በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ”

“አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ”

 ወደ አምላክ ቅረብ

“አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ”

አልረባም በሚል ስሜት የምትሠቃይ አንዲት ታማኝ ክርስቲያን “በደንብ የሚያውቀኝ ይሖዋ በፍጹም ሊወደኝ ወይም ሊቀበለኝ እንደማይችል ይሰማኛል” በማለት ጽፋለች። አንተስ እንዲህ ባለ አፍራሽ ስሜት እየተሠቃየህ ነው? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይቅርና የእሱን ትኩረት ማግኘት እንኳ እንደማይገባህ ይሰማሃል? ከሆነ በ⁠ነህምያ 13:31 (የ1954 ትርጉም) ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐሳብ ሊያበረታታህ ይችላል።

በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የአይሁዳውያን ገዥ የነበረው ነህምያ አምላክን ለማስደሰት የተቻለውን ሁሉ አድርጎ ነበር። የጠላት ተቃውሞ ቢኖርበትም የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና የመገንባቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት መርቷል። የአምላክን ሕግ ያስከብርና የተጨቆኑ ሰዎችን ይረዳ የነበረ ከመሆኑም በላይ የእምነት ባልንጀሮቹን እምነት ለመገንባት ጥረት አድርጓል። አምላክ ይህ ታማኝ ሰው ያደረገውን መልካም ተግባር ትኩረት ሰጥቶ ይመለከት ነበር? ነህምያ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር? በነህምያ ስም የተጻፈውን መጽሐፍ የመደምደሚያ ሐሳብ በመመርመር የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን።

ነህምያ “አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ” በማለት ጸልዮአል። * ነህምያ እንዲህ ብሎ የተናገረው ያደረጋቸው መልካም ነገሮች በአምላክ ዘንድ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንደሚቀሩ አሊያም አምላክ እሱን እንደሚረሳው ፍርሃት ስለተሰማው ነው? በፍጹም። ነህምያ ከእሱ በፊት የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹንም ሆነ የሚያደርጉትን መልካም ተግባር ለመመልከት ያለውን ልባዊ ፍላጎት በማስመልከት የተናገሩትን ነገር እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፀአት 32:32, 33፤ መዝሙር 56:8) ታዲያ ነህምያ አምላክን እየጠየቀ የነበረው ምንድን ነው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ማሰብ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አንድን ሰው በመልካም አስታውሶ ለዚያ ግለሰብ አንድ ነገር ማድረግ” የሚል መልእክት እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። ነህምያ ጸሎት ባለው ኃይል ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር አምላክ በፍቅር እንዲያስበውና እንዲባርከው ጠይቋል።—ነህምያ 2:4

ነህምያ፣ ይሖዋ እንዲያስበው ያቀረበው ጸሎት ምላሽ አግኝቷል? በአንድ በኩል ሲታይ ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ነህምያን አስታውሶታል ሊባል ይችላል። ይሖዋ የነህምያ ጸሎት ቋሚ በሆኑት መዛግብቱ ውስጥ መካተት እንደሚችል በመቁጠር በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንዲሆን ማድረጉ ነህምያን በፍቅር እንደሚያስታውሰው እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። ሆኖም ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው ይሖዋ የነህምያን ልባዊ ጸሎት ለመመለስ ከዚህ የበለጠ ነገር ያደርጋል።—መዝሙር 65:2

አምላክ፣ ነህምያ ንጹሑን አምልኮ ለማቋቋም ሲል ላደረጋቸው መልካም ነገሮች ገና ወሮታውን ይከፍለዋል። (ዕብራውያን 11:6) ይሖዋ ተስፋ በሰጠውና ወደፊት በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ነህምያን ከሞት በማስነሳት ይባርከዋል። * (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) ነህምያ ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ስለሚያገኝ ይሖዋ በእርግጥም በመልካም እንዳሰበው መመልከት ይችላል።

የነህምያ ጸሎት “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቃንን ትባርካቸዋለህ፤ በሞገስህም እንደ ጋሻ ትከልላቸዋለህ” በማለት ንጉሥ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 5:12) አዎን፣ አምላክ እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። እሱን ለማገልገል የተቻለህን ጥረት እስካደረግህ ድረስ በፍቅር እንደሚያስብህና አትረፍርፎ እንደሚባርክህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

በየካቲት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከ⁠ነህምያ 1 እስከ 13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዚህ መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው ከሚገኙትና ነህምያ አምላክ በመልካም እንዲያስበው በሌላ አባባል በታማኝነት ላከናወናቸው ሥራዎች ወሮታ እንዲከፍለው በጸለየባቸው ጊዜያት ከተጠቀመባቸው አራት ተመሳሳይ አገላለጾች ውስጥ ይህ የመጨረሻው ነው።—ነህምያ 5:19፤ 13:14, 22, 31

^ አን.7 አምላክ በምድር ላይ ላሉ ታማኝ ሰዎች ያለውን ዓላማ በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 እና 7⁠ን ተመልከት።