በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላኩ አጽናንቶታል

አምላኩ አጽናንቶታል

 በእምነታቸው ምሰሏቸው

አምላኩ አጽናንቶታል

ሰማዩ እየጠቋቋረ ቢሆንም ኤልያስ በዝናብ ውስጥ እየሮጠ ነው። ኢይዝራኤል ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ ይቀረዋል፤ በዚያ ላይ በዕድሜ የገፋ ሰው ነው። ያም ሆኖ ‘የእግዚአብሔር ኃይል’ በእሱ ላይ ስለወረደ ምንም ዓይነት የድካም ስሜት ሳይታይበት መሮጡን ተያይዞታል። በዚህ ወቅት ኤልያስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አግኝቶት የማያውቅ ልዩ ኃይል እንዳገኘ ሳይሰማው እንደማይቀር ጥርጥር የለውም። ጭራሹንም አክዓብ የተቀመጠበትን የቤተ መንግሥቱን ሠረገላ የሚጎትቱትን ፈረሶች ቀድሟቸው ሄደ!​—1 ነገሥት 18:46

አሁን ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን የትና የት ጥሎት ስለሄደ ከፊቱ ያለውን ረጅም መንገድ ብቻውን ሆኖ በመገስገስ ላይ ነው። ኤልያስ በዕለቱ የተፈጸመውን ፈጽሞ የማይረሳ ክንውን እያሰበና የሚወርድበትን ዝናብ ከፊቱ ላይ እየጠረገ ሲሮጥ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህ ቀን የኤልያስ አምላክ የሆነው ይሖዋ አንጸባራቂ ድል ያገኘበትና እውነተኛው አምልኮ ከፍ ከፍ ያለበት ዕለት ነው። ኤልያስ በጣም ርቆ በመሄዱና አካባቢው በጭጋግ በመሸፈኑ የተነሳ የቀርሜሎስ ተራራ ከዓይኑ ተሰውሯል፤ ይሖዋ በኤልያስ ተጠቅሞ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የበኣልን አምልኮ ድባቅ የመታው በዚህ ቦታ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ የበኣል ነቢያት በክፋት የተሞሉ አታላዮች መሆናቸው የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ የሚገባቸውን የሞት ቅጣት ተቀብለዋል። ኤልያስም ለሦስት ዓመት ተኩል ምድሪቱን ያጠቃው ድርቅ እንዲያከትም ወደ ይሖዋ ጸልዮ ነበር። ዝናቡ መጣል የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው! *​—1 ነገሥት 18:18-45

ኤልያስ ወደ ኢይዝራኤል ለመድረስ የሚፈጀውን 30 ኪሎ ሜትር በዝናብ እየተደበደበ በሚሮጥበት ጊዜ ‘የበኣል ነቢያት በመደምሰሳቸው አሁን እውነተኛ ለውጥ ይመጣል’ ብሎ ሳያስብ አይቀርም። መቼም አክዓብ መለወጥ አለበት! ቀደም ሲል የተፈጸሙትን ነገሮች መመልከቱ የበኣል አምልኮን እርግፍ አድርጎ እንዲተው፣ የንግሥት ኤልዛቤልን ድርጊት ለማስቆም እርምጃ እንዲወስድና የይሖዋን አገልጋዮች ማሳደዱን እንዲያቆም ሊያነሳሳው ይገባል።

ማናችንም ብንሆን ነገሮች እኛ በምንፈልገው መንገድ እየሄዱ እንደሆነ ሲሰማን ተስፋችን እንደሚለመልም የታወቀ ነው። ሁኔታዎች በመስተካከላቸው የተነሳ ሕይወታችን እየተሻሻለ እንደሆነ እንዲያውም ራስ ምታት ከሆኑብን ችግሮቻችን እንደተገላገልን ይሰማን ይሆናል። ኤልያስ እንዲህ አስቦ ከሆነ ምንም አያስደንቅም፤ ምክንያቱም እሱም ቢሆን “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው” ነው። (ያዕቆብ 5:17) ይሁን እንጂ፣ ኤልያስ እንዳሰበው ከችግሮቹ አልተገላገለም። እንዲያውም ከዘገባው መረዳት እንደምንችለው ኤልያስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በከፍተኛ ፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት በመዋጡ ሞትን ተመኝቷል። ለመሆኑ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ምን አጋጥሞት ነው? ይሖዋ ይህ ነቢይ እምነቱን እንዲያጠናክርና ድፍረቱን መልሶ እንዲያገኝ የረዳውስ እንዴት ነው? እስቲ እነዚህን ጉዳዮች በዝርዝር እንመልከት።

