በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ተሳዳቢ፣ ጠጪና ዕፅ ትወስድ የነበረች አንዲት የቡና ቤት አስተናጋጅ ሕይወቷን መቀየር የቻለችው እንዴት ነው? ለሃይማኖት ጥላቻ የነበረው አንድ የፖለቲካ ሰው ሃይማኖተኛ የሆነው ለምንድን ነው? በሩሲያ የፖሊስ ኃይል ውስጥ የጨበጣ ውጊያ አሠልጣኝ የነበረ አንድ ግለሰብ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ምን ፈታኝ ሁኔታዎችን መወጣት አስፈልጎት ነበር? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

“ከእናቴ ጋር ያለኝ ግንኙነት ታድሷል።”​—ናታሊ ሃም

የትውልድ ዘመን፦ 1965

የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

የኋላ ታሪክ፦ ዕፅ ትወስድ የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በደቡብ አውስትራሊያ በምትገኘውና ዓሣ በሚመረትባት ሮቤ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። የዚህች ከተማ ነዋሪዎች ጊዜ የሚያሳልፉት በአካባቢያቸው በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ነው። ወላጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሆቴሉ ስለሚያሳልፉ ልጆቻቸው ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ለአልኮል ሱሰኝነት፣ ጸያፍ ለሆነ ንግግርና ሲጋራ ለማጨስ የተጋለጡ ናቸው።

ገና 12 ዓመት ሳይሞላኝ ሲጋራ ማጨስ የጀመርኩ ሲሆን የማልሳደበው የስድብ ዓይነት አልነበረም፤ ከዚህም በላይ ከእናቴ ጋር ብዙ ጊዜ እንጋጭ ነበር። የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ የተለያዩ ሲሆን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ቤት ለቅቄ ወጣሁ። ከዚያም ከልክ በላይ አልኮል መጠጣት፣ ዕፅ መውሰድና ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራት ጀመርኩ። በቀላሉ የምቆጣና ነገር ዓለሙ የዞረብኝ ሰው ሆንኩ። የማርሻል አርት ኮርስና ሴቶች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንዲችሉ የሚሰጣቸውን ሥልጠና ለአምስት ዓመታት ከተከታተልኩ በኋላ ግን ራሴን መጠበቅ እንደምችል ሆኖ ተሰማኝ። ያም ሆኖ ለብቻዬ በምሆንበትና በሐሳብ በምዋጥበት ጊዜ በሐዘን ስለምደቆስ አምላክ እንዲረዳኝ እለምነው ነበር። “ብቻ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂጂ አትበለኝ” ብዬ እጸልይ ነበር።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ራሱን እንደ ሃይማኖተኛ የሚቆጥር ሆኖም የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባል ያልሆነ አንድ ጓደኛዬ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝ። እንደ ሌሎቹ ጓደኞቻችን ሁሉ እሱም ዕፅ ያጨስ ነበር። ይሁን እንጂ ከልቡ በአምላክ እንደሚያምን ይናገር የነበረ ከመሆኑም በላይ መጠመቅ እንዳለብኝ አሳመነኝ። በአካባቢያችን ወዳለ አንድ ሐይቅ ወስዶ አጠመቀኝ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከአምላክ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና እንደመሠረትኩ ተሰማኝ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ አግኝቼ አላውቅም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1988 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በሬን አንኳኩ። አንደኛው “የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” በማለት ጠየቀኝ። ከዚያም መዝሙር 83:18⁠ን (NW) ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አነበበልኝ፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይህም ሰዎች፣ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ከሁሉ በላይ እንደሆንክ  ያውቁ ዘንድ ነው።” በጣም ደነገጥኩ! እነሱ ከሄዱ በኋላ 56 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝና መንፈሳዊ መጻሕፍት ወደሚሸጡበት አንድ መደብር በመኪናዬ በመጓዝ ስሙ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንደሚገኝ አረጋገጥኩ፤ ስሙ በመዝገበ ቃላት ውስጥም እንደሚገኝ ተረዳሁ። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ እርግጠኛ ስሆን ‘ገና ስንት የማላውቀው ነገር አለ ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ።

