በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር ያለበት ማን ነው?

ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር ያለበት ማን ነው?

 ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር ያለበት ማን ነው?

“ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል።”​—ሉቃስ 6:40

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ አምላክ ለማስተማር ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። በቂ ትምህርት እንደሌላቸው አለዚያም ጥሩ አስተማሪዎች ለመሆን የሚያስችል መንፈሳዊ እውቀት እንደሚጎድላቸው ይሰማቸው ይሆናል። በዚህም የተነሳ ወሳኝ የሆነውን ይህን ኃላፊነት ለአንድ ዘመዳቸው ወይም ለሃይማኖት መሪ መተው ይመርጡ ይሆናል።

ይሁንና ለልጆች ሃይማኖታዊ እውነቶችንና ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎችን ለማስተማር ከማንም የተሻለ ብቃት ያለው ማን ነው? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ተመልከት፤ ከዚያም እነዚህን ሐሳቦች ተመራማሪዎች ከደረሱበት መደምደሚያ ጋር አወዳድር።

የአባት ድርሻ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።”​ኤፌሶን 6:4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ተመራማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ፦ አባቶች ጠንካራ ሃይማኖታዊ እምነት ማዳበራቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? በ2009 ታትሞ የወጣው ፋዘርስ ሪሊጂየስ ኢንቮልቭመንት ኤንድ ኧርሊ ቻይልድሁድ ቢሄቪየር የተሰኘ አንድ ጽሑፍ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ወንዶች፣ ባሉበት ሃይማኖት ውስጥ ከሰዎች ጋር ኅብረት መፍጠራቸው የተሻሉ አባቶች እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። ሃይማኖት ለግለሰቦች ማኅበራዊ ድጋፍ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ከመጥፎ ነገር እንዲቆጠቡ ጥበቃ ይሆናል፤ አልፎ ተርፎም ሕይወትን  ለመምራት የሚቻልበትን መንገድ የሚጠቁሙ ትምህርቶችንና መመሪያዎችን ይሰጣቸዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን በማሳደግና በማሠልጠን ረገድ አባቶች ያላቸውን ድርሻ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ምሳሌ 4:1፤ ቆላስይስ 3:21፤ ዕብራውያን 12:9) ይሁን እንጂ ይህ ምክር በዛሬው ጊዜም ይሠራል? በ2009 የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ፣ አባቶች በልጆቻቸው ላይ ስለሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ የሚያብራራ አንድ ጽሑፍ አሳትሞ ነበር። ተመራማሪዎቹ፣ አባቶቻቸው ትኩረት ሰጥተው በትጋት ያሳደጓቸው ልጆች የሌሎችን ስሜት የሚረዱና ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት ያላቸው ሰዎች የመሆናቸው አጋጣሚ እንደሚጨምር ደርሰውበታል። ወንዶች ልጆች መጥፎ ጠባይ የማዳበር አጋጣሚያቸው የሚቀንስ ሲሆን ሴቶች ልጆች ደግሞ የተሻለ የአእምሮ ጤንነት ያላቸው የመሆን አጋጣሚያቸው የሰፋ ነው። በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በአሁኑ ጊዜም ጠቃሚ ነው።

የእናት ድርሻ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የእናትህንም ትምህርት አትተው።”​ምሳሌ 1:8

ተመራማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ፦ በ2006 የታተመው ሃንድቡክ ኦቭ ቻይልድ ሳይኮሎጂ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እናቶች ከእያንዳንዱ ልጃቸው ጋር በተናጥል የሚያሳልፉት የጊዜ መጠን አባቶች ከሚያሳልፉት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በአማካይ ከ65 እስከ 80 በመቶ ብልጫ አለው፤ ይህ ሬሾ በብዙ አገሮች ተመሳሳይ ነው።” አንዲት እናት ከልጆቿ ጋር ይህን ያህል ጊዜ አብራ የምታሳልፍ ከመሆኑ አንጻር አነጋገሯ፣ ተግባሯና አስተሳሰቧ በልጇ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

እናትና አባት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገረውን ነገር ለልጆቻቸው ለማስተማር አብረው የሚሠሩ ከሆነ ለልጆቻቸው ቢያንስ ሁለት ውድ ስጦታዎችን እየሰጧቸው ነው ሊባል ይችላል። አንደኛ፣ ልጆቹ በሰማይ ካለው አባታቸው ጋር ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ የሚያገኙ ሲሆን ይህ ወዳጅነት ደግሞ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሊጠቅማቸው የሚችል ነው። ሁለተኛ፣ ልጆቹ የወላጆቻቸውን ምሳሌ በማየት አንድ ባልና ሚስት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ግቦች ላይ ለመድረስ እንዴት ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ይማራሉ። (ቆላስይስ 3:18-20) ወላጆችን ሌሎች ሊረዷቸው ቢችሉም ስለ አምላክና እሱ ለቤተሰብ አባላት ስለሰጠው የሥራ ድርሻ ለልጆቻቸው የማስተማሩ ኃላፊነት ግን የአባትና የእናት ነው።

ይሁንና ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር የሚኖርባቸው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የትኛው ነው?