።

ያገኘሁት ጥቅም፦

አሁን አስደሳች ትዳር ያለኝ ሲሆን ታናሽ እህቴንና እናቴን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ በመርዳቴ ደስተኛ ሆኛለሁ። አምላክን ማገልገልና ሌሎች ስለ እሱ እንዲማሩ መርዳት ትርጉም ያለው እውነተኛ ሕይወት እንድመራ አድርጎኛል።