የጨረቃ አዲስ ዓመት​—ክርስቲያኖች ሊያከብሩት ይገባል?

የጨረቃ አዲስ ዓመት​—ክርስቲያኖች ሊያከብሩት ይገባል?

የጨረቃ አዲስ ዓመት​—ክርስቲያኖች ሊያከብሩት ይገባል?

እስያ በየዓመቱ በጥር ወይም በየካቲት ወር ላይ በዓለም ላይ ካሉ አህጉራት ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን እንግዶች ታስተናግዳለች። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስያውያን የጨረቃን አዲስ ዓመት * ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደ ትውልድ አገራቸው ይጎርፋሉ።

የጨረቃ አዲስ ዓመት በእስያውያን የቀን አቆጣጠር ትልቅ ግምት የሚሰጠው በዓል ነው። አንድ አሜሪካዊ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “[በዓሉ] የአውሮፓውያንን አዲስ ዓመት፣ የአሜሪካንን የነፃነት ቀን፣ የታንክስጊቪንግ ቀንንና የገና በዓልን አጠቃሎ የያዘ ነው ማለት ይቻላል።” ይህ በዓል መከበር የሚጀምረው በቻይናውያን የጨረቃ አቆጣጠር የመጀመሪያዋ አዲስ ጨረቃ ስትወጣ ወይም በምዕራባውያን የቀን አቆጣጠር ከጥር 21 እስከ የካቲት 20 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። በዓሉ ለቀናት ወይም እስከ ሁለት ሳምንት ለሚያህል ጊዜ ይከበራል።

ይህ አዲስ ዓመት በዋነኝነት የሚከበረው አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ለመቀበል ነው። ሰዎች ቤታቸውን በማጽዳትና በማስዋብ፣ አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት፣ ምግብ አዘጋጅተው “መልካም ዕድል” ወይም “ብልጽግና” ብለው በመሰየም፣ ዕዳቸውን በመክፈል እንዲሁም ከተጣሉት ሰው ጋር በመታረቅ በዓሉን ለማክበር ዝግጅት ያደርጋሉ። አዲሱ ዓመት በሚከበርበት ዕለት ሰዎች ስጦታና የመልካም ምኞት (ብዙውን ጊዜ ሀብትና ብልጽግና በመመኘት) መግለጫዎችን ይለዋወጣሉ፣ ለገድ እንዲሆን ገንዘብ የያዘ ትንሽ ቀይ ከረጢት ይሰጣጣሉ፣ ልዩ ምግቦችን አዘጋጅተው ይመገባሉ፣ ርችቶችን ይተኩሳሉ፣ በቀለማት ያሸበረቁ የዘንዶ ወይም የአንበሳ ምስል ለብሰው የሚጨፍሩ ሰዎችን ይመለከታሉ አሊያም ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በዓሉን ያከብራሉ።

በዚህ ወቅት የሚደረገው እያንዳንዱ ነገር የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። ሙንኬክስ ኤንድ ሃንግሪ ጎስትስ፦ ፌስቲቫልስ ኦቭ ቻይና የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ዋነኛ ፍላጎታቸው መልካም ዕድልን መመኘት፣ ለአማልክትና ለመናፍስት አክብሮት መስጠትና ለመጪው ዓመት መልካም ምኞታቸውን መግለጽ ነው።” ይህ በዓል በሚከበርበት ወቅት በርካታ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፤ ታዲያ ክርስቲያኖች ለዚህ በዓል ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በባሕሉ መሠረት የሚደረገውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው? ክርስቲያኖች ይህን በዓል ሊያከብሩ ይገባል?

