በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አንድ ብቻ ልድገም”

“አንድ ብቻ ልድገም”

 “አንድ ብቻ ልድገም”

አለን አልኮል ከልክ በላይ መጠጣት የጀመረው የ11 ዓመት ልጅ እያለ ነበር። * እሱና ጓደኞቹ በፊልም ላይ ያዩአቸውን ገጸ ባሕርያት እያስመሰሉ ጫካ ውስጥ ይጫወቱ ነበር። አለንና ጓደኞቹ የሚወክሏቸው ገጸ ባሕርያት ፈጠራ ነበሩ፤ የሚጠጡት መጠጥ ግን እውነተኛ ነበር።

ቶኒ የ40 ዓመት ሰው ሳለ ማታ ማታ አንድ ሁለት እያለ የጀመረው መጠጥ ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቶ ወደ አምስትና ስድስት ብርጭቆ ደርሶ ነበር። ውሎ አድሮ ግን በቀን ውስጥ ምን ያህል እንደጠጣ ይጠፋበት ጀመር።

አለን የመጠጥ ችግሩን ለማሸነፍ የተደረገለትን እርዳታ ተቀበለ። ቶኒ ግን አሳቢ የሆኑ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ያቀረቡለትን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በአሁኑ ጊዜ አለን በሕይወት ተርፎ ታሪኩን ለመናገር በቅቷል፤ ቶኒ ግን ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከልክ በላይ ጠጥቶ ሞተር ብስክሌት ሲነዳ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል።

አንድ ሰው ከልክ በላይ ሲጠጣ የሚጎዳው ራሱን ብቻ አይደለም፤ ጦሱ ለሌላም ሰው ይተርፋል። * አልኮል አላግባብ የሚጠጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በስካር መንፈስ ይሳደባሉ፣ በሌሎች ላይ አካላዊ ጥቃት ያደርሳሉ፣ ሰዎችን ያስፈራራሉ ሌላው ቀርቶ የሰው ሕይወት ያጠፋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከመጠን በላይ መጠጣት ለመኪና አደጋም ሆነ በሥራ ቦታ ለሚደርስ ጉዳት እንዲሁም ለበርካታ የጤና ችግሮች መንስኤ ሲሆን ይታያል። አልኮል አላግባብ መጠጣት በየዓመቱ በኅብረተሰቡ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ያስከትላል፤ በግለሰቦች፣ በቤተሰቦችና በልጆች ላይ የሚደርሰውን አካላዊና ስሜታዊ ቀውስ ቤቱ ይቁጠረው።

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋማት እንደገለጹት ከሆነ “ዘወትር የሚጠጣ ሰው ሁሉ የመጠጥ ችግር ላይኖርበት ይችላል፤ የመጠጥ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁሉ ደግሞ በየቀኑ ይጠጣሉ ማለት አይደለም።” የመጠጥ ሱስ የሌለባቸው በርካታ ሰዎች ሳይታወቃቸው ብዙ መጠጣት ልማድ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የሚጠጡት ከስንት አንዴ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በአንድ ጊዜ ብቻ ከአምስት ብርጭቆ በላይ ይጠጣሉ።

አልኮል መጠጣት የምትፈልግ ከሆነ ከመጠን በላይ ጠጥተሃል የሚባለው ምን ያህል ብትጠጣ ነው? ‘አንድም እንኳ መድገም’ የማያስፈልግህ ደረጃ ላይ እንደደረስክ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 23:29, 30 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ቀጣዮቹ ርዕሶች ይህን ጉዳይ በሚመለከት ጠቃሚ መረጃ ይዘዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.5 ወንዶች የአልኮል ሱሰኛ የመሆናቸው አጋጣሚ ከሴቶች በአራት እጥፍ ሊበልጥ ስለሚችል በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ላይ በተባዕታይ ፆታ ተጠቅመናል። ይሁንና ትምህርቱ ለወንዶችም ለሴቶችም ይሠራል።