በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ ያከናውናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ ያከናውናሉ?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ ያከናውናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ አከናውነው አያውቁም። ልክ እንደ ኢየሱስ እነሱም ዋነኛ ተልእኳቸው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች መስበክ እንደሆነ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት በሚያከናውኑት ተአምራዊ ፈውስ ሳይሆን ከዚህ በላቀ ነገር እንደሆነ ያምናሉ።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በርኅራኄ ተገፋፍቶ የታመሙ ሰዎችን መፈወሱ ለሁላችንም ከፍተኛ ትርጉም አለው። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድርበት ወቅት “ታምሜአለሁ” የሚል እንደማይኖር ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ኢሳይያስ 33:24

ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስለሚከናወነው ፈውስ ምን ማለት ይቻላል? በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሆነ ከክርስትና እምነት ውጭ ባሉ አንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ ተአምራዊ ፈውስ እንደሚከናወን ሲነገር እንሰማለን። ይሁንና ኢየሱስ ‘በስሙ ብዙ ተአምራት አድርገናል’ የሚሉ ሰዎችን በተመለከተ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። እነዚህን ሰዎች “ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ” ይላቸዋል። (ማቴዎስ 7:22, 23) ታዲያ በዘመናችን ተአምራዊ ፈውስ እናከናውናለን የሚሉ ሰዎች ፈጽመዋቸዋል የሚባሉት “ተአምራት” እነዚህ ግለሰቦች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ወይም የእሱን ሞገስ እንዳገኙ ያመለክታሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ስላከናወናቸው ፈውሶች ምን እንደሚል እንመልከት። በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን ይህን ዘገባ በዛሬው ጊዜ ፈውስ ከሚከናወንበት መንገድ ጋር በማነጻጸር በዘመናችን የሚፈጸመው ፈውስ የአምላክ ድጋፍ ያለው መሆን አለመሆኑን መለየት እንችላለን።

ኢየሱስ፣ ተከታዮች ለማፍራት ወይም ብዙ ሰዎች ወደ እሱ እንዲመጡ ለማድረግ ሲል ፈውስ አከናውኖ አያውቅም። እንዲያውም ብዙ ሰዎችን የፈወሰው ሕዝብ በማያየው ጊዜ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ከፈወሰ በኋላ ይህን ተአምር ለማንም እንዳይናገሩ ያዛቸው ነበር።—ሉቃስ 5:13, 14

ኢየሱስ ተአምራት ሲያከናውን ፈጽሞ ክፍያ ጠይቆ አያውቅም። (ማቴዎስ 10:8) ኢየሱስ አንዴም ቢሆን ተአምር ለማከናወን ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቶ አያውቅም። ወደ ኢየሱስ የመጡት ሁሉም ሰዎች ከሕመማቸው ሙሉ በሙሉ ተፈውሰዋል፤ የግለሰቦቹ መፈወስ በእምነታቸው መጠን ላይ የተመካ አልነበረም። (ሉቃስ 6:19፤ ዮሐንስ 5:5-9, 13) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ሙታንን እንኳ አስነስቷል!—ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ ዮሐንስ 11:38-44

ምንም እንኳ ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን የፈጸመ ቢሆንም አገልግሎቱን ሲያከናውን ዋነኛ ትኩረቱ የፈጸማቸውን ተአምራት በመመልከት በስሜት ተነሳስተው እሱን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎችን በመሰብሰብ ላይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዋነኛ ሥራው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ ነበር። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በአምላክ መንግሥት ሥር ፍጹም ጤንነት ስለማግኘት የሚገልጸውን ተስፋ ለሌሎች በመናገር ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ አደራጅቷቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ፈውስ የማከናወን ልዩ ስጦታ እንደነበራቸው አይካድም፤ ሆኖም ይህ ዓይነቱ ስጦታ እንደሚቀር ተነግሮ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 12:29, 30፤ 13:8, 13) ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት በሚያከናውኑት ፈውስ ሳይሆን በመካከላቸው ባለው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:35) በአሁኑ ጊዜ የሚከናወነው ተአምራዊ ፈውስ፣ ከሁሉም ዘር ወይም የኑሮ ሁኔታ የመጡ ሰዎችን እንዲህ ባለው ፍቅር ያስተሳሰረ እውነተኛ የክርስቲያኖች ቤተሰብ ማስገኘት አልቻለም።

ይሁንና በዛሬው ጊዜ በመካከላቸው ያለው ፍቅር በጣም ጠንካራ በመሆኑ አንዳቸው ሌላውን ሊጎዱ ይቅርና ማንንም ሰው ለመጉዳት ፈቃደኛ የማይሆኑ ክርስቲያኖች አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ኃይለኛ ጦርነት ባለበት ጊዜም እንኳ ሌሎችን ለመጉዳት ፈቃደኞች አይደሉም። እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ከይሖዋ ምሥክሮች ውጭ ማንም ሊሆን አይችልም። የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስን ዓይነት ፍቅር በማሳየት በዓለም ዙሪያ ይታወቃሉ። በዘር፣ በዜግነት፣ በባሕልና በጎሳ የተለያዩ ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደ ተአምር የሚቆጠር ሲሆን ይህ ሊሆን የቻለው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ብቻ ነው። ታዲያ አንተስ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች በአንዱ ላይ በመገኘት እንዲህ ዓይነቱን ተአምር ለምን አትመለከትም?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በዘመናችን ተአምራዊ ፈውስ የሚያከናውኑ ሰዎች (በስተቀኝ እንደሚታየው) በእርግጥ የአምላክ ድጋፍ አላቸው?