በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ ትናንሾቹ ሰይጣኖች በመባል የሚታወቁ የወረበሎች ቡድን አባል የነበረ አንድ ሰው ሐቀኛና ትጉህ ሠራተኛ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በንግዱ ዓለም የተዋጣላት አንዲት ጃፓናዊት በሕይወቷ ውስጥ ዋነኛ ግብ አድርጋ ትመለከተው የነበረውን ሀብት ማሳደዷን ያቆመችው ለምንድን ነው? ስላደረገችውስ ለውጥ ምን ይሰማታል? የጦር መሣሪያ ነጋዴ የሆነን አንድ ሩሲያዊ፣ አትራፊ ሆኖም ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም ያነሳሳው ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ግለሰቦች የሚሉትን እንስማ።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ አድሪያን ፔሬዝ

ዕድሜ፦ 30

አገር፦ ሜክሲኮ

የኋላ ታሪክ፦ የወሮበላ ቡድን አባል

የቀድሞ ሕይወቴ፦ አሥራ ሦስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ቤተሰባችን የሜክሲኮ ግዛት ወደሆነችው ኤካቴፔክ ቴ ሞሬሎስ ከተማ ተዛወረ። በወቅቱ በከተማዋ ውስጥ በርካታ ወጣት ጥፋተኞች፣ ሥርዓት አልበኞችና የዕፅ ሱሰኞች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ እኔም ከልክ በላይ አልኮል መጠጣት፣ ንብረት ማበላሸትና የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም ጀመርኩ።

ከዚያም የትውልድ ከተማዬ ወደሆነችው ሳን ቪሴንቴ ተመለስን። ያም ሆኖ በዚያም በርካታ የዕፅ ሱሰኞች ነበሩ። ወጣቶች በየመንገዱ ሞተው ማየት የተለመደ ነበር። እኔም ትናንሾቹ ሰይጣኖች ተብለው የሚታወቁት የወረበሎች ቡድን አባል ሆንኩ። በስርቆት ተግባር ከመሠማራታችንም በላይ የዕፅ ሱሰኞች ነበርን። ሱሳችንን ለማርካት ስንልም እንደ አኳራጅና ማስቲሽ ያሉ ነገሮችን እናሸት ነበር። ብዙ ጊዜ ቤት እንዴት እንደደረስኩ የማላውቅ ሲሆን መንገድ ላይ የተኛሁባቸውም ጊዜያት ነበሩ። አንዳንድ ጓደኞቼ በስርቆትና በግድያ ወንጀል ተከሰው ወኅኒ ቤት ገብተዋል።

መጥፎ ተግባሮችን ብፈጽምም በአምላክ አምን ነበር። ከሚሰማኝ የሕሊና ወቀሳ ለመሸሽ ስል እንደ ፍኑተ መስቀል ባሉ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ እካፈል ነበር። ሥነ ሥርዓቱ እንዳለቀ ክርስቶስን ወክሎ ይጫወት የነበረውን ሰው ጨምሮ ሁላችንም በዓሉን  ምክንያት በማድረግ እስክንሰክር ድረስ እንጠጣ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በአሥራዎቹ ዕድሜዬ መገባደጃ ላይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። ሕይወቴ ዓላማ እንደሌለውና አኗኗሬን ካላስተካከልኩ የኋላ ኋላ አወዳደቄ እንደማያምር ተገነዘብኩ። ልቤን የነካው በገላትያ 6:8 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ ነው“ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።” ይህ ጥቅስ፣ ሕይወቴ ያማረ እንዲሆን ከፈለግሁ የወደፊቱን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መዝራት እንዳለብኝ እንዳስተውል ረድቶኛል።

መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ ስሄድ ይሖዋ ከዚህ ቀደም የሠራኋቸውን ኃጢአቶች ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነና በግለሰብ ደረጃ የሚያስብልኝ ሕያው አምላክ መሆኑን ተረዳሁ። ይሖዋ ጸሎትን እንደሚሰማ ከራሴ ተሞክሮ መገንዘብ ችያለሁ።