ያልጠበቀው ሁኔታ ተከሰተ

አክዓብ ኢይዝራኤል ወዳለው ቤተ መንግሥቱ ሲደርስ እንደተለወጠና መንፈሳዊ ሰው ለመሆን እንደፈለገ የሚያሳይ ነገር ያደርግ ይሆን? ዘገባው “አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት” ይላል። (1 ነገሥት 19:1) አክዓብ በዕለቱ ስለተከናወኑት ነገሮች ሲናገር የኤልያስ አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንዳልጠቀሰ ልብ በል። አክዓብ በዕለቱ የተከናወኑትን ተአምራዊ ነገሮች ይሖዋ ሳይሆን ‘ኤልያስ እንዳደረጋቸው’ መናገሩ ሥጋዊ አስተሳሰብ እንደነበረው ያሳያል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አክዓብ ለይሖዋ አምላክ  ክብር መስጠት እንዳለበት ካጋጠመው ሁኔታ ሊማር አልቻለም። ይሁንና የበቀል መንፈስ የተጠናወታት ኤልዛቤል የአክዓብን ወሬ ስትሰማ ምን ታደርግ ይሆን?

ኤልዛቤል ኤልያስ ያደረገውን ስትሰማ ደምዋ ፈላ! በንዴት ፊቷ ተለዋውጦ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” የሚል መልእክት ወደ ኤልያስ ላከችበት። (1 ነገሥት 19:2) ይህ እሱን ለመግደል ቆርጣ መነሳቷን የሚያሳይ ማስፈራሪያ ነው። በሌላ አባባል ‘የበኣል ነቢያቴን እንደገደልክ እኔም በነገው ዕለት አንተን ሳልገድል ብቀር ሞቻለሁ’ ብላ መዛቷ ነበር። ኤልያስ ዶፍ በሚወርድበት በዚያ ሌሊት ከእንቅልፉ ሲቀሰቀስ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ የተቀሰቀሰው ደህና ነገር ሊሰማ ሳይሆን የንግሥቲቱ መልእክተኞች ያመጡትን ሽብር የሚለቅ መልእክት ለመስማት ነው። ታዲያ ኤልያስ ይህ መልእክት ሲደርሰው ምን ተሰማው?

በተስፋ መቁረጥና በፍርሃት ስሜት ተዋጠ

ኤልያስ ከበኣል አምልኮ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ እንዳበቃ በማሰብ ተደስቶ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ዛቻውን ሲሰማ ተስፋው በሙሉ በዚያች ቅጽበት እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ኤልዛቤል ይሖዋ ያደረገውን ነገር ብትሰማም ምንም ለውጥ አላደረገችም። አምላክን በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ በጣም ብዙ ሰዎችን ከዚህ ቀደም አስገድላለች፤ አሁን ደግሞ ኤልያስ ተራው እንደደረሰ ተሰምቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁኔታው ሲገልጽ ‘ኤልያስ ፈርቶ ነበር’ ይላል። ምናልባት ኤልያስ ኤልዛቤል እንዴት ባለ አሰቃቂ ሁኔታ ልትገድለው እንዳሰበች በዓይነ ሕሊናው ታይቶት ይሆን? እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆይቶ ከሆነ መፍራቱ ምንም አያስገርምም። ወጣም ወረደ ኤልያስ “ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ።”​—1 ነገሥት 18:4፤ 19:3