“ምንጩን አስታውስ”

“ውኃ ስትጠጣ ምንጩን አስታውስ” የሚል አንድ የታወቀ የቻይናውያን አባባል አለ። ይህ አባባል በርካታ እስያውያን ወላጆቻቸውንና ቅድመ አያቶቻቸውን በጥልቅ የማክበር ባሕል እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። በአዲስ ዓመት በዓል ወቅት ወላጆችን ማክበር ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፤ እርግጥ ነው፣ ወደዚህ ዓለም ያመጧቸው ወላጆቻቸው በመሆናቸው ልጆች እንዲህ ያለ አክብሮት ማሳየታቸው የሚጠበቅ ነው።

በአዲስ ዓመት በዓል ወቅት ብዙ እስያውያን ቤተሰቦች ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ለዋዜማው ነው። በበዓሉ ዋዜማ ምሽት አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለየት ያለ እራት አዘጋጅተው አንድ ላይ ሆነው ይመገባሉ። በዓሉ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ላይ የሚሰባሰብበት አጋጣሚ ስለሚፈጥር ሁሉም ሰው በዚያ ምሽት ለመገኘት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በገበታው ዙሪያ ቦታ የሚዘጋጀው እዚያ ለሚገኙ የቤተሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ይገኛሉ ተብለው ለሚታሰቡት በሞት ለተለዩ የቤተሰቡ አባላት ጭምር ነው። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ በዚህ እራት ላይ “የቤተሰቡ አባላት ከሞቱ ዘመዶቻቸው ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ ይፈጠራል” በማለት ገልጿል። አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ደግሞ “በሕይወት ባሉትና በሙታን መካከል ያለው ግንኙነት ስለሚታደስ የሞቱት ዘመዶች ዓመቱን ሙሉ ለቤተሰቡ ጥበቃ ያደርጋሉ” በማለት ተናግሯል። ታዲያ ክርስቲያኖች ለዚህ ልማድ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

ወላጅን ማክበርና መውደድ በክርስቲያኖችም ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። ክርስቲያኖች “የወለደህን አባትህን አድምጥ፤ እናትህንም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” የሚለውን መለኮታዊ መመሪያ ይከተላሉ። (ምሳሌ 23:22) በተጨማሪም የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይታዘዛሉ፦ “‘አባትህንና እናትህን አክብር’፤ ይህ የተስፋ ቃል ያለው የመጀመሪያ ትእዛዝ ነው፦ ‘ይህም መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ያደርጋል።’” (ኤፌሶን 6:2, 3) አዎን፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ወላጆቻቸውን የመውደድና የማክበር ፍላጎት አላቸው!

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰቦች እርስ በርስ ለመተናነጽ አንድ ላይ ስላሳለፉት ጊዜ በተደጋጋሚ ይናገራል። (ኢዮብ 1:4፤ ሉቃስ 15:22-24) ያም ሆኖ ይሖዋ “መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ” በማለት አዟቸዋል። (ዘዳግም 18:10, 11) እንዲህ ያለው ትእዛዝ የተሰጠው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ያሉበትን ትክክለኛ ሁኔታ ይናገራል። “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል። ሙታን ምንም ነገር ስለማያውቁ ሕያዋን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ መካፈል አይችሉም፤ እንዲሁም ሕያዋንን ሊጠቅሙም ሆነ ሊጎዱ አይችሉም። (መክብብ 9:5, 6, 10) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ሙታን ከእንቅልፋቸው የሚነቁት ወደፊት ትንሣኤ በሚከናወንበት ጊዜ ብቻ ነው።—ዮሐ. 5:28, 29፤ 11:11, 14

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የሙታንን “መናፍስት” መስለው ለመቅረብ የሚጥሩት ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንደሆኑ ይገልጻል። እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ሰዎችን ለማሳሳትና በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ነው! (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) የአምላክ ትእዛዛት ጉዳት ከሚያደርሱብን አደገኛ ሁኔታዎች ይጠብቁናል። ስለሆነም ክርስቲያኖች ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር እንዲሁም ከአደጋ ለመጠበቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከሙታን “መናፍስት” አምልኮ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ወይም የሞቱ ዘመዶችን ጥበቃ ለማግኘት ተብለው ከሚደረጉ ከማንኛውም ልማዶች መራቃቸው የጥበብ እርምጃ ነው።—ኢሳይያስ 8:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 10:20-22

በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያኖች “በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜውን ያገኘው [ከአብ]” ስለሆነ እሱን ማክበር ይፈልጋሉ። (ኤፌሶን 3:14, 15) እዚህ ላይ አብ የተባለው ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) በመሆኑም ከጨረቃ አዲስ ዓመት አከባበር ጋር የተያያዙ ልማዶችን ስንመረምር እንዲህ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ይሖዋ እነዚህን ልማዶች እንዴት ይመለከታቸዋል? በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው?’—1 ዮሐንስ 5:3

ለቤተሰብ አማልክት ክብር መስጠት

ከጨረቃ አዲስ ዓመት አከባበር ጋር በተያያዘ በሰፊው ከሚዘወተሩት ልማዶች መካከል ለበር አምላክ፣ ለምድር አምላክ ወይም ለጠባቂ መንፈስ፣ ለሀብት ወይም ለዕድል አምላክ እንዲሁም ለኩሽና ወይም ለምድጃ አምላክ ለመሳሰሉት በርካታ የቤተሰብ አማልክት ክብር መስጠት ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ለኩሽና አምላክ የሚሰጠውን ክብር እንመልከት። * አዲስ ዓመት ከመከበሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ይህ አምላክ ስለ ቤተሰባቸው ሁኔታ ከቻይና አማልክት ሁሉ ለሚበልጠው ለንጉሠ ነገሥት ጄድ ሪፖርት ለማቅረብ ወደ ሰማይ ይሄዳል ተብሎ ይታመናል። ይህ የኩሽና አምላክ ስለ ቤተሰቡ ሁኔታ ጥሩ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው ሲሉ እንደ መሥዋዕት የሚቀርቡ ጣፋጭ ምግቦችንና ብስኩቶችን ጨምሮ ልዩ የሆነ ምግብ አዘጋጅተው ይልኩታል። ቤተሰቡ የዚህ አምላክ ጉዞ ፈጣን እንዲሆን ያላቸውን ምኞት ለመግለጽ ሥዕሉን ከተሰቀለበት በማውረድ አንዳንድ ጊዜ ጣፋጭ ምግቡን ከንፈሩ ላይ በመቀባት ውጭ አውጥተው ያቃጥሉታል። በአዲሱ ዓመት ዋዜማ፣ ይህ አምላክ በቀጣዩ ዓመት ወደ ቤታቸው ተመልሶ እንዲመጣ ለመጋበዝ አዲስ ሥዕል ከኩሽናው ምድጃ በላይ ይሰቅላሉ።

በርካታ ልማዶች ችግር ያለባቸው ባይመስሉም ክርስቲያኖች አምልኮን በተመለከተ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛት መከተል ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ብሏል። (ማቴዎስ 4:10) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው አምላክ እሱን ብቻ እንድናመልክ ይፈልጋል። ለምን? ይሖዋ በሰማይ የሚገኝ አባታችን እንደሆነ ልብ በል። አንድ አባት ልጆቹ እሱን ችላ ብለው ወደ ሌላ አባት ቢሄዱ ምን ይሰማዋል? ይህ አባት በሁኔታው በጣም አያዝንም?

ኢየሱስ በሰማይ የሚገኘውን አባቱን “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” በማለት ጠርቶታል፤ ይሖዋ ራሱ አምላኪዎቹን ከእሱ በቀር ‘ሌሎች አማልክት እንዳይኖሯቸው’ በግልጽ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 17:3፤ ዘፀአት 20:3) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋን ማስደሰት እንጂ ሌሎች አማልክትን በማገልገል እሱን ማሳዘን አይፈልጉም።—1 ቆሮንቶስ 8:4-6

