በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስታቸዋል። አንተስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ግራ የሚያጋባህ ጥያቄ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ስምዖን የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሲሰብክ ቢንያም የሚባል ሰው እንዳገኘ አድርገን እናስብ።

“መንፈስ ቅዱስ” ምንድን ነው ብለህ ታምናለህ?

ቢንያም፦ የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈስ ቅዱስ ስለማታምኑ ክርስቲያኖች እንዳልሆናችሁ ይሰማኛል።

ስምዖን፦ በመጀመሪያ፣ ክርስቲያኖች መሆናችንን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ። ዛሬ ጠዋት ወደ ቤትህ የመጣሁትም በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማምን ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲሰብኩ አዟቸዋል። ይሁን እንጂ ስለ መንፈስ ቅዱስ አንስተህ ነበር፤ አንተ “መንፈስ ቅዱስ” ምን እንደሆነ ነው የምታምነው?

ቢንያም፦ መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ሥላሴዎች አንዱ እንደሆነ አምናለሁ። መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እንደሚልክልን ቃል የገባው ረዳት ነው። ይህ ረዳት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። አብሮኝ እንዳለ እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ።

ስምዖን፦ ብዙ ሰዎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት ከአንተ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ከተወሰነ ጊዜ በፊት ምርምር አድርጌ ነበር። ጥቂት ደቂቃዎች ካሉህ ያገኘሁትን ሐሳብ ባካፍልህ ደስ ይለኛል።

ቢንያም፦ እሺ፣ ይቻላል።

ስምዖን፦ ብዙ ጊዜ እንዳልወስድብህ በዚህ ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ብቻ እንመልከት። መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እንደሚልክልን ቃል የገባው ረዳት መሆኑን ጠቅሰህ ነበር። እኔም በዚህ እስማማለሁ። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ ጋር እኩል የሆነና የራሱ ማንነት ያለው አካል እንደሆነ ይሰማሃል?

ቢንያም፦ አዎን፣ የተማርኩት እንደዚህ ነው።

መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ነው?

ስምዖን፦ መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚረዳን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እስቲ እንመልከት። ይህን ጥቅስ ሳታውቀው አትቀርም። በሐዋርያት ሥራ 2:1-4 ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ይላል፦ “በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር፤ ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ምላሶች ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ  ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።”

ቢንያም፦ ይህን ታሪክ አውቀዋለሁ።

ስምዖን፦ ቢንያም እስቲ አስበው፣ አንድ ሰው በሌላ ሰው ውስጥ ገብቶ ሊሞላው ይችላል?

ቢንያም፦ ይኼማ የማይሆን ነገር ነው።

ስምዖን፦ እስቲ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ትንሽ ወረድ ብለን ቁጥር 17⁠ን እንመልከት። የጥቅሱ የመጀመሪያ ክፍል “አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ’” ይላል። ቢንያም፣ እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅህ፦ አምላክ ከእሱ ጋር እኩል ከሆነው አምላክ ላይ የተወሰነውን ክፍል ወስዶ በሰዎች ላይ ሊያፈሰው ይችላል?

ቢንያም፦ ይህም ሊሆን አይችልም።

ስምዖን፦ መጥምቁ ዮሐንስ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን ለየት ባለ መንገድ ገልጾታል። ይህ ሐሳብ የሚገኘው በማቴዎስ 3:11 ላይ ነው። ጥቅሱን አንተ ታነበዋለህ?

ቢንያም፦ “እኔ ንስሐ በመግባታችሁ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ሆኖም ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ አልበቃም። እሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።”

ስምዖን፦ አመሰግንሃለሁ። መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሰዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ምን እንደሚደረጉ ተናግሯል?

ቢንያም፦ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚጠመቁ ተናግሯል።

ስምዖን፦ ትክክል ነህ። ዮሐንስ በእሳት ስለ መጠመቅም እንደጠቀሰ ልብ በል። እሳት የራሱ ማንነት ያለው አካል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህ ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል እንደሆነ እየተናገረ ያለ ይመስልሃል?

ቢንያም፦ አይ፣ አይመስለኝም።

ስምዖን፦ ስለዚህ እስካሁን በተመለከትናቸው ጥቅሶች መሠረት መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል አይደለም።

ቢንያም፦ ትክክል ነህ።

“ረዳት” የሆነው እንዴት ነው?

ስምዖን፦ ቅድም መንፈስ ቅዱስ “ረዳት” እንደሆነ ጠቅሰህ ነበር። ኢየሱስ በዮሐንስ 14:26 ላይ መንፈስ ቅዱስ “ረዳት” እንደሆነ ተናግሯል። እስቲ ጥቅሱን እናንብበው፦ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።” አንዳንዶች ይህ ጥቅስ፣ መንፈስ ቅዱስ ረዳት እንደሆነና እንደሚያስተምር ስለሚናገር ‘መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ነው’ የሚለውን ሐሳብ እንደሚደግፍ ይሰማቸዋል።

ቢንያም፦ አዎን፣ እኔም ቢሆን እንዲህ ነው የሚሰማኝ።

ስምዖን፦ ይሁንና ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሲናገር ዘይቤያዊ አነጋገር እየተጠቀመ ይሆን? ኢየሱስ ስለ ጥበብ ሲናገር ምን እንዳለ ልብ በል፤ ሉቃስ 7:35 ላይ “የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ተረጋግጧል” ብሎ ነበር። በዚህ ጥቅስ መሠረት ጥበብ የራሷ ማንነት ያላት አካል ነች ብለህ ታምናለህ? ደግሞስ ቃል በቃል ልጆች አሏት ማለት ነው?

