በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው? ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የትኛው ነው?

ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው? ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የትኛው ነው?

 ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው? ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የትኛው ነው?

“ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።”​—ዘዳግም 6:6, 7

ወላጆች ልጆችን የማሠልጠኑ ኃላፊነት አንዳንድ ጊዜ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምክር ለማግኘት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ደግሞ በሚቀርብላቸው ለቁጥር የሚታክት ምክር የተነሳ ጭራሹኑ ግራ ይጋባሉ። ዘመዶችና ጓደኞች አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸውን ምክር ከመስጠት አይቦዝኑም። በሌላ በኩል ደግሞ መጻሕፍት፣ በመጽሔቶች ላይ የሚወጡ ሐሳቦችና የኢንተርኔት ድረ ገጾች ለወላጆች የሚሆኑ ምክሮችን ያለማቋረጥ በገፍ ያቀርባሉ፤ ምናልባትም ከእነዚህ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሊሆኑ ይችላሉ።

በአንጻሩ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ልጆቻቸውን ምን ማስተማር እንዳለባቸው የሚገልጽ አስተማማኝ ምክር ከመለገስ ባለፈ እንዴት ሊያስተምሯቸው እንደሚገባም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎችን ይሰጣል። ከላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሚያመለክተው ወላጆች በየዕለቱ ከልጆቻቸው ጋር ስለ አምላክ ማውራት የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ አምላክ ለማስተማር ከረዷቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮች መካከል ከዚህ በታች አራቱ ብቻ ቀርበዋል።

1. ፍጥረትን ተጠቅሞ ማስተማር። ሐዋርያው ጳውሎስ “[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል” በማለት ጽፏል። (ሮም 1:20) ወላጆች ልጆቻቸው አምላክ እውን ሆኖ እንዲታያቸው ለመርዳት ብዙ ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ፤ ከእነዚህ መካከል ልጆች የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ልብ ብለው እንዲመለከቱ ማድረግና በእነዚህ ፍጥረታት ላይ የተንጸባረቁትን የአምላክ ባሕርያት እንዲያስተውሉ መርዳት ይገኙበታል።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስተምር ይህን ዘዴ ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፦ “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም። ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” (ማቴዎስ 6:26) ኢየሱስ እዚህ ላይ የይሖዋን ፍቅርና ርኅራኄ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይሁን እንጂ ከዚህም ያለፈ ነገር አድርጓል። አምላክ ለልጆቹ እነዚህን ባሕርያት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ደቀ መዛሙርቱን ረድቷቸዋል።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ጉንዳኖች ከአምላክ ያገኙትን ተፈጥሯዊ ጥበብ በመጥቀስ ከእነዚህ ፍጥረታት ጠቃሚ ትምህርት እንደምናገኝ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንተ ታካች፤ ወደ ጕንዳን ሂድ፤ ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤ አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤ ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤ በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል።” (ምሳሌ 6:6-8) ሰለሞን የተጠቀመበት ይህ  የማስተማሪያ ዘዴ ጠቃሚ ግቦችን ማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ አምላክ የሰጠንን ጉልበት መጠቀም ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለማስገንዘብ የሚያስችል እንዴት ያለ ውጤታማ መንገድ ነው!

ወላጆች የሚከተለውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የኢየሱስንና የሰለሞንን ውጤታማ የማስተማር ዘዴ መከተል ይችላሉ፦ (1) ልጆቻቸው የሚወዷቸው ዕጽዋትና እንስሳት የትኞቹ እንደሆኑ መጠየቅ። (2) ስለ እነዚህ ዕጽዋትና እንስሳት ይበልጥ ለማወቅ መጣር። (3) በእነዚህ ፍጥረታት ተጠቅሞ ስለ አምላክ ማስተማር።

2. ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት መያዝ። ኢየሱስ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ለሌሎች የሚያካፍለው እጅግ ጠቃሚ ነገር ነበረው። ሆኖም ብዙ ነገር ከመናገር ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። የሚያስተምራቸው ሰዎች ያላቸውን አስተሳሰብና ስሜት ለማወቅ ጉጉት ነበረው። (ማቴዎስ 17:24, 25፤ ማርቆስ 8:27-29) በተመሳሳይም ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተምሯቸው ብዙ ጠቃሚ ነገር እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው። ይሁንና ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ልጆቻቸው የሚሰማቸውን ነገር በነፃነት እንዲናገሩ ማበረታታት ያስፈልጋቸዋል።

