በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ከአማቶች ጋር ተስማምቶ መኖር

ከአማቶች ጋር ተስማምቶ መኖር

ጄኒ * እንዲህ ትላለች፦ የራየን እናት እኔን ስትነቅፍ ምንም ይሉኝታ አይሰማትም። እርግጥ የእኔም ወላጆች ቢሆኑ ለራየን የተሻሉ አይደሉም። እንዲያውም ወላጆቼ በሌላ ሰው ላይ እንዲህ ሲሆኑ አይቼ አላውቅም! ወላጆቻችንን መጠየቅ ለሁለታችንም ጭንቀት የሚፈጥር ነገር ሆኖብናል።

ራየን እንዲህ ይላል፦ እናቴ ለልጆቿ የሚመጥን የትዳር ጓደኛ ይኖራል ብላ ፈጽሞ አስባ አታውቅም፤ በጄኒ ላይ ስህተት መፈላለግ የጀመረችው ገና ከተዋወቁበት ጊዜ አንስቶ ነው። የጄኒ ወላጆችም ቢሆኑ ለእኔ እንደዚያው ነበሩ፤ ሁልጊዜ ያጣጥሉኛል። ችግሩ ግን ወላጆቻችን አንድ ነገር ካደረጉ በኋላ እኔም ሆንኩ ጄኒ ወላጆቻችንን ደግፈን መጣላታችን ነው።

ኮሜዲያን ከአማቶች ጋር የሚፈጠረውን ግጭት ታዳሚዎቻቸውን ለማሳቅ የሚጠቀሙበት ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው፤ በገሐዱ ዓለም ግን ሁኔታው የሚያስቅ አይደለም። በሕንድ የምትኖር ሪና የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “የባለቤቴ እናት ለብዙ ዓመታት በትዳራችን ውስጥ ይገቡ ነበር። እሳቸውን መናገር ስለማልችል ብዙውን ጊዜ ንዴቴን የምወጣው ባለቤቴ ላይ ነበር። ባለቤቴ ነጋ ጠባ ጥሩ ባል ከመሆንና ጥሩ ልጅ ከመሆን አንዱን መምረጥ የነበረበት ይመስላል።”

አንዳንድ አማቶች በልጆቻቸው ትዳር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡት ለምንድን ነው? ከላይ የተጠቀሰችው ጄኒ ይህ ሊሆን የሚችልበትን አንዱን ምክንያት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ተሞክሮ የሌለው አንድ ወጣት፣ ልጃቸውን የመንከባከቡን ኃላፊነት በሚገባ ይወጣል የሚል እምነት ስለሌላቸው ነው።” የሪና ባል ዲለፕ፣ ሌላውን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው ልጃቸውን ያሳደጉ ወላጆች [ልጃቸው ካገባ በኋላ] ገሸሽ እንደተደረጉ ሊሰማቸው ይችላል። በተጨማሪም ወንድ ወይም ሴት ልጃቸው ትዳራቸውን ጥሩ አድርገው ለመምራት የሚያስችላቸው ጥበብ ይጎድላቸዋል ብለው በቅንነት ስለሚያስቡ ሊሆን ይችላል።”

እውነቱን ለመናገር ግን አንዳንድ ጊዜ አማቶች በልጆቻቸው ትዳር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡት ተጠይቀው ሊሆን ይችላል። በአውስትራሊያ የሚኖሩትን ማይክልና ሊያን የተባሉ ባልና ሚስት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ማይክል እንዲህ ይላል፦ “ሊያን ያደገችው ሁሉን ነገር በግልጽ በሚነጋገርና እርስ በርሱ በጣም በሚቀራረብ ቤተሰብ ውስጥ ነው። በመሆኑም ከተጋባን በኋላ እኔና እሷ ብቻ ተነጋግረን ልንወስነው የሚገባንን ጉዳይ አባቷን ታማክራለች። አባቷ ብዙ ተሞክሮ እንዳለው አልክድም፤ ግን እኔን ከማማከር ይልቅ እሱን ማማከሯ በጣም ያበሳጨኛል!”

 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ባልና ሚስት ከአማቶቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በትዳራቸው ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። እናንተስ በትዳራችሁ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟችኋል? አንተ ከትዳር ጓደኛህ ወላጆች ጋር ያለህ ግንኙነት ባለቤትህ ደግሞ ከአንተ ወላጆች ጋር ያላት ግንኙነት ምን ይመስላል? በትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁለት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲሁም እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ምን ማድረግ እንደምትችሉ እስቲ እንመልከት።

አንደኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፦

የትዳር ጓደኛህ ከወላጆቿ ጋር በጣም እንደምትቀራረብ ይሰማህ ይሆናል። በስፔን የሚኖር ሉዊስ የተባለ አንድ ባል እንዲህ ይላል፦ “ባለቤቴ ወላጆቿ አካባቢ ካልኖርን እንደካደቻቸው ይሰማታል። በሌላ በኩል ደግሞ ወንድ ልጃችን በተወለደበት ወቅት ወላጆቼ በየቀኑ ማለት ይቻላል ከቤታችን አይጠፉም ነበር፤ ይህ ደግሞ በባለቤቴ ላይ ውጥረት ፈጥሮባት ነበር። በዚህም ምክንያት በየጊዜው እንጋጭ ነበር።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች፦

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ካገባ በኋላ የሚሆነውን ነገር አስመልክቶ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:24) “አንድ ሥጋ” መሆን ሲባል አንድ ላይ መኖር ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ባልና ሚስቱ አዲስ ቤተሰብ ስለመሠረቱ ለዚህ ቤተሰብ ካደጉበት ቤተሰብ የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) እርግጥ ባልም ሆነ ሚስት ወላጆቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለእነሱ ትኩረት መስጠትን ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:2) ታዲያ የትዳር ጓደኛህ ለወላጆቿ የምትሰጠው ትኩረት እንደተተውክ ወይም ችላ እንደተባልክ እንዲሰማህ ቢያደርግስ?

ማድረግ የምትችሉት ነገር፦

ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት ሞክሩ። የትዳር ጓደኛህ በእርግጥ ከወላጆቿ ጋር ከመጠን በላይ ትቀራረባለች ወይስ ችላ እንደተባልክ የተሰማህ አንተ ከወላጆችህ ጋር እምብዛም ስለማትቀራረብ ይሆን? ይህ ከሆነ አስተዳደግህ ለሁኔታው ባለህ አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? እንዲህ ያለ አመለካከት የያዝከው ምናልባት ቅናት ቢጤ ስለተሰማህ ይሆን?—ምሳሌ 14:30፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4፤ ገላትያ 5:26

ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ራስን በሐቀኝነት መመርመር ያስፈልጋል። እንዲህ ማድረጋችሁ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው። ከአማቶቻችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት አንተንና ባለቤትህን ነጋ ጠባ የሚያጨቃጭቃችሁ ከሆነ ችግሩ ያለው በእነሱና በእናንተ መካከል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በትዳራችሁ ውስጥ ችግር አለ ማለት ነው።

ብዙውን ጊዜ በትዳር ውስጥ ችግር የሚነሳው የትኛውም ባልና ሚስት በአንድ ጉዳይ ላይ ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት ስለማይኖራቸው ነው። ነገሮችን በትዳር ጓደኛህ ዓይን ለማየት ትሞክራለህ? (ፊልጵስዩስ 2:4፤ 4:5) በሜክሲኮ የሚኖረው አድሪያን እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው። እንዲህ ይላል፦ “ባለቤቴ ያደገችው በስሜቷ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ በሚያሳድር ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ በመሆኑም ከቤተሰቦቿ ጋር በጣም ላለመቀራረብ እጠነቀቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረኝ ወሰንኩ፤ በዚህ ሁኔታ ለዓመታት ቀጠልን። ይህ ደግሞ በእኔና በባለቤቴ መካከል ግጭት እንዲፈጠር አደረገ፤ ምክንያቱም ባለቤቴ ከቤተሰቧ በተለይም ከእናቷ ጋ መቀራረብ ትፈልግ ነበር።”

ከጊዜ በኋላ አድሪያን በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ አመለካከት ያዘ። እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ባለቤቴ ከወላጆቿ ጋር በጣም መቀራረቧ በስሜቷ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባት ባውቅም ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግም ችግር እንደሚያስከትል ተገነዘብኩ። በዚህም ምክንያት በተቻለኝ መጠን ከአማቶቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ለማደስ ብሎም ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ ለማድረግ መጣር ጀመርኩ።” *

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ አንተና ባለቤትህ ከአማቶቻችሁ ጋር በተያያዘ አሳሳቢ ናቸው የምትሏቸውን ነገሮች ጻፉ። ከቻላችሁ “እኔ እንደሚሰማኝ ከሆነ . . .” በማለት ጀምሩ፤ ከዚያም ወረቀቱን ተለዋወጡ። የሚያሳስቧችሁን ነገሮች ለመፍታት የሚያስችል ዘዴ ለማግኘት አንድ ላይ ሆናችሁ መግባባት በሰፈነበት መንፈስ ተወያዩ።

ሁለተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፦

አማቶቻችሁ ማንም ሳይጠይቃቸው በትዳራችሁ ውስጥ ሁልጊዜ ጣልቃ ይገቡ ይሆናል። በካዛክስታን የምትኖረው ኔልያ እንዲህ ትላለች፦ “ትዳር ከመሠረትን በኋላ የመጀመሪያዎቹን ሰባት ዓመታት የኖርነው ከባለቤቴ ቤተሰቦች ጋር ነበር። ልጆቻችንን  ከምናሳድግበት መንገድ እንዲሁም ከምግብ አሠራሬና ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ሁልጊዜ ግጭት ይፈጠር ነበር። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ባለቤቴንና እናቱን አነጋገርኳቸው፤ ይሁን እንጂ መነጋገራችን ችግሩን ከማባባስ ውጭ የፈየደው ነገር የለም።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች፦

