በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጸሎትን የሚሰማ’

‘ጸሎትን የሚሰማ’

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ጸሎትን የሚሰማ’

1 ዜና መዋዕል 4:9, 10

በእርግጥ ይሖዋ አምላክ ታማኝ አምላኪዎቹ የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት ይሰማል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያቤጽ ስለሚባል እምብዛም የማይታወቅ ሰው ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ በእርግጥም ይሖዋ ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ መሆኑን ያሳያል። (መዝሙር 65:2) ይህ አጭር ታሪክ የሚገኘው በማንጠብቀው ቦታ ይኸውም በአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ መግቢያ ላይ ባለው የዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ነው። እስቲ 1 ዜና መዋዕል 4:9, 10⁠ን አብረን እንመርምር።

ስለ ያቤጽ የምናውቀው ነገር ቢኖር በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ብቻ ነው። ቁጥር 9 “እናቱም ‘በጣር የወለድሁት’ ስትል ስሙን ያቤጽ አለችው” ይላል። * እንዲህ ያለ ስም ለልጇ ያወጣችለት ለምንድን ነው? እሱን በምትወልድበት ወቅት ከወትሮው በተለየ ምጥ ጠንቶባት ይሆን? ምናልባትም መበለት ስለነበረች ይሆን? ከሆነ ልጇን ስትወልድ ባሏ አጠገቧ አለመሆኑ አስጨንቋት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይገልጽም። ያም ሆነ ይህ እናቱ ከጊዜ በኋላ በዚህ ልጅ እንድትኮራ የሚያደርጋት ምክንያት ይኖራታል። የያቤጽ ወንድሞችና እህቶች ጥሩ ሰዎች የነበሩ ሊሆን ቢችልም እሱ ግን “ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ሰው ነበረ።”

ያቤጽ የጸሎት ሰው ነበር። ያቤጽ ጸሎቱን የጀመረው የአምላክን በረከት ለማግኘት በመለመን ነው። ከዚያም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ሦስት ልመናዎችን አቀረበ።

በመጀመሪያ “ግዛቴንም እንድታሰፋ እለምንሃለሁ” ሲል አምላክን ተማጽኗል። (ቁጥር 10) ይህ የተከበረ ሰው የባልንጀራውን መሬት የሚመኝ ስግብግብ አልነበረም። ከልቡ ያቀረበው ይህ ልመና ይዞታን ሳይሆን ሰዎችን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። ምናልባት እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ በርካታ ሰዎችን መያዝ የሚችል ይዞታ እንዲኖረው ግዛቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲሰፋለት መጠየቁ ሊሆን ይችላል። *

ቀጥሎም ያቤጽ የአምላክ “እጅ” ከእሱ ጋር እንዲሆን ልመና አቅርቧል። የአምላክ እጅ ሲባል በሥራ ላይ የዋለውን ኃይሉን ያመለክታል፤ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመርዳት በዚህ ኃይል ይጠቀማል። (1 ዜና መዋዕል 29:12) ያቤጽ የለመነውን ነገር ለማግኘት ዘወር ያለው ወደ አምላክ ሲሆን ይሖዋም በእሱ ላይ እምነት ያላቸውን ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት እጁ አጭር አይደለም።—ኢሳይያስ 59:1

በሦስተኛ ደረጃ ያቤጽ “እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ” (የ1954 ትርጉም) በማለት ጸልዮአል። “እንዳያሳዝነኝ” የሚለው አገላለጽ ያቤጽ የጸለየው መከራ እንዳይደርስበት ሳይሆን ክፋት በሚያስከትለው ነገር እንዳያዝን ወይም እንዳይሸነፍ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል።

ያቤጽ ያቀረበው ጸሎት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮች እንደሚያሳስቡት እንዲሁም ጸሎት ሰሚ በሆነው አምላክ ላይ እምነት እንዳለው በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ይሖዋ ምን መልስ ሰጠው? ይህ አጭር ዘገባ ታሪኩን የሚቋጨው “እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው” በማለት ነው።

ጸሎት ሰሚ የሆነው አምላክ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። የሚያመልኩት ሰዎች በሚያቀርቡት ጸሎት ይደሰታል። በእሱ ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሁሉ እንደሚከተለው ያለ መተማመን ሊኖራቸው ይችላል፦ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐንስ 5:14

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ያቤጽ የሚለው ስም “ሥቃይ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው።

^ አን.4 ታርገም የሚባለው አይሁዶች ያዘጋጁት ነፃ የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም የያቤጽን ጸሎት እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፦ “ብዙ ልጆች በመስጠት ባርከኝ፤ ደቀ መዛሙርት በመስጠት ግዛቴን አስፋልኝ።”