የእምነት ሰው ሆኖ በፍርሃት የተሸነፈ ኤልያስ ብቻ አይደለም። ከብዙ ዘመናት በኋላ የኖረው ሐዋርያው ጴጥሮስም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንደ እሱ በውኃ ላይ እንዲራመድ ሲጋብዘው ሐዋርያው ጥቂት እንደተራመደ ‘ማዕበሉን አየ።’ ከዚያም ፍርሃት ስላደረበት መስጠም ጀመረ። (ማቴዎስ 14:30) እኛም ከጴጥሮስና ከኤልያስ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። ፍርሃት እንዳያድርብን ከፈለግን አእምሯችን ከፊታችን በተጋረጠው አደጋ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የለብንም። ምንጊዜም ትኩረታችን ማረፍ ያለበት የተስፋችንና የብርታታችን ምንጭ በሆነው አምላክ ላይ ነው።

“በቅቶኛል”

ኤልያስ በጣም ስለፈራ በደቡብ ምዕራብ በኩል 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘውና በይሁዳ ደቡባዊ ድንበር አቅራቢያ ወዳለችው የቤርሳቤህ ከተማ ሸሸ። ቤርሳቤህ እንደደረሰም አገልጋዩን በዚያ ትቶት ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ዘገባው ኤልያስ “የአንድ ቀን መንገድ” እንደተጓዘ ስለሚናገር ጉዞ የጀመረው ገና ጀምበር እንደወጣች መሆኑን መገመት እንችላለን፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኤልያስ በዚህ ወቅት ስንቅም ሆነ ለመንገድ የሚሆን ምንም ነገር አልያዘም። በሐዘንና በፍርሃት የተዋጠው ይህ ነቢይ ለጉዞ የማይመቸውንና ሰው የረገጠው የማይመስለውን  አካባቢ እያቆራረጠ በጠራራ ፀሐይ መጓዝ ጀመረ። አናት የሚበሳው የፀሐዩ ትኩሳት ቀስ በቀስ እየበረደ ሲሄድና ጀንበሯም እየጠለቀች ስትመጣ የኤልያስ ጉልበትም እየተሟጠጠ መጣ። እናም ዝልፍልፍ ብሎ በአቅራቢያው ባገኘው አንድ የክትክታ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ በወቅቱ በዚህ ጠፍ ምድረ ሊያገኝ የቻለው መጠለያ ይህን ዛፍ ነበር።​—1 ነገሥት 19:4

ኤልያስ በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጦ ወደ ይሖዋ ጸለየ። “እኔ ከአባቶቼ አልበልጥም” በማለት እንዲሞት ለመነ። በመቃብር ውስጥ ያሉት የቀድሞ አባቶቹ አፈር እንደሆኑና ለማንም ምንም የሚጠቅም ነገር ማከናወን እንደማይችሉ አሳምሮ ያውቃል። (መክብብ 9:10) በመሆኑም ኤልያስ ከእነሱ እንደማይሻል ተሰምቶታል። “በቅቶኛል” በማለት በምሬት የተናገረው ለዚህ ነው። ‘የእኔ በሕይወት መኖር ምን ጥቅም አለው?’ የሚል ስሜት ሳያድርበት አልቀረም።

አንድ የአምላክ አገልጋይ ይህን ያህል ተስፋ መቁረጡ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። በሐዘን በመደቆሳቸው የተነሳ ሞትን የተመኙ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝገበው የሚገኙ ሲሆን ከእነዚም መካከል ርብቃ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴና ኢዮብ ይገኙበታል።​—ዘፍጥረት 27:46፤ 37:35፤ ዘኍልቍ 11:13-15፤ ኢዮብ 14:13

የምንኖረው “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ” የሆነ ዘመን ውስጥ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ሌላው ቀርቶ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ጭምር የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንተም እንዲህ ያለ አስጨናቂ ሁኔታ ካጋጠመህ የኤልያስን ምሳሌ በመከተል የውስጥህን ስሜት አውጥተህ ለአምላክ ንገረው። ደግሞም ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” መሆኑን አስታውስ። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ታዲያ ይሖዋ ኤልያስን ያጽናናው ይሆን?