ቢንያም፦ በፍጹም፤ ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር እንደሆነ ግልጽ ነው።

ስምዖን፦ ትክክል ነህ። ኢየሱስ ለመግለጽ የፈለገው፣ ጥበብ የምትታየው በድርጊት መሆኑን ነው። ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሰውኛ የሚባለውን ዘይቤያዊ አነጋገር ይጠቀማል። ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር፣ ሰው ያልሆነው ወይም የሰውነት ባሕርይ የሌለው ነገር የሰውን ባሕርይ ተላብሶ የሚቀርብበት መንገድ ነው። እኛም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዲህ ያለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ ጊዜ እንጠቀማለን። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ባለው ደስ የሚል ቀን አንድ ሰው “ፀሐይዋ እንድትገባ መጋረጃውን ግለጠው” ብሎ ሊናገር ይችላል አይደል?

ቢንያም፦ አዎን፣ ይህ የተለመደ አባባል ነው።

ስምዖን፦ ታዲያ ይህ ሲባል ፀሐይዋ ልክ እንደ ሰው ቤትህ ገብታ ትስተናገዳለች ማለት ነው?

ቢንያም፦ አይ፣ እንደዚያ ማለት አይደለም። ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።

ስምዖን፦ ስለዚህ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደ ረዳት ወይም አስተማሪ አድርጎ ሲናገር ዘይቤያዊ አነጋገር መጠቀሙ ይሆን?

 ቢንያም፦ ይመስለኛል። እንዲያውም ይህ ዓይነቱ አመለካከት መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ እንደሚፈስ እንዲሁም ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እንደሚጠመቁ ካነበብክልኝ ጥቅሶች ጋር ይስማማል። ሆኖም መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ካልሆነ ታዲያ ምንድን ነው?

መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

ስምዖን፦ በሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ ይነግረናል። ይህን ጥቅስ አንተ ብታነበውስ?

ቢንያም፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”

ስምዖን፦ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ከኃይል ጋር አያይዞ እንደገለጸው ልብ በል። ቀደም ብለን ባነበብናቸው ጥቅሶች መሠረት ይህ ኃይል የሚመጣው ከየት ይመስልሃል?

ቢንያም፦ ከአምላክ ማለትም ከአብ ዘንድ ነው።

ስምዖን፦ ትክክል ነህ። መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክ አጽናፈ ዓለምን ለመፍጠር የተጠቀመበት ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዘፍጥረት 1:2 ላይ “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር” ይላል። የአምላክ መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክ ዓላማውን ለማከናወንና ፈቃዱን ለመግለጽ የሚጠቀምበት በዓይን የማይታይ ኃይል ነው። አንድ ተጨማሪ ጥቅስ እንመልከት። ጥቅሱ የሚገኘው በሉቃስ 11:13 ላይ ነው። እባክህ ይህን ጥቅስ ታነበው?

ቢንያም፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”

ስምዖን፦ በሰማይ ያለው አባት በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሥልጣን ካለውና ለሚለምኑት የሚሰጠው ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር እኩል ሊሆን ይችላል?

ቢንያም፦ አይ ሊሆን አይችልም። ለማለት የፈለግኸው ገብቶኛል።

ስምዖን፦ ቢንያም፣ ብዙ ጊዜ እንደሌለህ ስለነገርኸኝ ከዚህ በላይ ጊዜህን አልውሰድብህ። ይሁን እንጂ ውይይታችንን ለማጠቃለል አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ። እስካሁን ከተመለከትናቸው ጥቅሶች አንጻር መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው ትላለህ?

ቢንያም፦ አምላክ የሚጠቀምበት ኃይል ነው።

ስምዖን፦ ትክክል ነህ። እንዲሁም በዮሐንስ 14:26 ላይ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደ ረዳት ወይም አስተማሪ አድርጎ ሲናገር ሰውኛ ተብሎ የሚጠራውን ዘይቤያዊ አነጋገር እየተጠቀመ እንደነበር ተመልክተናል።

ቢንያም፦ አዎን፣ ይህን አላውቅም ነበር።

ስምዖን፦ ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ የምናገኘው አንድ የሚያበረታታ ትምህርት አለ።

ቢንያም፦ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ስምዖን፦ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አምላክ መንፈሱን በመስጠት እንዲረዳን ልንለምነው እንችላለን። በተጨማሪም ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ እንድንችል መንፈሱን እንዲሰጠን አምላክን መጠየቅ እንችላለን።

ቢንያም፦ የሚገርም ነው! ስለዚህ ጉዳይ በደንብ ላስብበት እፈልጋለሁ።

ስምዖን፦ ከመሄዴ በፊት ሌላም ልታስብበት የምትችል ነጥብ ላንሳልህ። መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክ የሚጠቀምበት ኃይል በመሆኑ አምላክ የፈለገውን ነገር ሁሉ ለማከናወን ሊያውለው ይችላል አይደል?

ቢንያም፦ እንዴታ!

ስምዖን፦ ታዲያ ይህን ገደብ የለሽ ኃይሉን በዓለም ላይ የምናየውን መከራና ክፋት ለማስወገድ እስካሁን ያልተጠቀመበት ለምንድን ነው? ይህ ጉዳይ አሳስቦህ ያውቃል? *

ቢንያም፦ አዎን፣ ያሳስበኛል።

ስምዖን፦ ታዲያ በሚቀጥለው ሳምንት በዚህ ሰዓት መጥቼ ስለዚህ ጉዳይ ብንወያይ ምን ይመስልሃል?

ቢንያም፦ በጣም ደስ ይለኛል። ሳምንት እንገናኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.57 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11⁠ን ተመልከት።