በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የነበራቸው ፍርሃት ተወገደላቸው

የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የነበራቸው ፍርሃት ተወገደላቸው

 የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የነበራቸው ፍርሃት ተወገደላቸው

በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ ጋሪና ካረን የዓለም መጨረሻ እንደቀረበ አመኑ። ስለዚህ ከከተማ ወጥተው ወደ ገጠር ሄዱ፤ እንዲሁም በሁሉ ነገር ራሳቸውን ችለው ለመኖር ወሰኑ። ከጥፋቱ መትረፍ ፈልገው ነበር።

የሚያስፈልጋቸውን ሙያ ለመማር መጻሕፍት ገዙ፣ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን ተማሩ ብሎም የተለያዩ ሴሚናሮችን ተካፈሉ፤ ከዚህም ባሻገር የቻሉትን ያህል ብዙ ሰዎችን አነጋገሩ። የጓሮ አትክልቶችንና 50 የሚሆኑ አጫጭር የፍራፍሬ ዛፍ ዝርያዎችን ተከሉ። የእህልና የአትክልት ዘሮችን እንዲሁም የግብርና መሣሪያዎችን አከማቹ። እህል ማምረትና ምግብ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚቻልበትን መንገድ ተማሩ። አንዲት ጓደኛቸው እንስሳት ማረድንና ሥጋ ሳይበላሽ የሚቆይበትን ዘዴ አስተማረቻቸው። ካረን፣ ምናልባት ቀለብ ቢያልቅባቸው የጫካ ዕፅዋትና ሥራ ሥሮችን እየበሉ መቆየት እንዲችሉ እነዚህን ለይታ ለማወቅ የሚያስችላት ትምህርት ቀሰመች። ጋሪ ደግሞ ከበቆሎ ነዳጅ ማውጣት የሚቻልበትን መንገድ ተማረ፤ እንዲሁም በብረት በመጠቀም የእንጨት ምድጃ የሠራ ሲሆን ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ የያዘ ቤትም ገነባ።

ካረን “በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ይታዩ ከነበሩት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ሥልጣኔ ወዲያውኑ እንደሚያከትም ተሰምቶኝ ነበር” ብላለች። ጋሪም እንደሚከተለው ብሏል፦ “እንደሌላው ወጣት ሁሉ እኔም ዘረኝነትን፣ የቬትናም ጦርነትንና ሙስናን ለማስወገድ ንቁ ተሳትፎ አደርግ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ያሰብኩት እንደማይሳካ ገባኝ። የሰው ዘር ራሱን ለጥፋት በሚዳርግ ጎዳና ላይ እየገሰገሰ እንዳለ ሆኖ ታየኝ።”

 ጋሪ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን ምሽት ላይ ትርፍ ጊዜ ሳገኝ መጽሐፍ ቅዱስ አነሳሁና ከማቴዎስ እስከ ራእይ ድረስ አነበብኩ። በቀጣዮቹ አራት ቀናትም ምሽት ላይ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደገና አነበብኩት። በአምስተኛው ቀን ጠዋት ላይ ለካረን እንዲህ አልኳት፦ ‘የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው። አምላክ ምድርን ለማጽዳት በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። ከጥፋቱ የሚተርፉትን ሰዎች መፈለግ አለብን።’” ጋሪና ካረን ከመጨረሻው ዘመን ለመትረፍ የሚዘጋጁ ሰዎችን ለማግኘት ወደተለያዩ ሃይማኖቶች መሄድ ጀመሩ።

ብዙም ሳይቆይ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታቸው መጣና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ካረን እንዲህ ብላለች፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች ግልጽ ሲሆኑልኝ በጣም ተደሰትኩ። የመጨረሻውን ዘመን አስመልክቶ እውነቱን የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ፤ በመጨረሻ እውነቱን ለመረዳት ቻልኩ። ወደፊት የሚፈጸም እርግጠኛ ተስፋ መኖሩን ተማርኩ። ከሁሉም በላይ ግን የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪና አምላክ ከሆነው የሰማዩ አባቴ ጋር ወዳጅነት መሠረትኩ።”

ጋሪ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ጀመርኩ። አንዴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ ከዚያ መላቀቅ አልቻልኩም። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ሳነብና በትክክል እየተፈጸሙ መሆናቸውን የሚያሳዩትን ማስረጃዎች ስመረምር፣ አምላክ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ ሆንኩ። ‘ሰዎች መዘጋጀት ያለባቸው ለጥፋት ሳይሆን አምላክ እንድናገኝ ለሚፈልገው ሕይወት ነው’ ብዬ አሰብኩ።” ጋሪና ካረን ስለ መጪው ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት ያዙ። ስለ ዓለም መጨረሻ ከመጨነቅ ይልቅ አምላክ የሰውን ዘር እያስጨነቁት ያሉትን ችግሮች እንደሚያስወግድና ምድርንም መልሶ ገነት እንደሚያደርጋት እርግጠኞች ሆኑ።

ጋሪና ካረን በአሁኑ ጊዜ ይኸውም ከ25 ዓመት በኋላ ምን እያደረጉ ይሆን? ካረን እንዲህ ትላለች፦ “ለይሖዋ አምላክ ያለኝን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለኝን እምነት መገንባቴን የቀጠልኩ ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለመርዳት እጥራለሁ። ጋሪና እኔ እርስ በርሳችን ተደጋግፈን ቤተሰባችን ጠንካራ እንዲሆንና አምላክን በአንድነት እያመለከ እንዲቀጥል ለማድረግ እንጥራለን። የተደራጀን ሆነን ለመኖር እንዲሁም ለሌሎች ሰዎችና ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት መስጠት እንድንችል ኑሯችንን ቀላል ለማድረግ እንጥራለን።”

ጋሪም አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሕዝቦች እፎይታ እንዲያስገኝ አዘውትሬ እጸልያለሁ። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በሰበክሁ ቁጥር ቢያንስ ለአንድ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተስፋው ለመናገር እንድችል እጸልያለሁ። ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋ በደግነት ለጸሎቴ መልስ ሰጥቶኛል። እኔና ካረን ይሖዋ በቅርቡ በምድር ላይ ታላላቅ ለውጦችን እንደሚያመጣ እናምናለን፤ ይሁን እንጂ የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የነበረን ፍርሃት ተወግዷል።”—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:11, 12

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋሪና ካረን በአሁኑ ጊዜ ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ተስፋ እንዲያውቁ በመርዳት ላይ ይገኛሉ