ይሖዋ ነቢዩን አበረታው

ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ በጣም የሚወደው ይህ ነቢይ ምድረ በዳ ውስጥ ባለች አንዲት ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሞቱን ሲመኝ ሲመለከተው ምን የተሰማው ይመስልሃል? ቀጥሎ የሆነው ነገር የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ኤልያስ ድብን ያለ እንቅልፍ ሲወስደው ይሖዋ አንድ መልአክ ላከ። መልአኩ ትኩስ ዳቦና የሚጠጣ ውኃ ካቀረበለት በኋላ ቀስ ብሎ ኤልያስን ነካ በማድረግ ቀሰቀሰውና “ተነሥና ብላ” አለው። ኤልያስም እንደተባለው አደረገ። ኤልያስ ከበላ በኋላ መልአኩን አመስግኖታል ብለህ ታስባለህ? ዘገባው የሚናገረው ነቢዩ ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ እንደተኛ ብቻ ነው። ምናልባት የደረሰበት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከባድ መሆኑ የመናገር ፍላጎቱን ዘግቶት ይሆን? ያም ሆነ ይህ መልአኩ ኤልያስን በድጋሚ ቀሰቀሰው፤ ምናልባት በዚህ ወቅት ጎሕ ሳይቀድ አይቀርም። ለሁለተኛ ጊዜ “ተነሥና ብላ” በማለት ኤልያስን አሳሰበው፤ በተጨማሪም መልአኩ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ” የሚል ሐሳብ መናገሩ ኤልያስን አስገርሞት መሆን አለበት።​—1 ነገሥት 19:5-7

መልአኩ፣ አምላክ ማስተዋልን ስለሰጠው ኤልያስ ወዴት እንደሚሄድ አውቆ ነበር። ከዚህም ባሻገር ኤልያስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ረጅም መንገድ በራሱ ኃይል ብቻ ሊወጣው እንደማይችል መልአኩ ተረድቶ ነበር። ስለ ግባችንንና ስላሉብን የአቅም ገደቦች ከእኛ በተሻለ የሚያውቅን አምላክ ማገልገል እንዴት የሚያጽናና ነው! (መዝሙር 103:13, 14) ታዲያ ኤልያስ የተመገበው ምግብ የጠቀመው እንዴት ነው?

ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ።” (1 ነገሥት 19:8) ኤልያስ ከእሱ ስድስት መቶ ዓመታት በፊት ይኖር እንደነበረው እንደ ሙሴና ከእሱ አንድ ሺህ ዓመታት በኋላ እንደኖረው እንደ ኢየሱስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል። (ዘፀአት 34:28፤ ሉቃስ 4:1, 2) ኤልያስ መልአኩ ያቀረበለትን ምግብ መመገቡ ችግሮቹን በሙሉ ባያስወግድለትም ተአምራዊ በሆነ መንገድ ብርታት ሰጥቶታል። በዕድሜ የገፋው ይህ ነቢይ መግቢያ መውጫው በማይታወቅ በዚያ ምድረ በዳ ውስጥ ከወር በላይ ሲኳትን ይታይህ!

በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አገልጋዮቹን በሥጋዊ ምግብ አማካኝነት  ተአምራዊ ኃይል እንዲያገኙ ባያደርግም ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ መንገድ ያበረታቸዋል። ለአገልጋዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል። (ማቴዎስ 4:4) በአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመርኩዘው በጥንቃቄ በሚዘጋጁ ጽሑፎች አማካኝነት ስለ አምላክ ስንማር በመንፈሳዊ እንበረታለን። እንዲህ የመሰለ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ችግሮቻችንን በሙሉ ባያስወግድልንም በዚህ መንገድ ካልሆነ በስተቀር ልንወጣቸው የማንችላቸውን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። በተጨማሪም ወደ “ዘላለም ሕይወት” ይመራናል።​—ዮሐንስ 17:3

