በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎት—እንዴት?

ጸሎት—እንዴት?

የጸሎት ነገር ከተነሳ ብዙ ሃይማኖቶች ትኩረት የሚሰጡት ሰዎች በጸሎት ጊዜ ለሚኖራቸው አኳኋን፣ ለሚጠቀሟቸው ቃላት እንዲሁም ለሚፈጽሟቸው የአምልኮ ሥርዓቶች ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ እነዚህን ጉዳዮች ወደ ጎን ትተን ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ማለትም “እንዴት መጸለይ ይገባናል?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊሆኑ በሚችሉ ሌሎች ነጥቦች ላይ እንድናተኩር ይረዳናል።

ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በተለያየ ጊዜና ቦታ እንዲሁም በተለያየ አኳኋን እንደጸለዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ድምፅ ሳያሰሙም ሆነ ጮክ ብለው የጸለዩባቸው ጊዜያት አሉ። ወደ ሰማይ ቀና ብለው አሊያም አንገታቸውን ደፍተው ጸልየዋል። ጸሎታቸውን ለማቅረብ ምስሎችን፣ መቁጠሪያዎችን ወይም የጸሎት መጻሕፍትን ከመጠቀም ይልቅ በራሳቸው አባባል ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርበዋል። ጸሎታቸው በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኝ ያደረገው ምንድን ነው?

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ሰዎች ጸሎታቸውን ያቀረቡት ወደ አንድ አምላክ ብቻ ይኸውም ወደ ይሖዋ ነው። ይሁን እንጂ ሌላም አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። አንደኛ ዮሐንስ 5:14 እንዲህ ይላል፦ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።” ጸሎታችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። እንዲህ ስንል ምን ማለታችን ነው?

ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ለመጸለይ በመጀመሪያ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለጸሎት አስፈላጊ ነገር ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ታዲያ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ካልሆንን ጸሎታችንን አይሰማም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ አምላክ ፈቃዱን ለማወቅና ለመረዳት እንድንጥር ብሎም ያወቅነውን ተግባራዊ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (ማቴዎስ 7:21-23) ደግሞም ከተማርነው ጋር በሚስማማ መንገድ መጸለይ ያስፈልገናል።

ጸሎት በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት የሚያገኘው ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ በእምነት የሚቀርብና በኢየሱስ ስም የሚቀርብ ከሆነ ነው

ስለ ይሖዋና ስለ ፈቃዱ እያወቅን ስንሄድ እምነታችን እያደገ ይሄዳል፤ እምነት ደግሞ ለጸሎት ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው። ኢየሱስ “እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 21:22) እምነት ማለት ሁሉንም ነገር እንዲሁ በጭፍን መቀበል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ነገር ላይ እምነት ማሳደር ሲባል ያ ነገር ባይታይም እንኳ መኖሩን በተጨባጭ ማስረጃ መቀበል ማለት ነው። (ዕብራውያን 11:1) ልናየው የማንችለው ይሖዋ፣ እውንና ልንተማመንበት የምንችል አምላክ እንደሆነ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ከዚህም በላይ ይሖዋ እምነት እንዲጨምርልን ምንጊዜም መጠየቅ የምንችል ሲሆን እሱም ለእኛ የሚያስፈልገንን ነገር መስጠት ያስደስተዋል።—ሉቃስ 17:5፤ ያዕቆብ 1:17

አሁንም ‘እንዴት መጸለይ አለብን?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆን ሌላ አስፈላጊ ነገር አለ። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል።  (ዮሐንስ 14:6) ስለዚህ አብ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ በኩል ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ በስሙ እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:13፤ 15:16) እንዲህ ሲባል ወደ ኢየሱስ መጸለይ አለብን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ፍጹምና ቅዱስ ወደ ሆነው አባታችን መቅረብ የምንችልበት መንገድ መሆኑን በማስታወስ በስሙ እንጸልያለን።

ኢየሱስን በጣም የሚቀርቡት ተከታዮቹ በአንድ ወቅት “እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብለው ጠይቀውት ነበር። (ሉቃስ 11:1) ተከታዮቹ እየጠየቁት የነበረው እስካሁን ስለተወያየንባቸው መሠረታዊ ነገሮች እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ማወቅ የፈለጉት ስለ ጸሎታቸው ይዘት ነበር፤ በሌላ አባባል ‘ስለ ምን ጉዳይ እንጸልይ?’ ብለው የጠየቁት ያህል ነበር።