በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ራሳቸውን ለሚችሉበት ጊዜ ማዘጋጀት

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ራሳቸውን ለሚችሉበት ጊዜ ማዘጋጀት

“ከወንዶች ልጆቼ ጋር ማውራት ያስደስተኝ ነበር። የምናገረውን ነገር በጥሞና አዳምጠው ወዲያውኑ ተግባራዊ ያደርጉ ነበር። አሁን ግን በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስለሆኑ በሁሉም ነገር እንጋጫለን። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የመካፈል ፍላጎታቸው እንኳ ቀንሷል። ‘አሁን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መነጋገር ያስፈልገናል?’ ብለው ይጠይቃሉ። ልጆቼ ወደ ጉርምስና ዕድሜ ከመድረሳቸው በፊት፣ እንዲህ ያለውን ነገር በሌሎች ላይ ባየውም እንኳ በቤተሰቤ ውስጥ ያጋጥመኛል ብዬ በጭራሽ አስቤ አላውቅም።”—ረጂ *

ጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ አላችሁ? ካላችሁ በልጃችሁ ሕይወት ውስጥ በጣም አስደናቂ ለውጥ የሚከሰትበትን የእድገት ደረጃ የማየት አጋጣሚ አግኝታችኋል ማለት ነው። ይሁንና ይህ ዕድሜ በጣም አስጨናቂ ሊሆንባችሁም ይችላል። ቀጥሎ የተገለጹት ሁኔታዎች እናንተንም አጋጥመዋችሁ ይሆን?

  • ልጃችሁ ትንሽ ሳለ፣ ከወደብ ጋር እንደታሠረ ጀልባ ከእናንተ መራቅ አይፈልግም ነበር። አሁን ግን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ጉዞ ለመጀመር ካለው ጉጉት የተነሳ ገመዱን ለማስለቀቅ እየጎተተ ነው። ከሁኔታው እንደተረዳችሁት ልጃችሁ አብራችሁት እንድትጓዙ አልፈለገም።

  • ልጃችሁ ትንሽ በነበረችበት ጊዜ ከእናንተ የምትደብቀው ነገር አልነበራትም። አሁን ግን በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስለምትገኝ ከጓደኞቿ ጋር አንድ ‘ክበብ’ መሥርታለች። ከዚህም ሌላ፣ እናንተ የዚህ ክበብ አባላት እንድትሆኑ የፈለገች ሆኖ አልተሰማችሁም።

እናንተም በቤታችሁ ይህን የመሰለ ሁኔታ ካጋጠማቸሁ ልጃችሁ ሊለወጥ የማይችል ዓመፀኛ እየሆነ ነው ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። ‘ታዲያ ምን እየሆነ ነው’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጉርምስና ወቅት በልጃችሁ እድገት ላይ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና እንመልከት።

የጉርምስና ወቅት—ወሳኝ የሆነ የእድገት ደረጃ

አንድ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጋቸው በርካታ ነገሮች አሉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተራመደበትን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንደበቱ ቃል ያወጣበትን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት የሄደበትን ቀን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ወላጆች ልጃቸው አንድ የእድገት ደረጃ ላይ መድረሱ ያስደስታቸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ወላጆች ለማየት የሚጓጉለትን ነገር ማለትም የልጃቸውን እድገት የሚያሳዩ ናቸው።

አንዳንድ ወላጆች በደስታ ባይቀበሉትም የጉርምስና ጊዜም ራሱን የቻለ የእድገት ደረጃ ነው። እነዚህ ወላጆች ስጋት ያደረባቸው መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም። ደግሞስ የትኛው ወላጅ ነው ታዛዥ የነበረው ልጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነጭናጫ ጎረምሳ ሲሆን የማያስጨንቀው? ያም ሆኖ የጉርምስና ወቅት ወሳኝ የሆነ የእድገት ደረጃ ነው። በምን መንገድ?

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው “ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ” የሚሄድበት ቀን እንደሚመጣ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:24) የጉርምስና ወቅት፣ ልጃችሁ ከእናንተ ተለይቶ መኖር ለሚጀምርበት ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በዚያ ቀን ልጃችሁ ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ” ማለት መቻል አለበት።—1 ቆሮንቶስ 13:11

ልጃችሁም በጉርምስና ዕድሜው ወቅት የልጅነት ባሕርይውን እየተወ በራሱ የሚተማመን ብሎም ራሱን ችሎ ለመኖር ብቁ የሆነና ኃላፊነት የሚሰማው ጎልማሳ ወጣት ለመሆን ዝግጅት እያደረገ ነው። እንዲያውም አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ የጉርምስና ወቅት ልጆች ከወላጆቻቸው ለመለየት የሚሰናዱበት ወቅት እንደሆነ ተናግሯል።

እውነት ነው፣ “ትንሹ” ልጃችሁ ብዙም ሳይቆይ ራሱን ችሎ እንደሚኖር ስታስቡት ስጋት ሊያድርባችሁ ይችላል። እንዲህ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፦

  • “ልጄ መኝታ ክፍሉን እንኳ በሥርዓት መያዝ ካልቻለ ብቻውን መኖር ሲጀምር የሚመጡትን ኃላፊነቶች መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?”