ኤልያስ ወደ 320 የሚጠጋ ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ኮሬብ ተራራ ደረሰ፤ ይሖዋ አምላክ በሚነድ ቁጥቋጦ ውስጥ በአንድ መልአክ አማካኝነት ለሙሴ የተገለጠለትና በኋላም ለእስራኤላውያን ሕጉን የሰጣቸው በዚህ ቦታ ነበር። ኤልያስ አንድ ዋሻ አግኝቶ በዚያ ውስጥ ተጠለለ።

ይሖዋ ነቢዩን ያጽናናበትና ያበረታበት መንገድ

ኤልያስ በኮሬብ ሳለ የይሖዋ “ቃል” (ምናልባትም መንፈሳዊ ፍጡር በሆነ አንድ መልእክተኛ አማካኝነት ሊሆን ይችላል) “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል አጭር ጥያቄ አቀረበለት። ጥያቄው ለስለስ ባለ መንገድ የቀረበ ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም ኤልያስ የልቡን አውጥቶ ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ እንደተከፈተለት እንዲሰማው አድርጓል። ስለዚህ ኤልያስ በውስጡ የሚሰማውን ስሜት እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ።” (1 ነገሥት 19:9, 10) ከዚህ አነጋገሩ መረዳት እንደሚቻለው ኤልያስን ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረጉት ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ።

አንደኛ፣ ኤልያስ ልፋቱ መና እንደቀረ ተሰምቶታል። ለዓመታት የአምላክን ቅዱስ ስምና አምልኮ ከሁሉ በላይ በማስቀደም ይሖዋን የማገልገል ከፍተኛ ‘ቅንዓት’ እንዳለው ቢያሳይም ሁኔታዎቹ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ እንደሄዱ ተሰምቶታል። በአንድ በኩል ሕዝቡ እምነተ የለሽና ዓመፀኛ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሐሰት አምልኮ በጣም እየተስፋፋ ነበር። ሁለተኛ፣ ኤልያስ ብቻውን እንደቀረ ተሰምቶታል። በአገሪቱ ውስጥ ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች የተረፈው እሱ ብቻ እንደሆነ ስላሰበ “የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ” በማለት ተናግሯል። ሦስተኛ፣ ኤልያስ ፍርሃት አድሮበታል። እንደ እሱ ይሖዋን ያገለግሉ ከነበሩት ነቢያት ውስጥ አብዛኞቹ ስለተገደሉ ቀጥሎ የእሱ ተራ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ይህን ስሜቱን አውጥቶ መናገር ለኤልያስ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ኩራትም ሆነ ኀፍረት ስሜቱን አውጥቶ ከመናገር ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። የልቡን አውጥቶ ለአምላክ በጸሎት በመናገር ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ጥሩ ምሳሌ ትቷል።​—መዝሙር 62:8

ይሖዋ የኤልያስን ፍርሃትና ጭንቀት ለማስወገድ ምን አደረገ? መልአኩ፣ ኤልያስ በዋሻው መግቢያ ላይ እንዲቆም ነገረው። ኤልያስ ቀጥሎ ምን እንደሚከናወን ባያውቅም እንደታዘዘው አደረገ። በድንገት ኃይለኛ ነፋስ ነፈሰ! በዚህ ጊዜ ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ተሰምቶ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ነፋሱ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ተራሮቹና ዐለቶቹ ተሰነጣጥቀዋል። ኤልያስ ነፋሱ ፀጉራም ካባውን ከላዩ ላይ ገፍፎ እንዳይወስድበት ሙጭጭ አድርጎ እንደያዘ ዓይኑን ለመከለል ሲሞክር በሐሳብህ ይታይህ። ከዚያም የመሬት መንቀጥቀጥ  አካባቢውን አናወጠው፤ በዚህ ወቅት ኤልያስ ሚዛኑን ለመጠበቅ ምን ያህል ትግል እንደሚያደርግ ለማሰብ ሞክር! ከዚያም በመቀጠል ኃይለኛ እሳት በመነሳቱ ኤልያስ ወደ ዋሻው ዘሎ ገባ፤ በዚህም የተነሳ በወላፈኑ ከመበላት ለጥቂት ዳነ።​—1 ነገሥት 19:11, 12

