በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

“ውድ ራኬል

የብርታት ምንጭ ስለሆንሽኝ በጣም አመሰግንሻለሁ። አንቺ ባታስተውይውም እንኳ ሰዎችን ለማበረታታት ያለሽ ፍላጎትና ደግነት የተሞላበት አነጋገርሽ በጣም ረድተውኛል።”—ጄኒፈር

ያልጠበቅከው የምሥጋና ደብዳቤ ደርሶህ ያውቃል? ከሆነ ተደስተህ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ደግሞም ሁላችንም ቢሆን በተፈጥሯችን ሰዎች አድናቆት ሲቸሩን ደስ ይለናል።—ማቴዎስ 25:19-23

አድናቆትን መግለጽ በሰጪውና በተቀባዩ መካከል ያለውን ዝምድና ይበልጥ ያጠናክራል። ከዚህም በላይ አንድ ሰው አድናቆቱን የሚገልጽ ከሆነ የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ እንደሚከተል ያሳያል። ኢየሱስ፣ ሰዎች ላከናወኑት መልካም ተግባር ሳያመሰግናቸው አያልፍም ነበር።—ማርቆስ 14:3-9፤ ሉቃስ 21:1-4

የሚያሳዝነው ግን ምስጋናቸውን በቃልም ሆነ በጽሑፍ የሚገልጹ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን” ሰዎች “የማያመሰግኑ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚታየው አመስጋኝ ያለመሆን መንፈስ እንዳይጋባብን ካልተጠነቀቅን እኛም አድናቆታችንን ከመግለጽ ልንቆጠብ እንችላለን።

ወላጆች፣ ልጆቻቸው አመስጋኝ እንዲሆኑ ለማሠልጠን ምን ማድረግ ይችላሉ? ማመስገን የሚገባንስ እነማንን ነው? በዙሪያችን ያሉ ሰዎች አመስጋኝ ባይሆኑም እንኳ ለሌሎች አድናቆታችንን መግለጽ ያለብን ለምንድን ነው?

በቤተሰብ ውስጥ

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማቅረብ ተግተው ይሠራሉ። ይሁንና አንዳንዴ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ጥረታቸውን እንደማያደንቁ ይሰማቸው ይሆናል። ታዲያ ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ? የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

(1) ምሳሌ መሆን። ልጆችን በማሠልጠን ረገድ በጣም ውጤታማ ከሆኑት ዘዴዎች መካከል አንዱ ምሳሌ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት እስራኤል ትኖር ስለነበረች አንዲት ትጉህ እናት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ልጆቿ ተነሥተው፤ ቡርክት ይሏታል።” ልጆቿ አመስጋኝ መሆን እንዳለባቸው የተማሩት ከማን ነው? ቀሪው የጥቅሱ ክፍል ‘ባሏም እንዲሁ ያመሰግናታል’ በማለት ፍንጭ ይሰጠናል። (ምሳሌ 31:28) በመሆኑም አንዳቸው ሌላውን የሚያመሰግኑ ወላጆች አድናቆትን መግለጽ ለተቀባዩ ደስታ እንደሚያስገኝለት፣ የቤተሰብን ግንኙነት እንደሚያጠናክርና የጉልምስና ምልክት እንደሆነ ልጆቻቸው እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል።

ስቲቨን የተባለ አንድ አባት “ባለቤቴ፣ እራት ስላዘጋጀችልን በማመስገን ለልጆቼ ምሳሌ ለመሆን እጥራለሁ” ብሏል። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ስቲቨን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሁለቱ ሴት ልጆቼ ይህንን ሁኔታ ከማስተዋላቸውም በላይ ሌሎችን ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን ይበልጥ ተገንዝበዋል።” ያገባችሁ ከሆናችሁ፣ የትዳር ጓደኛችሁ የተለመዱ የሚመስሉ ሥራዎችን በሚያከናውንበት ጊዜ አመስጋኝነታችሁን ትገልጹለታላችሁ? ልጆቻችሁ የሚጠበቅባቸውን ተግባር በሚፈጽሙበት ጊዜም እንኳ ታመሰግኗቸዋላችሁ?