እናቴ የይሖዋ ምሥክሮች ነገረ ሥራቸው ከሰው የማይገጥም እንደሆነ ትነግረኝ ነበር። ስለ እነሱ ከማውቃት ቁንጽል ነገር በመነሳት በጣም አክራሪና መዝናናት የማያውቁ እንደሆኑ አስብ ነበር። ቤቴን ሲያንኳኩ እንደሌለሁ ለማስመሰል አሰብኩ። ይሁንና የሚመጡበት ጊዜ ሲደርስ ሐሳቤን ቀየርኩ። ሲመጡም ወደ ቤት እንዲገቡ የጋበዝኳቸው ሲሆን ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን ባስጠኑኝ ቁጥር የተማርኩትን ነገር ለወንድ ጓደኛዬ ለክሬግ እነግረው ነበር። አንድ ቀን በጣም ተበሳጨና የምማርበትን መጽሐፍ ከእጄ ላይ ነጥቆ ማንበብ ጀመረ። በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስለ አምላክ እውነቱን እንዳወቀ ተረዳ። ከጊዜ በኋላ እኔና ክሬግ ዕፅ መውሰዳችንንም ሆነ አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣታችንን አቆምን፤ በተጨማሪም የቡና ቤት አስተናጋጅነት ሥራዬን ለቀቅኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት ስንል ተጋባን።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርንበት ጊዜ ከክሬግ ጋር የነበረኝ ግንኙነት በቋፍ ላይ ነበር። አሁን ግን ክሬግ ጥሩ ባል ሆኗል፤ ሁለት ቆንጅዬ ልጆችም አሉን። በተጨማሪም የእምነት አጋሮቻችን የሆኑ ወዳጆችን በማግኘት ተባርከናል።

መጀመሪያ ላይ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደተገናኘሁ ስታውቅ በጣም ተበሳጭታ ነበር። ይሁንና እንዲህ የተሰማት ስለ እነሱ ትክክለኛ ግንዛቤ ስለሌላት ነበር። አሁን ከእናቴ ጋር ያለኝ ግንኙነት ታድሷል። ከዚህም በላይ እንደ ቀድሞው የባዶነት ስሜት አይሰማኝም። እንዲያውም ሕይወቴ ዓላማና ትርጉም ያለው ሆኗል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ፍላጎቴ እየረካ እንዳለ ይሰማኛል።—ማቴዎስ 5:3

“በርካታ አስገራሚ እውነታዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ።”—ኢዛካላ ፓኤኑ

የትውልድ ዘመን፦ 1939

የትውልድ አገር፦ ቱቫሉ

የኋላ ታሪክ፦ የፖለቲካ ሰው

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በአሁኑ ጊዜ በቱቫሉ ግዛት ሥር በሆነችው ኑኩላይላይ በተባለች ውብ የፓስፊክ ደሴት ውስጥ ነው። በፓስፊክ ደሴቶች ውስጥ የሕዝቡን ሕይወት የሚቆጣጠሩት በሳሞአ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሠለጠኑ ፓስተሮች ነበሩ። የደሴቶቹ ነዋሪዎች ለፓስተሮቹና ለቤተሰቦቻቸው ቀለብ የማቅረብና መኖሪያ ቤት የማዘጋጀት ግዴታ ነበረባቸው፤ እንዲያውም በሁሉ ነገር ምርጣቸውን እንዲሰጡ ይጠበቅባቸዋል። ነዋሪዎቹ ለቤተሰባቸው የሚሆን በቂ ምግብ ባይኖራቸውም እንኳ ለፓስተሮቹ ቀለብ እንዲያቀርቡ ይገደዱ ነበር።

እኔ በምኖርበት ደሴት ውስጥ ያለው ፓስተር የመንደራችንን ትምህርት ቤት ያስተዳድር የነበረ ሲሆን የሃይማኖት ትምህርት፣ ሒሳብና በተወሰነ መጠን ጂኦግራፊ ያስተምር ነበር። ፓስተሩ ተማሪዎችን ደም በደም እስኪሆኑ ድረስ ሲደበድባቸው ትዝ ይለኛል። ይሁንና ወላጆችን ጨምሮ ፓስተሩን ለመቃወም የደፈረ ሰው አልነበረም። የአምላክን ያህል ይከበር ነበር።

 አሥር ዓመት ሲሆነኝ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ በአካባቢው ብቸኛ ወደሆነው የመንግሥት ትምህርት ቤት ለመግባት ወደ ሌላ ደሴት ሄድኩ። ትምህርቴን ሳጠናቅቅ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጠርኩ። በወቅቱ እነዚህ ደሴቶች በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ሲሆን ጊልበርትና ኤሊስ ተብለውም ይጠሩ ነበር። በየሳምንቱ የሚታተመው የመንግሥት ጋዜጣ አዘጋጅ ከመሆኔ በፊት በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ውስጥ አገልግያለሁ። ልዑል ቻርልስን ለመቀበል ሲባል የተደረገውን የገንዘብ ወጪ አስመልክቶ አንድ አንባቢ የሰጠውን ሂስ በጋዜጣው ላይ እስካወጣሁበት ጊዜ ድረስ ሁሉም ነገር ሰላም ነበር። ደብዳቤውን የጻፈው ግለሰብ የተጠቀመው የሐሰት ስም ስለነበር አለቃዬ እውነተኛ ስሙን እንድነግረው ጠየቀኝ። ስሙን ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኔ ከአለቃዬ ጋር ተጋጨን፤ ወዲያውኑም ወሬው በሰፊው ተናፈሰ።