አጉል እምነቶችና መናፍስታዊ ድርጊቶች

የጨረቃ አዲስ ዓመት በዓል ከኮከብ ቆጠራ ጋር የተቆራኘ ነው። በጨረቃ የቀን አቆጣጠር እያንዳንዱ ዓመት በቻይናውያን የዞዲያክ ምልክቶች ላይ ካሉት እንደ ዘንዶ፣ ነብር፣ ጦጣና ጥንቸል ከመሳሰሉት 12 እንስሳት መካከል በአንዱ ይሰየማል። በአንድ እንስሳ በተሰየመ ዓመት የተወለዱ ሰዎች የዚያ እንስሳ ባሕርይ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል፤ አሊያም እነዚህ ሰዎች በዚያ ዓመት ያቀዷቸው ነገሮች እንደሚሳኩ ሆኖ ይሰማቸዋል። ለሀብት ወይም ለዕድል አምላክ የሚሰጠውን ክብር ጨምሮ ከጨረቃ አዲስ ዓመት አከባበር ጋር የተያያዙ ሌሎች በርካታ ልማዶች አንድ ግለሰብ መልካም “ዕድል” እንዲገጥመው ታስበው የሚከናወኑ ናቸው። ታዲያ ክርስቲያኖች እነዚህን ልማዶች እንዴት ሊመለከቷቸው ይገባል?

ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “በሰማያት ያሉ ነገሮችን የሚያመልኩ፣ ከዋክብትን የሚመለከቱ፣ አዲስ ጨረቃም በወጣች ቁጥር [በእነሱ] ላይ ስለሚመጣው ነገር የሚተነብዩ” ሰዎችን ገሥጿቸዋል። ‘ዕጣ ፈንታና ዕድል ለተባሉት ጣዖታት’ የሚቀርበውን አምልኮም አውግዟል። (ኢሳይያስ 47:13 NW፤ 65:11, 12) እውነተኛ አምላኪዎች ከመንፈሳዊ ዓለም ወይም ከከዋክብት ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብለው በሚታመኑ ሚስጥራዊ ወይም የማይታዩ አካላት አይታመኑም፤ ከዚህ ይልቅ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 3:5, 6) አዎን፣ አጉል እምነት ሰዎችን እስረኛ ያደርጋቸዋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ግን ነፃ ያወጣቸዋል።—ዮሐንስ 8:32

ለአምላክ ፍቅር እንዳለህ አሳይ

ከጨረቃ አዲስ ዓመት ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ልማዶችንና እምነቶችን አመጣጥ ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን በእነዚህ ልማዶች ላይ ተካፋይ ላለመሆን መወሰን ግን ሌላ ነገር ነው። የጨረቃ አዲስ ዓመት በዓል በሚያከብር ኅብረተሰብ ውስጥ የምትኖር ከሆነ ወይም ቤተሰቦችህ እንደ ባሕል በመቁጠር ይህን በዓል የሚያከብሩ ከሆነ ከባድ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅብሃል።

አንድ ሰው ግፊት እየተደረገበት በአቋሙ ጸንቶ መቆም ድፍረትና ቆራጥነት እንደሚጠይቅበት እሙን ነው። በእስያ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን “ከእኔ በቀር በአካባቢዬ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ አዲስ ዓመትን ስለሚያከብሩ በጣም ፈርቼ ነበር” በማለት ተናግራለች። ተጽዕኖውን እንድትቋቋም የረዳት ምን ነበር? “ጸንቼ ልቆም የቻልኩት ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር ስላዳበርኩ ብቻ ነው” ብላለች።—ማቴዎስ 10:32-38

አንተስ ለይሖዋ እንዲህ ያለ ከልብ የመነጨ ፍቅር አለህ? ይሖዋን እንድትወደው የሚያደርግህ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሕይወት የሰጠህ ይሖዋ አምላክ እንጂ አንድ ምስጢራዊ አምላክ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በሚመለከት “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህም ብርሃንን እናያለን” ይላል። (መዝሙር 36:9) የሚያስፈልግህን ነገር የሚያሟላልህና ደስተኛ ሕይወት እንድትመራ የሚያስችልህ የዕድል አምላክ ወይም የኩሽና አምላክ ሳይሆን ይሖዋ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 14:17፤ 17:28) አንተስ እሱን ትወደዋለህ? ይህን የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ አብዝቶ እንደሚባርክህ እርግጠኛ ሁን።—ማርቆስ 10:29, 30