(2) ማሠልጠን። የአመስጋኝነት መንፈስ ከአበባ ጋር ይመሳሰላል። ሁለቱም ቢሆኑ ጥሩ ውጤት እንዲያስገኙ ከተፈለገ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸው የአድናቆት መንፈስ እንዲያድርባቸውና አድናቆታቸውን ለሌሎች እንዲገልጹ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው? ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህንን ለማድረግ የሚያስችላቸውን አንድ ቁልፍ ነገር ጠቁሟል።—ምሳሌ 15:28

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ስጦታ ሲሰጣቸው የሰጣቸው ግለሰብ ባደረገው ጥረትና ባሳየው የልግስና መንፈስ ላይ እንዲያሰላስሉ ልታሠለጥኗቸው ትችላላችሁ? ለም አፈር ለአበባ ምቹ እንደሆነ ሁሉ ማሰላሰልም ልጆች የአድናቆት መንፈስ እንዲኖራቸው ጥሩ መሠረት ይሆናቸዋል። ሦስት ልጆችን ያሳደገችው ማሪያ እንዲህ ትላለች:- “ልጆቼ፣ ስጦታ ሲሰጣቸው ከስጦታው በስተጀርባ ያለውን ነገር ማለትም ግለሰቡ ይህን ያደረገው ስለሚያስብላቸው መሆኑን እንዲያስተውሉ እረዳቸዋለሁ፤ ይህን ማድረግ ግን ጊዜ ወስዶ ሁኔታውን ማብራራት ይጠይቃል። ሆኖም እንዲህ ማድረጉ አያስቆጭም።” ይህ ዓይነቱ ውይይት ልጆች አድናቆታቸውን ሲገልጹ ምን መናገር እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን አመስጋኞች መሆን ያለባቸው ለምን እንደሆነም ጭምር እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።

ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸው መልካም ነገሮችን የሚቀበሉት ስለሚገባቸው ብቻ እንዳልሆነ እንዲያስተውሉ ይረዷቸዋል። * በምሳሌ 29:21 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በአገልጋይና በጌታ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ ቢሆንም ከልጆች ጋር በተያያዘም ይሠራል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ሰው አገልጋዩን ከልጅነቱ ጀምሮ ቢያቀማጥል፣ የኋላ ኋላ [ልጁ] ሐዘን ያገኘዋል [“ምስጋና ቢስ ይሆናል፣” NW]።”

ትንንሽ ልጆች አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ማሠልጠን የሚቻለው እንዴት ነው? የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሊንዳ እንዲህ ብላለች:- “ልጆቻችን እኔና ባለቤቴ ካዘጋጀነው የምስጋና ደብዳቤ ጋር አብረን የምንልክላቸውን ሥዕል እንዲስሉ ወይም በምንልከው ካርድ ላይ ስማቸውን እንዲጽፉ በማድረግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እናበረታታቸዋለን።” እርግጥ ነው፣ እነዚህ ልጆች የሚስሉት ሥዕል ቀላልና የእጅ ጽሑፋቸውም ለማንበብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ልጆች እንዲህ ባለው ተግባር መሳተፋቸው በሕይወታቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

(3) መጽናት። ሁላችንም ብንሆን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ አለን። ይህ ደግሞ አመስጋኞች እንዳንሆን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (ዘፍጥረት 8:21፤ ማቴዎስ 15:19) ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮችን “በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ . . . እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው [ልበሱ]” በማለት ይመክራቸዋል።—ኤፌሶን 4:23, 24

ተሞክሮ ያካበቱ ወላጆች፣ ‘አዲሱን ሰው እንዲለብሱ’ ልጆቻቸውን መርዳት የመናገሩን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ያውቃሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስቲቨን “ሴቶች ልጆቻችን በራሳቸው ተነሳሽነት አመስጋኝነታቸውን እንዲገልጹ ማስተማር ብዙ ጊዜ ፈጅቶብናል” በማለት ተናግሯል። ሆኖም ስቲቨንና ባለቤቱ ተስፋ አልቆረጡም። ስቲቨን እንዲህ ብሏል:- “ከብዙ ልፋት በኋላ ልጆቻችን አመስጋኝነታቸውን መግለጽ ተማሩ። አሁን ለሰዎች አድናቆታቸውን ሲገልጹ ስንመለከት ኩራት ይሰማናል።”

ወዳጆቻችንን እና ጎረቤቶቻችንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

አንዳንድ ጊዜ፣ ለተደረገልን ነገር አድናቆት ቢኖረንም እንኳ ምስጋናችንን አንገልጽ ይሆናል። ይሁንና የተደረገልንን ነገር ማድነቅ ብቻ ሳይሆን አድናቆታችንን መግለጽ አስፈላጊ ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንድንችል በአንድ ወቅት የሥጋ ደዌ ይዟቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር በተያያዘ ኢየሱስ አጋጥሞት የነበረውን ሁኔታ እንመልከት።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ የሥጋ ደዌ ከያዛቸው አሥር ሰዎች ጋር ተገናኘ። መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ እንደሚከተለው ይላል:- “በታላቅ ድምፅ፣ ‘ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!’ አሉት። እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ ‘ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ’ አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።”—ሉቃስ 17:11-16

ኢየሱስ፣ ዘጠኙ ሰዎች ምስጋናቸውን ሳይገልጹ መቅረታቸውን ችላ ብሎ አልፎት ይሆን? ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ ‘የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?’”—ሉቃስ 17:17, 18