ከአለቃዬ ጋር ከተጋጨን ብዙም ሳይቆይ የመንግሥት ሥራዬን ለቅቄ የፖለቲካውን ዓለም ተቀላቀልኩ። ኑኩላይላይ በተካሄደው ምርጫ በማሸነፍ የንግድና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ሆኜ ተሾምኩ። ከጊዜ በኋላ የኪሪባቲ (የቀድሞዋ ጊልበርት) እና የቱቫሉ (የቀድሞዋ ኤሊስ) ደሴቶች ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት በሂደት ላይ ሳሉ በወቅቱ የነበረው ገዥ በቱቫሉ አስተዳደር ውስጥ የሚኒስትርነት ሥልጣን እንድቀበል ግብዣ አቀረበልኝ። ይሁንና የቅኝ ገዥዎች አጫፋሪ ሆኜ መታየት ስላልፈለግኩ የቀረበልኝን ግብዣ ሳልቀበል ቀረሁ። የመንግሥት ድጋፍ ባይኖረኝም ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት በተደረገ አጠቃላይ ምርጫ ላይ ተወዳደርኩ። ሆኖም አልተሳካልኝም። ከዚያ በኋላ ከባለቤቴ ጋር በመሆን የትውልድ ቦታዬ ወደሆነችው ደሴት ተመልሼ እንደማንኛውም ሰው ለመኖር ወሰንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? እሁድ ሰንበት ስለሆነ ከእኔ በስተቀር የደሴቶቹ ነዋሪዎች በሙሉ ዕለቱን እንደ ቅዱስ አድርገው ይመለከቱት ነበር። እኔ ግን እሁድን የማሳልፈው በጀልባ በመጓዝና ዓሣ በማጥመድ ነበር። ሃይማኖተኛ ሆኜ መታየት አልፈለግኩም። አባቴ እሱም ሆነ ሌሎች ሰዎች በእኔ ድርጊት ምን ያህል እንዳዘኑ ነገረኝ። ያም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወቴን እንድትቆጣጠረው ፈጽሞ አልፈለግኩም ነበር።

የቱቫሉ ዋና ከተማ ወደሆነችው ፉናፉቲ እሄድ ስለነበር አንድ ቀን ታናሽ ወንድሜ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ አብሬው እንድሄድ ጋበዘኝ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሚስዮናዊ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር በርከት ያሉ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ሰጠኝ። በተጨማሪም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተምሯቸው አንዳንድ መሠረተ ትምህርቶች አረማዊ ምንጭ እንዳላቸው የሚያጋልጥ አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ። መጽሐፉን ደጋግሜ አነበብኩት። ክርስቲያኖች ሰንበትን * የመጠበቅ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚገልጸውን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አስገራሚ እውነታዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ። ያወቅሁትን ነገር ለባለቤቴ ስነግራት ወዲያውኑ ቤተ ክርስቲያን መሄዷን አቆመች።

እኔ ግን ከሃይማኖት ጋር ምንም ንክኪ እንዳይኖረኝ ወስኜ ነበር። ወደ ሁለት የሚጠጉ ዓመታት ቢያልፉም ያወቅኳቸውን ነገሮች ከአእምሮዬ ማውጣት አልቻልኩም። በመጨረሻም ፉናፉቲ ለሚገኘው ሚስዮናዊ ደብዳቤ በመጻፍ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን ነገርኩት። እሱም ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ባገኘው ጀልባ ተሳፍሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ሊያስተምረኝ እኔ ወዳለሁበት መጣ። አባቴ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደፈለግኩ ሲያውቅ በጣም ተበሳጨ። ይሁን እንጂ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገር ካስተማሩኝ በኋላ እንደሆነ ነገርኩት።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በ1986 በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ ከዓመት በኋላም ባለቤቴ ተጠመቀች። ሁለቱ ሴት ልጆቻችንም መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ሲሆን አሁን የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል።

እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ ቀሳውስትና ምዕመናን የሚል ክፍፍል የሌለበት ሃይማኖት አባል በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል። (ማቴዎስ 23:8-12) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ይመሠክራሉ። (ማቴዎስ 4:17) ስለ እሱና ስለ ሕዝቡ እውነቱን እንዳውቅ ስለረዳኝ ይሖዋ አምላክን አመሰግነዋለሁ!

