በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰማይ ምን ይመስላል?

ሰማይ ምን ይመስላል?

 ሰማይ ምን ይመስላል?

አንዳንድ ሰዎች ስለ ሰማይ ሊነግረን የሚችል ከዚያ የመጣ ሰው ስለሌለ ስለ ሰማይ ማወቅ አይቻልም ብለው ያስባሉ። ምናልባት እንዲህ የሚሉት ኢየሱስ “ከሰማይ የመጣሁት . . . የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ዘንግተው ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 6:38) ኢየሱስ ለአንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 8:23) ታዲያ ኢየሱስ ስለ ሰማይ ምን ተናግሯል?

ኢየሱስ ሰማይ ይሖዋ የሚኖርበት ቦታ እንደሆነ ተናግሯል። አምላክን ‘በሰማይ ያለው አባቴ’ በማለት ጠርቶታል። (ማቴዎስ 12:50) ሆኖም ኢየሱስ “ሰማይ” የሚለውን ቃል ሌላ ነገር ለመግለጽም ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል፣ “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ” ብሎ በተናገረው ሐሳብ ላይ “ሰማይ” የሚለው ቃል የምድርን ከባቢ አየር ያመለክታል። (ማቴዎስ 6:26) ያም ሆኖ ይሖዋ የሚኖረው ከምድር ከባቢ አየር እጅግ ርቆ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ ከምድር ክበብ በላይ . . . ይቀመጣል” ይላል።—ኢሳይያስ 40:22

‘በሰማይ ያለው አባታችን’ የሚኖረው በከዋክብት መካከል ነው? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አጽናፈ ዓለምም “ሰማይ” ተብሎ ተጠርቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ መዝሙራዊ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?”—መዝሙር 8:3, 4

አንድ አናጢ በሠራው ቁም ሣጥን ውስጥ ይኖራል ብለን እንደማንጠብቀው ሁሉ ይሖዋ አምላክም በፈጠረው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ይኖራል ብለን አንጠብቅም። በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ወቅት እንደሚከተለው ብሏል፦ “አምላክ በእርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ!” (1 ነገሥት 8:27) ይሖዋ በግዑዙ ሰማይ ውስጥ የማይኖር ከሆነ ታዲያ እሱ የሚኖርበት ሰማይ የትኛው ነው?

ሰዎች በጣም በረቀቁ ቴሌስኮፖች ታግዘው ስለ ግዑዙ ሰማይ ማጥናት ችለዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ሕዋ ተጉዘዋል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” በማለት የተናገረው ሐቅ አልተለወጠም። (ዮሐንስ 1:18) ኢየሱስ አምላክ የማይታይበትን ምክንያት ሲገልጽ “አምላክ መንፈስ ነው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 4:24

መንፈስ፣ ሰዎች ካላቸው ሕይወት የላቀ የሕይወት ዓይነት ነው። መንፈስ በሰዎች የስሜት ሕዋሳት ሊታይ ወይም ሊዳሰስ በሚችል እንደ ሥጋና ደም ባለ ቁስ አካል የተዋቀረ አይደለም። በመሆኑም ኢየሱስ “በሰማይ” ካለው አባቱ ጋር ይኖር እንደነበር ሲናገር ማንኛውም ሥጋዊ አካል ካለው ሕይወት ይበልጥ ክቡር የሆነ የሕይወት ዓይነት እንደነበረው መናገሩ ነው። (ዮሐንስ 17:5፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21) መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማይ” በማለት የጠራው፣ ኢየሱስ መንፈስ ሆኖ ይኖርበት የነበረውን እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ዓለም ነው። ታዲያ ይህ ቦታ ምን ይመስላል? እዚያስ ምን ይከናወናል?

 አስደሳች እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት ቦታ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰማይ በርካታ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት ቦታ እንደሆነ ይገልጻል። በዚያ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንዳሉ ይናገራል። (ዳንኤል 7:9, 10) እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት እያንዳንዳቸው አንዱን ከሌላው ልዩ የሚያደርገው የራሳቸው የሆነ ባሕርይ አላቸው። ይህን እንዴት እናውቃለን? በምድር ላይ ያሉትን ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ስንመለከት በሁሉም ነገር ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ፍጥረታት የሉም፤ ከዚህ በመነሳት በሰማይም ቢሆን አንዱ ፍጥረት ከሌላው እንደሚለይ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። የሚገርመው እነዚህ የተለያዩ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሙሉ በአንድነት ተቀናጅተው ይሠራሉ፤ ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ተባብሮ መሥራት እምብዛም በማይታይበት በምድር ላይ ካለው ሁኔታ ፍጹም ተቃራኒ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚገልጸው ልብ በል። “እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፤ ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤ እግዚአብሔርን ባርኩ። እናንተ ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ፤ ሰራዊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።” (መዝሙር 103:20, 21) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በሰማይ ላይ ብዙ ሥራ እየተከናወነ ነው። ይህ ሥራ አስደሳች እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

መላእክት ምድር ከመፈጠሯ በፊት እንኳ አስደሳች ሥራ ያከናውኑ ነበር። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር የአምላክ ልጆች ‘ዘምረዋል እንዲሁም እልል ብለዋል።’ (ኢዮብ 38:4, 7) እንዲያውም በሰማይ ከሚኖሩት የአምላክ ልጆች አንዱ ሌሎች ነገሮች በሙሉ በተፈጠሩበት ጊዜ ከአምላክ ጋር የመሥራት መብት አግኝቷል። (ቆላስይስ 1:15-17) በሰማይ ስለሚከናወነው አስደሳች እንቅስቃሴ የሚናገረው ይህ ግሩም ሐሳብ ስለ ሰማይም ሆነ ስለ ሰው ልጆች በአእምሮህ ውስጥ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርግ ይሆናል።

ሰዎች የተፈጠሩት ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ነበር?

መላእክት ምድር ከመፈጠሯ በፊት አምላክን ያገለግሉ ስለነበር የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት የተፈጠሩት በሰማይ እንዲኖሩ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” ብሏቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28፤ የሐዋርያት ሥራ 17:26) አዳም አምላክን የማወቅና በታማኝነት የማገልገል ችሎታ ያለው የመጀመሪያው ምድራዊ ፍጡር ሆነ። እሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ዘሮች አባት የመሆን መብት ተሰጠው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል።—መዝሙር 115:16

ሰዎች በተፈጥሯቸው መሞት አይፈልጉም፤ ሞት ለሰዎች ተፈጥሯዊ ነገር አይደለም። አምላክ ሞትን የጠቀሰው አዳም ካልታዘዘ እንደሚቀጣ በተናገረበት ጊዜ ነው። አዳም ታዝዞ ቢሆን ኖሮ ፈጽሞ አይሞትም ነበር።—ዘፍጥረት 2:17፤ ሮም 5:12

አምላክ ለአዳም ወደ ሰማይ ስለ መሄድ ምንም አለመናገሩ የሚያስገርም አይደለም። ስለሆነም ምድር የተፈጠረችው ሰዎች በሰማይ ለሚኖራቸው ሕይወት ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መፈተኛ ቦታ እንድትሆን ታስቦ አይደለም። ሰዎች የተፈጠሩት በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው፤ ይህ የአምላክ ዓላማ ገና አልተፈጸመም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 37:29) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ሰዎች የተፈጠሩት ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ታስቦ አልነበረም። ታዲያ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ቃል የገባላቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ይህን ሲል ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ መናገሩ ነበር?