አኗኗሬን መለወጥ ቀላል አልነበረም። የወሮበላ ቡድኑን ትቶ መውጣት አስቸጋሪ ነበር። ከቡድኑ ጋር ያለኝን ግንኙነት ባቋርጥም አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ማለፍ አይፈቀድልኝም። አንዳንድ ጊዜ ከድሮ ጓደኞቼ መደበቅ ነበረብኝ፤ ምክንያቱም ካገኙኝ ወደ ቀድሞ ሕይወቴ እንድመለስ ጫና ያሳድሩብኛል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመንግሥት አዳራሽ መሰብሰብ ስጀምር ሰዎቹ አፍቃሪ መሆናቸውን ተመለከትኩ። እነዚህ ሰዎች ያላቸው ጠንካራ እምነትና የተማሩትን ነገር በተግባር ለማዋል የሚያደርጉትን ጥረት ሳስተውል እጅግ ተደነቅኩ። ቀድሞ ከነበርኩበት ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነበር።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ አሥር ዓመት ሆኖኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሕይወቴ ተግባራዊ ለማድረግ እጥራለሁ። በመሆኑም በቤተሰቤ ዘንድ አክብሮት ለማትረፍ ችያለሁ። አሁን፣ ትጉህ ሠራተኛ እንደሆንኩ አድርገው የሚመለከቱኝ ከመሆኑም በላይ እነሱንም በገንዘብ መደገፍ ችያለሁ። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን በአሁኑ ጊዜም የይሖዋ ምሥክር ሆናለች። አባቴም ቢሆን በአኗኗሩ ላይ ለውጥ እያደረገ ይገኛል። አብዛኞቹ የቤተሰቤ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም ያደረግኩትን ለውጥ ከተመለከቱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአንድን ሰው ሕይወት ሊለውጥ እንደሚችል አምነዋል።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ያዮኢ ናጋታኒ

ዕድሜ፦ 50

አገር፦ ጃፓን

የኋላ ታሪክ፦ የተዋጣላት ነጋዴ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት ተግባቢ የሆኑ ሰዎች በሚኖሩባት በአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ነበር። አባቴ አሥር ሠራተኞች ያሉት አንድ ትልቅ ሱቅ ነበረው። እናቴና አባቴ በሥራ የተወጠሩ ቢሆኑም ቤታችን ከሱቃችን አጠገብ ስለነበር ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም።

ከሦስት ሴቶች ልጆች መካከል ታላቋ እኔ ስሆን ገና ከልጅነቴ የቤተሰቡን ንግድ ለማንቀሳቀስ ሥልጠና ተሰጥቶኝ ነበር።  ትዳር የመሠረትኩት በልጅነቴ ነበር። ባንክ ቤት ይሠራ የነበረው ባለቤቴ የቤተሰባችንን ንግድ ለመርዳት ሲል ሥራውን ለቀቀ። ሦስት ልጆችን በላይ በላዩ ወለድን። እኔ ከጠዋት እስከ ማታ ሱቁ ውስጥ ስሠራ እናቴ ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ታከናውንና ልጆቹን ትንከባከብ ነበር። እንደዚያም ሆኖ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን የተወሰነ ጊዜ እናሳልፍ ነበር።

በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት ገበያው እየቀዘቀዘ ሲሄድ ድርጅታችን መክሰር ጀመረ። በመሆኑም ከዋናው መንገድ አጠገብ የሕንፃ መሣሪያ ሱቅ ለመክፈት ወሰንን። የሱቁን ግንባታ ከመጀመራችን በፊት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የነበረው አባቴ በድንገት ጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመርጋቱ ሳቢያ የመናገር ችሎታውን አጣ። በዚህም ምክንያት አዲሱን ሱቅ የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ። ባለቤቴ በድሮ ሱቃችን ውስጥ መሥራቱን ቀጠለ። ሕይወታችንም በጥድፊያ ተሞላ።