  • “ልጄ ቤት እንድትገባ በተነገራት ሰዓት በመምጣት እምነት የሚጣልባት መሆን ካልቻለች ሥራ ስትይዝ እንዴት አድርጋ ነው የተሰጣትን ኃላፊነት በጊዜው ማከናወን የምትችለው?”

ተመሳሳይ ነገሮች እናንተንም የሚያስጨንቋችሁ ከሆነ የሚከተለውን ልብ በሉ፦ ራስን ችሎ መኖር፣ ልጃችሁ በአንድ እርምጃ የሚያልፈው በር ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የሚጓዝበት መንገድ ነው፤ ጉዞውን ለማጠናቀቅም ዓመታት ይፈጅበታል። በአሁኑ ጊዜ ግን “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” የሚለው ቃል እውነት መሆኑን ልጃችሁ በሚያደርገው ነገር እያያችሁ ነው።—ምሳሌ 22:15

ይሁንና ተገቢውን አመራር ካገኘ፣ ልጃችሁ የጉርምስና ዕድሜውን አልፎ ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል የማስተዋል ችሎታውን በማሠራት ያሠለጠነ’ ኃላፊነት የሚሰማው የበሰለ ወጣት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።—ዕብራውያን 5:14

ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ ቁልፍ ነጥቦች

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ በሚያደርጋቸው ነገሮች ኃላፊነት የሚሰማው ልጅ እንደሆነ ካሳየ፣ ተጨማሪ ነፃነት ልትሰጡት ትችላላችሁ?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን ራሱን ለሚችልበት ጊዜ ለማዘጋጀት ‘የማሰብ ችሎታውን’ እንዲያዳብር ልትረዱት ይገባል፤ ይህም እሱ ራሱ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ እንዲችል ያስታጥቀዋል። * (ሮም 12:1, 2) ቀጥሎ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይህን እንድታደርጉ ይረዷችኋል።

ፊልጵስዩስ 4:5፦ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጃችሁ አንድ ነገር ምናልባትም ቤት እንዲገባ የሚጠበቅበት ሰዓት እንዲሻሻልለት ጠየቃችሁ እንበል። ወዲያውኑ “አይሆንም” ብላችሁ ትመልሱለታላችሁ። ልጃችሁ እየተነጫነጨ “ለምንድን ነው አሁንም እንደ ሕፃን የምታዩኝ?” ይላል። “ሥራህ እንደ ሕፃን ስለሆነ ነዋ!” ብላችሁ ከመመለሳችሁ በፊት የሚከተለውን አስቡበት፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች፣ ማግኘት ከሚገባቸው በላይ ነፃነት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፤ ወላጆች የሚሰጡት ነፃነት ደግሞ በአብዛኛው መስጠት ከሚችሉት ያነሰ ነው። ታዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ ነፃነት መስጠት ትችሉ ይሆን? ቢያንስ ሁኔታውን በልጃችሁ ቦታ ሆናችሁ ለማየት ለምን አትሞክሩም?

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ለልጃችሁ የበለጠ ነፃነት መስጠት የምትችሉባቸው አንድ ወይም ሁለት ሁኔታዎችን ጻፉ። ከዚያም ለልጃችሁ ተጨማሪ ነፃነት እንደተሰጠው ግለጹለትና ነፃነቱን እንዴት እየተጠቀመበት እንዳለ እንደምትከታተሉም ንገሩት። ነፃነቱን በአግባቡ ከተጠቀመበት ከጊዜ በኋላ የበለጠ ነፃነት ሊሰጠው ይችላል። በአግባቡ ካልተጠቀመበት ግን የተሰጠው ነፃነት ይወሰድበታል።—ማቴዎስ 25:21

ቆላስይስ 3:21፦ “አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።”—አዲሱ መደበኛ ትርጉም። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመከታተል ይሞክራሉ። ውሎውንና የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ በጥብቅ ይከታተሉታል። ጓደኛ ይመርጡለታል እንዲሁም በስልክ ሲነጋገር ተደብቀው ያዳምጣሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው ዘዴ ወላጆች የሚፈልጉትን ውጤት የሚያስገኝ አይደለም። መፈናፈኛ ማሳጣት ልጁ ነፃ የሚወጣበትን መንገድ እንዲፈልግ ከመገፋፋት ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ጓደኞቹን ሁልጊዜ መተቸትም ይበልጥ እንዲወዳቸው ሊያደርገው ይችላል፤ በስልክ ሲያወራ ተደብቆ ማዳመጥም ቢሆን እናንተ ሳታውቁ ከጓደኞቹ ጋር የሚገናኝበትን ሌላ ዘዴ እንዲቀይስ ሊያነሳሳው ይችላል። ይበልጥ ጥብቅ ለመሆን በሞከራችሁ መጠን ልጃችሁ የዚያኑ ያህል ከቁጥጥራችሁ ውጭ እየሆነ ይሄዳል። ልጃችሁ ከእናንተ ጋር እያለ በራሱ ውሳኔ ማድረግን ካልተማረ፣ ራሱን ችሎ መኖር ሲጀምር እንዴት ውሳኔ ማድረግ ይችላል?

