በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ’

‘ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ’

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ’

2 ሳሙኤል 22:26

የምናምነው ሰው ሲያሳዝነን ወይም ሲክደን ስሜታችን በጣም ይጎዳል። ታማኝነት በጠፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለው ሁኔታ የተለመደ ነገር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ ለእኛ ያለውን ታማኝነት በምንም ዓይነት መንገድ እንደማያጓድል ልንተማመንበት የምንችል አካል አለ? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በዚህ ረገድ የሰጠውን ምሥክርነት እንመልከት።

ዳዊት በሕይወት ዘመኑ የከፉ ክህደቶች አጋጥመውታል። በዳዊት ይቀና የነበረው የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል አሳድዶታል፤ በዚህም ምክንያት በስደት ይኖር ነበር። በቤተሰቡ ውስጥ ደግሞ ሚስቱ ሜልኮል ለባሏ ያላትን ታማኝነት ከመጠበቅ ይልቅ ‘በልቧ ንቃዋለች።’ (2 ሳሙኤል 6:16) የዳዊት ታማኝ አማካሪ የነበረው አኪጦፌል ዳዊትን በመካድ በእሱ ላይ በተደረገው ሴራ ተካፋይ ሆኗል። ለመሆኑ የዚህ ሴራ ጠንሳሽ ማን ነበር? የሚገርመው ከአብራኩ የወጣው የገዛ ልጁ አቤሴሎም ነበር! ዳዊት እንዲህ ያለ ክህደት በተደጋጋሚ ያጋጠመው መሆኑ ተስፋ ቆርጦ ታማኝነቱን ምንጊዜም የማያጓድል አካል የለም እንዲል አድርጎት ይሆን?

የዚህን ጥያቄ መልስ በ2 ሳሙኤል 22:26 ላይ ከሰፈረውና ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ማግኘት እንችላለን። የማይናወጥ እምነት የነበረው ዳዊት ማራኪ በሆነው መዝሙሩ ላይ ይሖዋ አምላክን “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን . . . ታሳያለህ” ብሎታል። ሰዎች ምንም ያህል ቢያሳዝኑት ይሖዋ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ዳዊት ይተማመን ነበር።

እስቲ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ አንድ በአንድ እንመርምር። ‘ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ሐረግ “ፍቅራዊ ደግነትህን ታሳያለህ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እውነተኛ ታማኝነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። ይሖዋ ለእሱ ታማኝ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ራሱን በፍቅር ያቆራኛል። *

ታማኝነት በተግባር የሚገለጽ ከስሜት ያለፈ ነገር መሆኑን ልብ በል። ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ እንደተረዳው ይሖዋ ታማኝ መሆኑን ያሳያል። ዳዊት ሕይወቱ በጨለማ በተዋጠበት ጊዜ ይሖዋ ይህን ታማኝ ንጉሥ ረድቶታል፣ በታማኝት ጠብቆታል እንዲሁም መመሪያ ሰጥቶታል። ውለታ የማይረሳው ዳዊት ‘ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ ሊታደገው’ የሚችለው ይሖዋ እንደሆነ አውቋል።—2 ሳሙኤል 22:1

ታዲያ ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ይሖዋ አይለወጥም። (ያዕቆብ 1:17) ለሚያወጣው መመሪያ ታማኝ ከመሆኑም በላይ የገባውን ቃል ይፈጽማል። ዳዊት በሌላ መዝሙሩ ላይ ይሖዋ “ታማኞቹንም አይጥልም” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 37:28

ይሖዋ ለምናሳየው ታማኝነት ትልቅ ግምት ይሰጣል። እሱን በታማኝነት ስንታዘዝ ታዛዥነታችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የእሱን የታማኝነት ምሳሌ እንድንከተል ያበረታታናል። (ኤፌሶን 4:24፤ 5:1) በእነዚህ መንገዶች ታማኝነት ስናሳይ ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን መተማመን እንችላለን። ሰዎች ምንም ያህል ቢያሳዝኑን ይሖዋ ያጋጠመንን ማንኛውንም ችግር መቋቋም እንድንችል በመርዳት በታማኝነት ከእኛ ጎን ይቆማል። ታዲያ ‘ታማኝ ወደ ሆነው አምላክ’ ለመቅረብ አልተገፋፋህም?—ራእይ 16:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ሁለተኛ ሳሙኤል 22:26 ከመዝሙር 18:25 ጋር ተመሳሳይ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን መዝሙር “ለታማኙ ሙሉ በሙሉ ፍቅርህን ታሳያለህ” በማለት ተርጉሞታል።—ዘ ሳልምስ ፎር ቱዴይ