 ‘የይሖዋ ምሥክሮች በግድ ሊያሳምኑኝ አልሞከሩም።’—አልዪክሳንደር ሰስኮቭ

የትውልድ ዘመን፦ 1971

የትውልድ አገር፦ ሩሲያ

የኋላ ታሪክ፦ የጨበጣ ውጊያ አሠልጣኝ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት የሶቪየት ኅብረት ዋና ከተማ በነበረችው በሞስኮ ነው። ቤተሰቦቼ ይኖሩ የነበረው በአንድ ትልቅ አፓርታማ ውስጥ ሲሆን አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን በአንድ ፋብሪካ ውስጥ አብረው ይሠሩ ነበር። የአካባቢው ሰዎች በጣም ቀዥቃዣ ልጅ ከመሆኔ የተነሳ ሲማረሩብኝና አንድ ቀን በአጭሩ እንደምቀጭ አሊያም ዘብጥያ መውረዴ እንደማይቀር ሲናገሩ ትዝ ይለኛል። ያሉትም አልቀረም ገና በአሥር ዓመቴ በፖሊስ መዝገብ ላይ ሰፈርኩ።

አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ገባሁ፤ ከዚያም ድንበር ጠባቂ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ቤት ተመልሼ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጠርኩ፤ ይሁንና ሥራው አሰልቺ ሆነብኝ። በመሆኑም በሩሲያ የፖሊስ ኃይል ሥር ያለውን አድማ በታኝ ክፍል በመቀላቀል የጨበጣ ውጊያ አሠልጣኝ ሆንኩ። በሞስኮ የሚገኙ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድ አስተዋጽኦ ያደረግኩ ሲሆን ዓመፅ ወደተቀሰቀሰባቸው የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጉዣለሁ። ሥራዬን በማከናውንበት ጊዜ ውስጤን ጭንቅ ይለኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከሥራ ስመለስ ሌሊት በእንቅልፍ ልቤ ባለቤቴ ላይ ጉዳት እንዳላደርስ ስለምፈራ አልጋ ለይቼ እተኛ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር የምከተለው የዓመፅ ጎዳና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር እንደማይስማማ ተገነዘብኩ። በተጨማሪም ሲጋራ ማቆምና የአልኮል መጠጥ መቀነስ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ሆኖም ሥራዬን መቀየር እንደማልችል አስብ ነበር፤ ምክንያቱም ምንም ዓይነት ሙያ ስለሌለኝ ቤተሰቤን ለማስተዳደር የሚያስችል ሌላ ሥራ አላገኝም የሚል ፍራቻ ነበረኝ። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት መቼም ቢሆን መስበክ እንደማልችል ይሰማኝ ነበር።

በጊዜ ሂደት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ ትክክል መሆኑን እየተገነዘብኩ መጣሁ። እንዲሁም በ⁠ሕዝቅኤል 18:21, 22 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም አበረታታኝ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ [ቢመለስ] . . . በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም።”

የይሖዋ ምሥክሮች በግድ ሊያሳምኑኝ አለመሞከራቸው አስደስቶኛል፤ ከዚህ ይልቅ በምማረው ነገር ላይ ቆም ብዬ እንዳስብ ረድተውኛል። አርባ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ መጽሔቶቻቸውን በመውሰድ በሦስት ሳምንት ውስጥ አንብቤ ጨረስኩ። የተማርኩት ነገር እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ እንድሆን አደረገኝ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ትዳሬ ሊፈርስ ተቃርቦ ነበር። አሁን ግን ከባለቤቴ ጋር ያለን ግንኙነት ተሻሽሏል። እኔ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር ባለቤቴም ማጥናት ጀመረች፤ በኋላም አንድ ላይ ይሖዋን ለማገልገል ወሰንን። በአሁን ጊዜ ደስታ የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት እየመራን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጭ ሥራ ማግኘት ችያለሁ።

መጀመሪያ ላይ ከቤት ወደ ቤት ስሰብክ ከዚህ በፊት ወንጀለኞችን ለመያዝ ወደ ሰዎች ቤት ስሄድ የሚሰማኝ ዓይነት ስሜት ስለሚመጣብኝ በጣም እጨነቅ ነበር። አሁን ግን ትዕግሥቴን የሚፈታተን ነገር ቢያጋጥመኝ እንኳ መረጋጋት እንደምችል እርግጠኛ ነኝ። ሰዎችን እንዴት በትዕግሥት መያዝ እንደምችል በጊዜ ሂደት ተምሬያለሁ። አብዛኛውን ዕድሜዬን በከንቱ ማባከኔ በጣም ቢቆጨኝም በአሁኑ ጊዜ ሕይወቴን ትርጉም ባለው መንገድ እየመራሁ እንዳለ ይሰማኛል። ጉልበቴን ይሖዋ አምላክን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት በማዋሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]