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከዚህ በኋላ ከልጃችሁ ጋር በአንድ ጉዳይ ላይ ስትነጋገሩ ውሳኔው ወይም ምርጫው ምን ዓይነት ስም ሊያሰጠው እንደሚችል ለማስረዳት ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ጓደኞቹን ከመተቸት ይልቅ “እገሌ አንድ ሕግ በመጣሱ ምክንያት ተይዞ ቢታሰር ይህ ሁኔታ ሌሎች ለአንተ ምን ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ይመስልሃል?” ብላችሁ ጠይቁት። ልጃችሁ የሚወስነው ውሳኔ ስሙ በመልካም እንዲነሳ ወይም ስሙ እንዲጎድፍ ሊያደርግ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዱት።—ምሳሌ 11:17, 22፤ 20:11

ኤፌሶን 6:4፦ “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።” ‘የይሖዋን አስተሳሰብ በውስጣቸው መቅረጽ’ እውነታውን ከመንገር ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ይህ ሲባል በድርጊቱ ላይ ለውጥ ማድረግ እንዲችል የልጁን አእምሮና አስተሳሰብ ለመማረክ መጣር ማለት ነው። ልጃችሁ በተለይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኝበት ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ወሳኝ ነው። አንድሬ የተባለ የልጆች አባት “ልጃችሁ ዕድሜው እየጨመረ በመጣ መጠን አቀራረባችሁም መለወጣችሁና አሳማኝ ምክንያት በማምጣት ለማስረዳት መሞከራችሁ የተሻለ ነው” በማለት ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:14

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ አንድ ጉዳይ ሲነሳ ልጃችሁ በእናንተ ቦታ፣ እናንተ ደግሞ በእሱ ቦታ ብትሆኑ ምን ምክር እንደሚሰጣችሁ ጠይቁት። የራሱን ሐሳብ የሚደግፍ ወይም የሚቃረን ምክንያት ለማግኘት ምርምር እንዲያደርግ አበረታቱት። ከሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በጉዳዩ ላይ እንደገና ተነጋገሩ።

ገላትያ 6:7፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” አንድን ትንሽ ልጅ ከክፍሉ ወይም ከቤት እንዳይወጣ በማድረግ ወይም የሚወደውን ነገር እንዳያደርግ በመከልከል መቅጣትና ማስተማር ይቻላል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝን ልጅ ግን ድርጊቱ የሚያስከትልበትን መዘዝ እንዲቀበል በማድረግ ማስተማር የተሻለ ነው።—ምሳሌ 6:27

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ዕዳውን በመክፈል ወይም መጥፎ ውጤት ሲያመጣ ለአስተማሪው ሰበብ በመደርደር ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ አታድርጉ። ድርጊቱ የሚያስከትልበትን ውጤት ይቅመስ፤ እንደዚያ ከሆነ ዘላቂ ትምህርት ሊያገኝ ይችላል።

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁ የጉርምስና ዕድሜውን ያለምንም ውጣ ውረድ፣ በሰላም አልፎ ጎልማሳ ሰው ቢሆንላችሁ ደስ ይላችሁ ይሆናል። ይሁንና ውጣ ውረድ የሌለበት የጉርምስና ዕድሜ የሚያሳልፉት ከስንት አንድ ናቸው። ያም ሆኖ የጉርምስና ዕድሜ ልጃችሁን ‘በሚሄድበት መንገድ ለማስተማር’ ግሩም አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። (ምሳሌ 22:6) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ደስተኛ ቤተሰብ ለመገንባት የሚያስችል ጽኑ መሠረት ይሆኑላችኋል።

^ አን.3 ስሙ ተለውጧል።

^ አን.19 በዚህ ርዕስ ውስጥ ልጆችን ስንጠቅስ በወንድ ጾታ የተጠቀምን ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለሴት ልጆችም ይሠራሉ።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦

ልጄ ራሱን ችሎ ከቤት ሲወጣ . . .

  • መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የማድረግ ልማድ ማዳበር

  • ጥሩ ምርጫ እና ውሳኔ ማድረግ፣

  • ከሌሎች ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ፣

  • ጤንነቱን መጠበቅ፣

  • ገንዘቡን በአግባቡ መያዝ፣

  • ቤቱን በሥርዓት መያዝና አስፈላጊውን እድሳት ማድረግ፣

  • በራሱ ተነሳሽነት ኃላፊነቶቹን መወጣት ይችላል?