ሦስቱም ሁኔታዎች በተከሰቱበት ወቅት ይሖዋ በእነዚያ አስደናቂ የተፈጥሮ ኃይል መግለጫዎች ውስጥ እንዳልነበረ ዘገባው ይነግረናል። አምላኪዎቹ “ደመና ጋላቢ” ወይም ዝናብ አምጪ እንደሆነ በማሰብ ክብር እንደሚሰጡ እንደ በኣል ይሖዋ በተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ የሚገኝ ምናብ የወለደው አምላክ እንዳልሆነ ኤልያስ ያውቅ ነበር። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙት እጅግ ታላቅ የሆኑት የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ ምንጭ ከመሆኑም በላይ እሱ ከሠራው ከማንኛውም ነገር የላቀ ኃይል አለው። ሰማያትም እንኳን እሱን ሊይዙት አይችሉም! (1 ነገሥት 8:27) ታዲያ ኤልያስ ይህን ሁሉ መመልከቱ የጠቀመው እንዴት ነው? ኤልያስ ምን ያህል ፈርቶ እንደነበር አስታውስ። ይሖዋ በፈለገው ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል ይህ ነው የማይባል ኃይል እንዳለው ኤልያስ ተመልክቷል፤ ታዲያ ይህን የመሰለ አምላክ ከጎኑ እያለለት አክዓብንም ሆነ ኤልዛቤልን የሚፈራበት ምንም ምክንያት አለ?​—መዝሙር 118:6

እሳቱ እንዳለፈ ጸጥታ ሰፈነ፤ ከዚያም ኤልያስ “ለስለስ ያለ ድምፅ” ሰማ። * “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚለው ለስለስ ባለ ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበለት ጥያቄ ኤልያስ ስሜቱን በድጋሚ እንዲገልጽ የሚጋብዝ ነበር፤ እሱም ያስጨነቀውን ነገር ለሁለተኛ ጊዜ ግልጥልጥ አድርጎ ተናገረ። እንዲህ ማድረጉ ይበልጥ ቀለል እንዲለው ሳያደርገው አልቀረም። ኤልያስ ቀጥሎ የሰማው ‘ለስለስ ባለ ድምፅ’ የተነገረው ሐሳብ ግን ይበልጥ አጽናንቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሖዋ፣ ኤልያስ እሱ እንዳሰበው ዋጋ ቢስ አለመሆኑን እንዲገነዘብ ረዳው። ይሖዋ ይህን ያደረገው እንዴት? አምላክ የበኣል አምልኮን ከእስራኤል ምድር ለማስወገድ ከሚደረገው ጦርነት ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳሰበ ገለጸለት። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአምላክ ዓላማ አንዳች የሚገታው ነገር ሳይኖር ወደፊት በመገስገስ ላይ ስለሆነ የኤልያስ ልፋት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ለኤልያስ አንዳንድ ዝርዝር መመሪያዎችን በመስጠት እንደገና ወደ ሥራው እንዲመለስ ስላደረገው ይህ ነቢይ አሁንም ቢሆን በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ድርሻ ነበረው።​—1 ነገሥት 19:12-17