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የጨረቃ አዲስ ዓመት የቻይናውያን አዲስ ዓመት ወይም የጸደይ በዓል ተብሎም ይጠራል፤ ይህ በዓል በቻይና ቹንዚየ፣ በቬትናም ተት፣ በኮሪያ ሶልነል እንዲሁም በቲቤት ሎሳር ይባላል።

^ አን.14 በዚህ ርዕስ ላይ የተገለጹት ልማዶች በእስያ ውስጥ ከአገር አገር ቢለያዩም ምንጫቸው ግን አንድ ነው። የበለጠ መረጃ ለማግኘት የታኅሣሥ 22, 1986 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 20-21 እንዲሁም የጥር 8, 1970 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 9-11 ላይ ያለውን ሐሳብ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ወዳጅ ዘመዶችን ማረጋጋት

አንድ የቤተሰብ አባል በጨረቃ አዲስ ዓመት በዓል ላይ መካፈሉን ሲያቆም ወዳጅ ዘመዶቹ ሊደነግጡ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ሊናደዱ፣ ሊጎዱ አልፎ ተርፎም እንደተካዱ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በቤተሰብ መካከል ያለውን አስደሳች ግንኙነት ጠብቆ ለመኖር ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል። በተለያየ የእስያ አገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች የሰጧቸውን የሚከተሉትን አስተያየቶች እንመልከት፦

ጂንግ፦ “አዲስ ዓመት ከመድረሱ በፊት ወደ ዘመዶቼ እሄድና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ በሆኑ ልማዶች ላይ የማልካፈልበትን ምክንያት በዘዴ እነግራቸዋለሁ። እምነታቸውን የሚያቃልል ምንም ነገር ላለማድረግ እጠነቀቃለሁ፤ እንዲሁም ለሚጠይቁኝ ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በአክብሮት እመልስላቸዋለሁ። ይህ ደግሞ ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ ረድቶኛል።”

ሊ፦ “አዲስ ዓመት ከመድረሱ በፊት ለባለቤቴ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ሕሊናዬን መስማት እንዳለብኝ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ በዘዴ ነገርኩት። በበዓሉ ሰሞን ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ብሄድ በዓሉን ባላከብርም እንኳ እሱ የሚያፍርበትን ምንም ነገር እንደማላደርግ ቃል ገባሁለት። የሚገርመው ነገር ቤተሰቡ የሞቱ ዘመዶቻቸውን በሚያመልክበት ቀን በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ወደ ሌላ አካባቢ ይዞኝ ሄደ።”

ሺየ፦ “ቤተሰቦቼን ከልብ እንደምወዳቸው ያረጋገጥኩላቸው ከመሆኑም በላይ የማምንባቸው ነገሮች የተሻልኩ ሰው እንደሚያደርገኝ ነገርኳቸው። ከዚያም እንደ ገርነት፣ ዘዴኛነትና ፍቅር ያሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ብርቱ ጥረት አደረግሁ። ውሎ አድሮ ሃይማኖቴን ማክበር ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስ አጥንቶ እውነተኛ ክርስቲያን ሆነ።”

ሚን፦ “ወላጆቼን አክብሮት በተሞላበት መንገድ ረጋ ብዬ አነጋገርኳቸው። ‘መልካም ዕድል’ እንደማልላቸው ከዚህ ይልቅ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ እንዲባርካቸው እንዲሁም ሰላምና ደስታ እንዲሰጣቸው ሁልጊዜ ስለ እነሱ እንደምጸልይ እነግራቸዋለሁ።”

ፎንግ፦ “ቤተሰቤን ለመጠየቅ የግድ አዲስ ዓመት መጠበቅ እንደማያስፈልገኝ ለወላጆቼ ነገርኳቸው። ቶሎ ቶሎ እየሄድኩ እጠይቃቸዋለሁ። ይህ ደግሞ ወላጆቼን በጣም ስላስደሰታቸው እኔን መንቀፍ ትተዋል። ታናሽ ወንድሜም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማር ፍላጎት አሳይቷል።”

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Panorama Stock/​age Fotostock