ይሁንና ልጆች መጥፎ ዝንባሌ ቢያሳዩ ወይም የሚሰጣቸውን ጠቃሚ ትምህርት ለመቀበል ፈጣን ባይሆኑስ? ኢየሱስ ሐዋርያቱን የያዘበትን መንገድ ተመልከቱ። ሐዋርያቱ አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው ኃይለኛ ክርክር ይነሳ የነበረ ከመሆኑም በላይ የትሕትናን ባሕርይ ማንጸባረቅ ያሉትን ጥቅሞች በመማር ረገድ ፈጣኖች አልነበሩም። ሆኖም ኢየሱስ በትዕግሥት ይዟቸዋል፤ እንዲሁም የትሕትናን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ነግሯቸዋል። (ማርቆስ 9:33, 34፤ ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24, 25) ወላጆች የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ ለልጆቻቸው በትዕግሥት እርማት ይሰጣሉ፤ አስፈላጊ ከሆነም ልጆቹ የትምህርቱን ጠቀሜታ በደንብ እስኪረዱ ድረስ ያንኑ ትምህርት ደጋግመው ያስተምራሉ። *

3. ምሳሌ በመሆን ማስተማር። ወላጆች ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ምክር ልብ ማለታቸው አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ “ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?” በማለት ጽፎላቸዋል።​—ሮም 2:21

ይህ ምክር በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ልጆች ይበልጥ ትኩረት የሚሰጡት ወላጆቻቸው ለሚናገሩት ሳይሆን ለሚያደርጉት ነገር ነው። እንዲያውም ወላጆች የሚናገሩትን ነገር በተግባር የሚያውሉ ከሆነ የሚነገራቸውን የሚሰሙ ልጆች የማፍራት አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ይሆናል።

4. ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማስተማር። ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በሚስዮናዊነት አገልግሎት የተካፈለው ጢሞቴዎስ በአካባቢው ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ ጥሩ ስም ነበረው። (የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2) ለዚህ አንዱ ምክንያት ጢሞቴዎስ ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን’ ተምሮ ስለነበረ ነው። የጢሞቴዎስ እናትና አያት ቅዱሳን መጻሕፍትን አብረውት ማንበብ ብቻ ሳይሆን እነዚያ መጻሕፍት የያዟቸውን እውነቶች ማስተዋል እንዲችል ጭምር ረድተውት ነበር።​—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15

እርዳታ ከየት ማግኘት ትችላላችሁ?

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት ለልጆች በማስተማር ረገድ ወላጆችን ለማገዝ ተብለው የሚዘጋጁ በርካታ ጽሑፎችን እያተሙ ያወጣሉ። አንዳንዶቹ የተጻፉት ትንንሽ ልጆችን ታሳቢ በማድረግ ነው። ሌሎቹ ደግሞ በወላጆችና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ልጆቻቸው መካከል ቀጣይነት ያለው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። *

እርግጥ ነው፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ አምላክ ለማስተማር ከመነሳታቸው በፊት እነሱ ራሳቸው ልጆች ለሚያነሷቸው አንዳንድ ከባድ ጥያቄዎች መልሶቹን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣላችሁ፦ አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ሙታን የት ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች የእነዚህንም ሆነ የሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ማወቅ እንድትችሉ ሊረዷችሁ ፈቃደኞች ናቸው፤ ይህ ደግሞ እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ ወደ አምላክ መቅረብ እንድትችሉ ይረዳችኋል።​—ያዕቆብ 4:8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በ⁠ዘዳግም 6:7 ላይ “አስጠናቸው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አንድን ነጥብ፣ ደግሞ ደጋግሞ መግለጽን ያመለክታል።

^ አን.15 ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸውን ዋና ዋና ትምህርቶች ጥሩ አድርጎ የሚገልጸውን ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለውን መጽሐፍ ወይም በጣም ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ቀለል ባለ መንገድ የሚያብራራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተሰኘውን መጽሐፍ በመጠቀም ወላጆች ትንንሽ ልጆችን ማስተማር ይችላሉ። ለወጣቶች ደግሞ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 እና 2 የተሰኙትን መጻሕፍት መጠቀም ይችላሉ።