ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ በቤተልሔም እንዲወለድ ምክንያት የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ዓላማው ምን ነበር?

በሉቃስ ወንጌል ዘገባ መሠረት አውግስጦስ ቄሳር በመላው የሮም ግዛት የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ ባወጣ ጊዜ “ሁሉም ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።” (ሉቃስ 2:1-3) የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የዮሴፍ የትውልድ ከተማ ደግሞ ቤተልሔም ስለሆነ ዮሴፍና ማርያም ይህን አዋጅ በመታዘዝ ለመመዝገብ ወደዚያ ተጓዙ፤ ኢየሱስም በቤተልሔም ሳሉ ተወለደ። ይህ ዓይነቱ ምዝገባ ለሮም መንግሥት ቀረጥ መሰብሰብ እንዲሁም ለውትድርና ምልመላ ማካሄድ ቀላል እንዲሆንለት አስችሏል።

ሮማውያን በ30 ዓ.ዓ. ግብፅን በተቆጣጠሩበት ጊዜ እንዲህ ያለው የሕዝብ ቆጠራ በግብፅ ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት የቆየ የመንግሥት አሠራር ነበር። ሮማውያንም ይህንን አሠራር ከግብፃውያን በመኮረጅ በተቆጣጠሯቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ እንዳደረጉ ምሑራን ይናገራሉ።

በግብፅ ያስተዳድር የነበረው ሮማዊ አገረ ገዥ በ104 ዓ.ም. ያወጣው አዋጅ፣ እንዲህ ያለ የሕዝብ ቆጠራ ወይም ምዝገባ ይካሄድ እንደነበር ማስረጃ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው የዚህ አዋጅ ቅጂ እንዲህ ይላል፦ “የግብፅ አገረ ገዥ የሆነው ጋይየስ ቪቢየስ ማክሲመስ (እንዲህ ይላል)፦ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበት ጊዜ ስለደረሰ በተለያዩ ምክንያቶች በሌላ አውራጃ የሚገኙ ሁሉ የተለመደውን የሕዝብ ቆጠራ ትእዛዝ ለመፈጸም እንዲሁም መሬታቸውን በሚገባ ለማልማት ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኗል።”

ዮሴፍ ማርያምን ሳያገባት የፍቺ ወረቀት ሊሰጣት ያሰበው ለምንድን ነው?

በማቴዎስ ወንጌል ዘገባ መሠረት ማርያም ‘ለዮሴፍ ታጭታ በነበረበት ጊዜ፣’ አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት ዮሴፍ መፀነሷን ተረዳ። ዮሴፍ ማርያም የፀነሰችው “በመንፈስ ቅዱስ” መሆኑን ስላላወቀ ለቃል ኪዳኗ ታማኝ ሳትሆን እንደቀረች አድርጎ ሳያስብ አልቀረም፤ በመሆኑም ሊፈታት አሰበ።—ማቴዎስ 1:18-20

አይሁዳውያን፣ የተጫጩ ወንድና ሴትን እንደተጋቡ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ እስኪከናወን ድረስ እንደ ባልና ሚስት አብረው መኖር አይጀምሩም። መተጫጨት ጽኑ ቃል ኪዳን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ወንዱ ሐሳቡን በመቀየሩ ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ጋብቻው ሳይፈጸም ቢቀር ሴቷ የፍቺ ወረቀት እስክታገኝ ድረስ ለማግባት ነፃ አትሆንም። እንዲሁም ከሠርጋቸው ቀን በፊት ወንዱ ቢሞት እንደ መበለት ትቆጠር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ታጭታ እያለች ዝሙት ከፈጸመች እንደ አመንዝራ ተቆጥራ የሞት ቅጣት እንድትቀበል ይደረግ ነበር።—ዘዳግም 22:23, 24

ማርያም ማርገዟን ሰው ቢያውቅ የሚገጥማትን ነገር ዮሴፍ በደንብ እንዳሰበበት ጥርጥር የለውም። ዮሴፍ ለሚመለከታቸው ሰዎች ስለ ሁኔታው መናገር እንዳለበት ተሰምቶት የነበረ ቢሆንም ማርያምን ሊደርስባት ከሚችለው ጉዳት መጠበቅና አሉባልታ እንዳይናፈስ ማድረግ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም በስውር ሊፈታት አሰበ። ነጠላ የሆነች እናት የፍቺ ወረቀት ያላት መሆኑ ቀደም ሲል አግብታ እንደነበር የሚያሳይ ይሆናል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግብፅ ያስተዳድር የነበረው ሮማዊ አገረ ገዥ ያወጣው የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ፣ 104 ዓ.ም.

[ምንጭ]

© The British Library Board, all rights reserved (P.904)