በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሥቃያቸውን ተረድቼአለሁ’

‘ሥቃያቸውን ተረድቼአለሁ’

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ሥቃያቸውን ተረድቼአለሁ’

ዘፀአት 3:1-10

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው።” (ኢሳይያስ 6:3 NW) በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት ይሖዋ አምላክ በንጽሕናና በቅድስና ረገድ አቻ እንደማይገኝለት ይጠቁማሉ። ‘አምላክ ቅዱስ መሆኑ ለሰዎች ደንታ የሌለውና ሊቀረብ የማይችል እንዲሆን ያደርገው ይሆን? እንዲህ ያለ ቅዱስ አምላክ፣ ፍጽምና ለጎደለኝና ኃጢአተኛ ለሆንኩት ለእኔ በእርግጥ ሊያስብልኝ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዘፀአት 3:1-10 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን አምላክ ለሙሴ የተናገራቸውን የሚያጽናኑ ቃላት እስቲ እንመርምር።

በአንድ ወቅት ሙሴ በጎች እየጠበቀ ሳለ አንድ አስገራሚ ነገር ተመለከተ፤ በአቅራቢያው የነበረ አንድ ቍጥቋጦ በእሳት ቢያያዝም ‘አልተቃጠለም’ ነበር። (ቁጥር 2) ሙሴ በሁኔታው በጣም ስለተገረመ ነገሩን ለማጣራት ወደ ቁጥቋጦው ተጠጋ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በአንድ መልአክ አማካኝነት በእሳቱ መካከል ተገልጦ ሙሴን “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው። (ቁጥር 5) የሚነደው ቁጥቋጦ የአምላክን መገኘት ይወክል ስለነበር መሬቱ እንኳ ሳይቀር ቅዱስ ሆኖ ነበር!

ቅዱስ የሆነው አምላክ ሙሴን ለማነጋገር የተነሳሳበት ምክንያት ነበረው። እንዲህ ብሏል፦ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።” (ቁጥር 7) አምላክ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ያሰሙት የነበረውን የልመና ጩኸት ሰምቷል። ሥቃያቸው በእሱ ላይ የደረሰ ያህል ሆኖ ተሰምቶታል። አምላክ “ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ” በማለት እንደተናገረ ልብ በል። አንድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ “ተረድቼአለሁ” የሚለውን ቃል አስመልክቶ ሐሳብ ሲሰጥ “ይህ አገላለጽ የሌላን ሰው ስሜት መጋራትን፣ ማዘንንና መራራትን ያመለክታል” ብሏል። ይሖዋ ለሙሴ የተናገራቸው ቃላት ለሌሎች በጥልቅ የሚያስብ አምላክ እንደሆነ ያሳያሉ።

ታዲያ አምላክ ምን ያደርግ ይሆን? እንዲሁ በማዘንና በመራራት ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ እርምጃ ወስዷል። ሕዝቡን ከግብፅ ነፃ አውጥቶ “ማርና ወተት ወደምታፈሰው . . . ምድር” ለማስገባት ዓላማ ነበረው። (ቁጥር 8) ይሖዋ፣ ይህን ዓላማውን ዳር ለማድረስ ‘ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዲያወጣ’ ለሙሴ ተልእኮ ሰጠው። (ቁጥር 10) ሙሴም በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ ነፃ በማውጣት የተሰጠውን ተልእኮ በታማኝነት ተወጥቷል።

ይሖዋ አሁንም አልተለወጠም። በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹ፣ በእነሱ ላይ የሚደርሰውን ችግር እንደሚያይና ለእርዳታ የሚያሰሙትን ጩኸት እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። የሚደርስባቸውን መከራ በሚገባ ያውቃል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ አገልጋዮቹ በመራራት ብቻ አይወሰንም። ከዚህ ይልቅ ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ እነሱን ለመርዳት እርምጃ ይወስዳል፤ ‘ምክንያቱም ስለ እነሱ ያስባል።’—1 ጴጥሮስ 5:7

አምላክ ሩኅሩኅ መሆኑ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል። ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም በእሱ እርዳታ በተወሰነ ደረጃ ቅዱስ መሆን የምንችል ከመሆኑም ሌላ በእሱ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ይዘን መገኘት እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) በመንፈስ ጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ክርስቲያን፣ ሙሴ ከቁጥቋጦው ጋር በተያያዘ ስላጋጠመው ሁኔታ የሚናገረው ዘገባ አጽናንቷታል። እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “ይሖዋ መሬቱን እንኳ ቅዱስ ማድረግ ከቻለ እኔም የተስፋ ጭላንጭል ሊኖረኝ ይችላል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዜ በእጅጉ ረድቶኛል።”

ቅዱስ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ይበልጥ መማር ትፈልጋለህ? ይሖዋ ‘አፈጣጠራችንን ስለሚያውቅና ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስብ’ ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ይቻላል።—መዝሙር 103:14