በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች ስለ አምላክ መማር ይኖርባቸዋል?

ልጆች ስለ አምላክ መማር ይኖርባቸዋል?

ልጆች ስለ አምላክ መማር ይኖርባቸዋል?

“ሃይማኖት ጥላቻን አስተማረን እንጂ እርስ በርስ እንድንዋደድ አላደረገንም።”​—ጆናታን ስዊፍት፣ እንግሊዛዊ ደራሲ

ስዊፍት ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገሩት በ18ኛው መቶ ዘመን ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በእሳቸው ሐሳብ ይስማማሉ። እንዲያውም ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ አምላክ የማስተማር መብት ሊኖራቸው አይገባም የሚል እምነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ልጆች ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ማደጋቸው በሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይሰማቸዋል።

አንተስ ምን ትላለህ? ከሚከተሉት ሐሳቦች ውስጥ ይበልጥ ምክንያታዊ የሚመስልህ የትኛው ነው?

● ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ አምላክ እንዲያስተምሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም።

● ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መንፈሳዊ ጉዳዮችን አንስተው መወያየት ከመጀመራቸው በፊት ልጆቹ እስኪያድጉ ድረስ መጠበቅ አለባቸው።

● ወላጆች አምላክን በተመለከተ ያላቸውን እምነት ለልጆቻቸው ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ሊነግሯቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ወላጆች ልጆቻቸው እየበሰሉ የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ በመጠቀም ጉዳዩን እንዲመረምሩ ሊያበረታቷቸው ይገባል።

● ልጆች የወላጆቻቸውን እምነት ያለምንም ማንገራገር መቀበል አለባቸው።

ልጆች ስለ ሃይማኖት መማራቸው ይጎዳቸዋል?

አሳቢ የሆነ ማንኛውም ወላጅ ልጁን መጉዳት አይፈልግም። ይሁን እንጂ የተገኙት ማስረጃዎች ልጆች ስለ አምላክ መማር የለባቸውም የሚለውን አባባል የሚደግፉ ናቸው? ላለፉት አሥርተ ዓመታት ተመራማሪዎች የወላጆች ሃይማኖታዊ እምነት በልጆች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ጥልቅ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ታዲያ የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው?

ተመራማሪዎች፣ ሃይማኖት መጥፎ ተጽዕኖ ከማሳደር ይልቅ ለአንድ ልጅ እድገት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ደርሰውበታል። በ2008 ሶሻል ሳይንስ ሪሰርች * በተሰኘ ጽሑፍ ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ሪፖርት “ሃይማኖት በወላጅና በልጅ መካከል ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክረው ይኸውም አንድን ልጅ ከእናቱም ሆነ ከአባቱ ጋር እንደሚያቀራርበው ታይቷል” በማለት ተናግሯል። ይኸው ሪፖርት አክሎ “ሃይማኖትና መንፈሳዊነት በብዙ ልጆች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ይመስላል፤ እነዚህ ነገሮች በቤተሰብ መካከል ላለው ግንኙነትም ወሳኝ ናቸው” በማለት ተናግሯል። ይህ የጥናት ውጤት ኢየሱስ ክርስቶስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ምን ያህል እንደሚስማማ ልብ በል።​—ሉቃስ 11:28

ልጆች ስለ አምላክና ስለ ሃይማኖት ከመማራቸው በፊት እስኪያድጉ ድረስ መቆየት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ አመለካከት የሚከተለውን እውነት ከግምት ያላስገባ ነው፦ የአንድ ልጅ አእምሮ ለመሞላት እንደተዘጋጀ ባዶ ባልዲ ነው። በእርግጥም ወላጆች ምርጫ የማድረግ ፈተና ተደቅኖባቸዋል፤ አንድም፣ ጠቃሚ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎችና እምነቶች በማስተማር ይህን “ባልዲ” ቤት ውስጥ መሙላት አለዚያም ከቤት ውጭ ያሉ የተለያዩ አስተሳሰቦች የልጃቸውን አእምሮና ልብ እንዲሞሉት መተው።

ቁልፉ ምንድን ነው?

ሃይማኖት አለመቻቻልና ጥላቻ እንዲቀጣጠል የማድረግ ኃይል እንዳለው ታሪክ አረጋግጧል። ታዲያ ወላጆች ጆናታን ስዊፍት የገለጹት ዓይነት መጥፎ ውጤት እንዳይደርስ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ልጆቻቸው ሌሎችን እንዲወዱ የሚረዳቸውን ሃይማኖታዊ እምነት ማስተማር የሚችሉትስ እንዴት ነው?

ቁልፉን ለማግኘት ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ይኖርብናል፦ (1) ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው? (2) እነሱን ማስተማር የሚኖርበት ማን ነው? (3) ከሁሉ የተሻለው የማስተማሪያ ዘዴ የትኛው ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ይህ ጥናት የተመሠረተው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩ ቁጥራቸው ከ21,000 የሚበልጥ ልጆች እንዲሁም ከልጆቹ ወላጆችና አስተማሪዎች በተሰበሰበ መረጃ ላይ ነው።