በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

ኢየሱስና አባቱ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

ኢየሱስና አባቱ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:30) አንዳንድ ሰዎች ይህን ጥቅስ ኢየሱስና አባቱ የሥላሴ ክፍል እንደሆኑ ለማስረዳት ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሲናገር እንደዚያ ማለቱ ነበር?

እስቲ መጀመሪያ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት። ኢየሱስ በቁጥር 25 ላይ ሥራዎቹን የሚያከናውነው በአባቱ ስም እንደሆነ ተናግሯል። ከቁጥር 27 እስከ 29 ደግሞ አባቱ ስለሰጠው ምሳሌያዊ በጎች ተናግሮ ነበር። ኢየሱስና አባቱ አንድ አካል ቢሆኑ ኖሮ እነዚህ ሁለት አባባሎች ምንም ትርጉም አይኖራቸውም ነበር። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ‘እኔና አባቴ በጣም ስለምንቀራረብ በጎቹን ከአባቴ እጅ ሊነጥቃቸው የሚችል እንደሌለ ሁሉ ከእኔም እጅ የሚነጥቃቸው የለም’ ማለቱ ነበር። ይህ ዓይነቱ አነጋገር አንድ ልጅ ለአባቱ ጠላት ‘አባቴን ነካህ ማለት እኔን ነካህ ማለት ነው’ ብሎ ከሚናገረው አባባል ጋር የሚመሳሰል ነው። አንድ ልጅ እንዲህ ብሎ ቢናገር ማንም ሰው ቢሆን ልጁና አባትየው አንድ አካል አላቸው ብሎ አያስብም። ይሁን እንጂ ማንም ሰው በልጁና በአባትየው መካከል ጠንካራ አንድነት እንዳለ በቀላሉ መረዳት ይችላል።

በተመሳሳይም ኢየሱስና አባቱ ይሖዋ አምላክ “አንድ” ናቸው ሲባል በዓላማና በአመለካከት ፍጹም የሆነ አንድነት አላቸው ማለት ነው። ኢየሱስ፣ እንደ ሰይጣን ዲያብሎስና እንደ መጀመሪያዎቹ ጥንዶች ማለትም እንደ አዳምና ሔዋን የአምላክን መመሪያ ችላ ብሎ በራሱ መመራት አልፈለገም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ወልድ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም። አብ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ወልድም በተመሳሳይ መንገድ ያንኑ ነገር ያደርጋል።”—ዮሐንስ 5:19፤ 14:10፤ 17:8

ይሁን እንጂ፣ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠንካራ አንድነት አላቸው ሲባል አንዱን ከሌላው መለየት አስቸጋሪ ነው ማለት አይደለም። ይሖዋና ኢየሱስ የራሳቸው የሆነ ባሕርያት ያላቸው ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው። ኢየሱስ የራሱ የሆነ ስሜት፣ አስተሳሰብና ተሞክሮ ያለው ከመሆኑም በላይ የፈለገውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለው። ያም ሆኖ ኢየሱስ ከራሱ ፈቃድ ይልቅ የአባቱን ፈቃድ ያስቀድም ነበር። ኢየሱስ በሉቃስ 22:42 ላይ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ ከአባቱ የተለየ ፈቃድ ባይኖረው ኖሮ ይህ አባባል ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር። ኢየሱስና አባቱ አንድ አካል ከሆኑ ለምን ወደ አምላክ ይጸልያል? እንዲሁም አባቱ ብቻ የሚያውቃቸው እሱ ግን የማያውቃቸው ነገሮች እንዳሉ ለምን በትሕትና ይናገራል?—ማቴዎስ 24:36

በበርካታ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥ የታቀፉ ሰዎች፣ እርስ በርሳቸው እንደሚጣሉና እንደሚደባደቡ ተደርገው የሚገለጹ አማልክትን ያመልካሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ክሮነስ የተባለው የጥንት ግሪካውያን አምላክ አባቱን ዩረነስን በኃይል ከሥልጣን እንዳስወገደና የራሱን ልጆች እንደበላ የሚናገር አፈ ታሪክ አለ። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በይሖዋ አምላክና በልጁ በኢየሱስ መካከል ካለው በፍቅር ላይ የተመሠረተ አንድነት ምንኛ የተለየ ነው! በይሖዋና በኢየሱስ መካከል ያለው አንድነት እነሱን ይበልጥ እንድንወዳቸው የሚያደርግ ነው። እንዲያውም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ካላቸው ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር አንድ የመሆን አስደናቂ መብት አለን። ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ጸልዮአል፦ “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው፤ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው [ነው]።”—ዮሐንስ 17:20, 21

በመሆኑም ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” ሲል ሚስጥራዊ ስለሆነው ሥላሴ መናገሩ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በሁለት አካላት መካከል ሊኖር ስለሚችል አስደናቂ አንድነት መናገሩ ነበር።