ኤልያስ የተሰማው የብቸኝነት ስሜትስ መፍትሔ አግኝቶ ይሆን? ይሖዋ ይህን ችግር ለመፍታት ሁለት ነገሮችን አድርጓል። አንደኛ፣ ከጊዜ በኋላ እሱን የሚተካውን ኤልሳዕን ነቢይ አድርጎ እንዲቀባ ለኤልያስ ነገረው። ከኤልያስ በዕድሜ የሚያንሰው ይህ ሰው የኤልያስ የሥራ ባልደረባና ረዳት በመሆን ለብዙ ዓመታት ሊያገለግል ነው። በእርግጥም ይህ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ ነው! ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሚከተለውን በጣም አስደሳች ዜና አበሰረው፦ “እኔም ጕልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺህ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ።” (1 ነገሥት 19:18) ለካስ ኤልያስ ብቻውን አልነበረም። በኣልን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ታማኝ ሰዎች እንዳሉ ሲሰማ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት። ሕዝቡ ሁሉ ማለት ይቻላል በይሖዋ ላይ ባመፀበት በዚህ ወቅትም ኤልያስ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን መቀጠሉ እነዚህ ሰዎች የእሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ያነሳሳቸዋል። ኤልያስ በአምላክ መልእክተኛ አማካኝነት ‘ለስለስ ባለ ድምፅ’ የተነገረውን ይህን የይሖዋ ቃል መስማቱ ልቡ በጥልቅ እንዲነካ ሳያደርገው አልቀረም።

እኛም እንደ ኤልያስ ከፍጥረት ሥራዎቹ በግልጽ የሚታዩትን ታላላቅ የተፈጥሮ ኃይሎች ስንመለከት ልንደመም እንችላለን፤ ደግሞም መደመማችን ተገቢ ነው። ፍጥረት የፈጣሪን ኃይል በግልጽ ያንጸባርቃል። (ሮም 1:20) ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ገደብ የሌለው ኃይሉን በመጠቀም ታማኝ አገልጋዮቹን መርዳት ያስደስተዋል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሁን እንጂ አምላክ እኛን ለማናገር በዋነኝነት የሚጠቀመው ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ነው። (ኢሳይያስ 30:21) በሌላ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ኤልያስ እንደሰማው ዓይነት “ለስለስ ያለ ድምፅ” ነው፤ ይሖዋ ዛሬም በዚህ መንገድ ተጠቅሞ ይመራናል፣ እርማት ይሰጠናል፣ ያበረታታናል እንዲሁም እንደሚወደን ያረጋግጥልናል።

ታዲያ ኤልያስ ይሖዋ በኮሬብ ተራራ ላይ የሰጠውን ማጽናኛ ተቀብሏል? ምን ጥያቄ አለው! ወዲያውኑ ወደ ሥራው በመመለስ እንደ ድሮው የሐሰት አምልኮን ክፋት በድፍረትና በታማኝነት ማጋለጥ ጀመረ። እኛም በተመሳሳይ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ማለትም ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት የምናገኘውን መጽናኛ’ ከልብ የምንቀበል ከሆነ ኤልያስን በእምነቱ ልንመስለው እንችላለን።​—ሮም 15:4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በጥር 1 እና በሚያዝያ 1, 2008 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” በሚለው ዓምድ ሥር የወጡትን “ለንጹሑ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል” እና “በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.29 የዚህ “ለስለስ ያለ ድምፅ” ምንጭ ይሖዋ በ⁠1 ነገሥት 19:9 ላይ የሚገኘውን ‘ቃሉን’ ለማስተላለፍ የተጠቀመበት መንፈሳዊ አካል ሳይሆን አይቀርም። ይህ መንፈሳዊ አካል የአምላክ ወኪል በመሆኑ በቁጥር 15 ላይ የተጠቀሰው “እግዚአብሔር” ተብሎ ነው። ይህም ይሖዋ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ለመምራት የተጠቀመበትንና “ስሜ በርሱ ላይ ነው” በማለት አምላክ የተናገረለትን መንፈሳዊ አካል ያስታውሰን ይሆናል። (ዘፀአት 23:21) እውነት ነው፣ ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ያም ሆኖ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ማለትም ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ልዩ ቃል አቀባይ ሆኖ እንዳገለገለ ልብ ማለት ይገባል።​—ዮሐንስ 1:1

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ኤልያስን፣ በክፉውም ሆነ በደጉ ጊዜ በእጅጉ ባርኮታል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ በተስፋ መቁረጥ ስሜት በተዋጠበት ጊዜ የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ኤልያስን ለማጽናናትና ለማበረታታት እጅግ ታላቅ የሆነውን ኃይሉን ተጠቅሟል