ካገባችሁ በኋላ በወላጆቻችሁ ሥልጣን ሥር መሆናችሁ ያከትማል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” ማለትም ባሏ እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ያም ሆኖ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ባልም ሆነ ሚስት ወላጆቻቸውን ማክበር አለባቸው። እንዲያውም ምሳሌ 23:22 “የወለደህን አባትህን አድምጥ፤ እናትህንም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” በማለት ይናገራል። ይሁንና ወላጆችህ ወይም የባለቤትህ ወላጆች ገደባቸውን አልፈው አመለካከታቸውን በእናንተ ላይ ለመጫን ቢሞክሩ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?

ማድረግ የምትችሉት ነገር፦

ወላጆቻችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ያደረጋቸውን ምክንያት ለመረዳት ሞክሩ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ራየን “አንዳንድ ጊዜ ወላጆች አሁንም ድረስ በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ቦታ እንዳላቸው ማወቅ ይፈልጋሉ” ብሏል። ወላጆቻችሁ እንዲህ የሚያደርጉት ሆን ብለው ላይሆን ስለሚችል “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ብቻ እንኳ ችግሩን ሊፈታው ይችላል። (ቆላስይስ 3:13) ይሁንና ወላጆቻችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው በአንተና በባለቤትህ መካከል ከባድ ግጭት የሚያስከትል ቢሆንስ?

አንዳንድ ባልና ሚስት ከወላጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ተገቢ የሆነ ገደብ ማበጀታቸው ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ይህ ሲባል ግን ሕግ ታወጡላቸዋላችሁ ማለት አይደለም። * ብዙውን ጊዜ በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጡት ለትዳር ጓደኛችሁ እንደሆነ በምታደርጓቸው ነገሮች በግልጽ ማሳየት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በጃፓን የሚኖረው ማሳዩኪ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ወላጆቻችሁ አመለካከታቸውን ሲገልጹላችሁ ወዲያውኑ በሐሳባቸው አትስማሙ። አዲስ ቤተሰብ እየገነባችሁ መሆኑን አስታውሱ። በመሆኑም በመጀመሪያ የትዳር ጓደኛችሁ ስለ ምክሩ ምን አመለካከት እንዳለው ለማወቅ ጣሩ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ወላጆቻችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው በሁለታችሁ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ ተነጋገሩ። በወላጆቻችሁ ላይ ምን ገደብ መጣል እንደምትችሉና ይህንን ገደብ እንዴት ማክበር እንደምትችሉ አንድ ላይ ተቀምጣችሁ ጻፉ፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ወላጆቻችሁን እንደምታከብሩ ማሳየት አለባችሁ።

ከወላጆቻችሁ ጋር የሚፈጠሩትን ብዙዎቹን አለመግባባቶች አንድም የእነሱን ዓላማ በመረዳት በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ያሉት አለመግባባቶች ሁለታችሁን እንዲያጋጯችሁ ባለመፍቀድ መፍታት ይቻላል። ጄኒ ይህን ጉዳይ በሚመለከት የሚከተለውን ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ እኔና ባለቤቴ ስለ ወላጆቻችን ስንነጋገር ስሜታዊነት ያጠቃናል፤ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ስለ ወላጆቻችን ጉድለት አንስተን መነጋገራችን ስሜታችንን ከመጉዳት ሌላ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተገነዘብን። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የወላጆቻችንን ጉድለት እንደ ማጥቂያ መሣሪያ ከመጠቀም ይልቅ በችግሩ ላይ ማነጣጠራችን ጠቃሚ እንደሆነ ተረዳን። ይህ ሁኔታ እኔንና ባለቤቴን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አቀራረበን።”

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.14 ወላጆች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከባድ ኃጢአት የሚፈጽሙና ንስሐ የማይገቡ ከሆነ ይህ ሁኔታ በቤተሰቡ ግንኙነት ላይ ውጥረት ስለሚፈጥር ግንኙነታቸውን በገደብ ማድረግ እንዳለባቸው የታወቀ ነው።—1 ቆሮንቶስ 5:11

^ አን.19 አንዳንድ ጊዜ ከወላጆቻችሁ ወይም ከአማቶቻችሁ ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ካለባችሁ አነጋገራችሁ አክብሮትና ገርነት የሚንጸባረቅበት መሆን አለበት።—ምሳሌ 15:1፤ ኤፌሶን 4:2፤ ቆላስይስ 3:12

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .

  • አማቶቼ ምን ግሩም ባሕርያት አሏቸው?

  • የትዳር ጓደኛዬን ችላ ሳልል ለወላጆቼ አክብሮት ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?