የሥጋ ደዌ ይዟቸው የነበሩት የተቀሩት ዘጠኝ ሰዎች ዓመጸኞች አልነበሩም። ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው በግልጽ የተናገሩ ሲሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ራሳቸውን ለካህናት ማሳየትን ጨምሮ ኢየሱስ የሰጣቸውን መመሪያዎች በፈቃደኝነት ታዘዋል። ኢየሱስ ላደረገላቸው መልካም ነገር ጥልቅ አድናቆት እንደነበራቸው ግልጽ ቢሆንም አመስጋኝነታቸውን ሳይገልጹ ቀርተዋል። ይህ ድርጊታቸው ክርስቶስን አሳዝኖታል። እኛስ? አንድ ሰው መልካም ነገር ሲያደርግልን ምስጋናችንን ለመግለጽ ወይም አድናቆታችንን የሚያሳይ ነገር ለማድረግ ፈጣኖች ነን?

መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር . . . ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5 NW) በመሆኑም ከልብ የመነጨ የአድናቆት መግለጫ መልካም ምግባር እንዳለን ብቻ ሳይሆን አፍቃሪዎች እንደሆን ያሳያል። በሥጋ ደዌ በሽታ ስለተያዙት ሰዎች የሚናገረው ታሪክ፣ ክርስቶስን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ብሔራቸው፣ ዘራቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ሆነ ምን ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ማሳየትና አድናቆታቸውን መግለጽ እንዳለባቸው ያስተምረናል።

እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ጎረቤቴን፣ የሥራ ባልደረባዬን፣ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን አሊያም ሐኪም ቤት፣ ሱቅ ወይም ሌላ ቦታ ያገኘሁትን ሰው ያመሰገንኩት መቼ ነው?’ በአንድ ወይም በሁለት ቀን ውሎህ ውስጥ ሰዎችን ‘አመሰግናለሁ’ ያልክባቸውን ወይም አድናቆትህን የሚገልጽ ተግባር የፈጸምክባቸውን ጊዜያት በወረቀት ላይ ለምን አትመዘግብም? እንዲህ ማድረግህ አድናቆትህን በመግለጽ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምትችልበትን አቅጣጫ ሊጠቁምህ ይችላል።

እርግጥ ነው፣ ከሁሉም በላይ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ “[የበጎ] ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ” ምንጭ ነው። (ያዕቆብ 1:17) አምላክ ያደረገልህን ነገር ለይተህ በመጥቀስ የታሰበበት የምስጋና ጸሎት ያቀረብከው መቼ ነው?—1 ተሰሎንቄ 5:17, 18

ሰዎች አመስጋኝ ባይሆኑም አድናቆታችንን ከመግለጽ መቆጠብ የሌለብን ለምንድን ነው?

አንዳንዶች ላደረግንላቸው መልካም ነገሮች አመስጋኝ ላይሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ሌሎች አመስጋኝ ባይሆኑም እንኳ አድናቆታችንን ከመግለጽ መቆጠብ የሌለብን ለምንድን ነው? እንዲህ እንድናደርግ ከሚገፋፉን ምክንያቶች መካከል እስቲ አንዱን ብቻ እንመልከት።

አመስጋኝ ላልሆኑ ሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ቸር የሆነው ፈጣሪያችንን፣ ይሖዋ አምላክን እንመስላለን። ብዙ ሰዎች ይሖዋ ላሳያቸው ፍቅር አድናቆት የሚጎድላቸው ቢሆኑም አምላክ ለእነሱ መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አላለም። (ሮሜ 5:8፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) “እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።” እኛም በዚህ አመስጋኝ ባልሆነ ዓለም ስንኖር ለሌሎች አድናቆታችንን ለመግለጽ የተቻለንን ያህል በመጣር “በሰማይ ላለው [አባታችን] ልጆች” መሆናችንን እናሳያለን።—ማቴዎስ 5:45

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 በርካታ ወላጆች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከታላቁ አስተማሪ ተማር (እንግሊዝኛ) የሚለውን መጽሐፍ ከልጆቻቸው ጋር ይወያዩበታል። ምዕራፍ 18 “ለተደረገልህ ነገር አስታውሰህ ታመሰግናለህ?” የሚል ርዕስ አለው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በአንድ ወይም በሁለት ቀን ውሎህ ውስጥ ሰዎችን ‘አመሰግናለሁ’ ያልክባቸውን ወይም አድናቆትህን የሚገልጽ ተግባር የፈጸምክባቸውን ጊዜያት ለማወቅ ሞክር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አመስጋኝ በመሆን ረገድ ለልጆቻችሁ ምሳሌ ሁኑ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንንሽ ልጆች እንኳ አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ሊሠለጥኑ ይችላሉ