አዲሱ ሱቃችን ብዙ ትርፍ አስገኘልን። እኔም ባገኘሁት ውጤት በመኩራራት የበለጠ ስኬት ለማግኘት ሌት ተቀን መሥራት ጀመርኩ። ልጆቼን የምወድ ብሆንም የማስበው ስለ ሥራዬ ብቻ ነበር። ከባለቤቴ ጋር የምናወራው ከስንት አንዴ ሲሆን በዚህ ጊዜም እንጨቃጨቃለን። ያለብኝን ጭንቀት ለመርሳት ስል ከጓደኞቼና በሥራ ከምገናኛቸው ሰዎች ጋር በየዕለቱ ማለት ይቻላል ስጠጣ አመሻለሁ። የማደርገው ነገር ቢኖር መሥራት፣ መጠጣትና መተኛት ነበር። የተደላደለ ኑሮ እኖር ነበር፤ ሆኖም ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ከቀን ወደ ቀን ደስታ እየራቀኝ ይሄድ ጀመር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ሦስት ጥቅሶች በአኗኗሬ ላይ ለውጥ እንዳደርግ ረድተውኛል። በማቴዎስ 5:3 ላይ የሚገኘው “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና” የሚለው ሐሳብ ትርጉም ስረዳ አለቀስኩ። በንግዱ ዓለም ስኬታማ መሆንና የጓደኞቼን አድናቆት ማትረፍ የቻልኩ ብሆንም የባዶነት ስሜት ይሰማኝ የነበረው ለምን እንደሆነ ይህ ጥቅስ እንድገነዘብ ረድቶኛል። አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ የሚያገኘው በመንፈሳዊ ድሃ መሆኑን አውቆ ያንን ፍላጎቱን ማርካት ሲችል መሆኑን ተረዳሁ።

በጃፓን የኢኮኖሚ ቀውስ በተከሰተ ጊዜ ወዳጆቼ የገጠማቸው ሁኔታ 1 ጢሞቴዎስ 6:9 እውነት መሆኑን አስገንዝቦኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል“ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ።” ከዚህ በተጨማሪም በማቴዎስ 6:24 ላይ ኢየሱስ፣ “እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም” በማለት የተናገረው ሐሳብ ለእኔ እንደተጻፈ ሆኖ ስለተሰማኝ በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ለማድረግ ወሰንኩ።

ወላጆቼን፣ ባለቤቴንና ልጆቼን ችላ ብዬ እንደነበር ተገነዘብኩ። በተጨማሪም መጥፎ ባሕርይ አዳብሬ ነበር። ዕብሪተኛ፣ ግልፍተኛና ትዕግሥት የለሽ ነበርኩ። መጀመሪያ ላይ ባሕርዬን መለወጥና ክርስቲያን መሆን የምችል አልመሰለኝም ነበር። ያም ሆኖ ልጆቼን ከልብ እወዳቸው ስለነበር ከቤተሰቤ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ሳደርግ ልጆቼም ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡኝ አስተዋልኩ። ከልጆቼ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ብሎም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዣቸው መሄድ ጀመርኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ የሕይወትን ዓላማ ማወቄ እንዲሁም አምላክን የሚያስደስት ሕይወት በመምራት እሱን ማገልገል መቻሌ ውስጣዊ እርካታና ደስታ አስገኝቶልኛል። ለሥራዬ ስል የቤተሰቤን ሕይወት ችላ ማለቴን በማቆሜ ለራሴ ያለኝ ግምት ጥሩ እየሆነ ሄደ።

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ተግባራዊ ሳደርግ ባሕርዬ እየተሻሻለ መሄዱን ያስተዋለችው እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ክርስቲያን ለመሆን ተገፋፋች። አባቴም ሆነ ባለቤቴ ውሳኔያችንን ባለመቃወማቸው ደስተኛ ነኝ። ከልጆቼ ጋር ይበልጥ የተቀራረብኩ ሲሆን አሁን ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት አለኝ።

 አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ሚካኢል ዙየፍ

ዕድሜ፦ 51

አገር፦ ሩሲያ

የኋላ ታሪክ፦ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ነጋዴ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት ለም በሆነችው የክራስኖጎርስክ ከተማ ነበር። ከከተማዋ በስተ ደቡብ የሞስኮ ወንዝ ይገኛል። በስተ ምዕራብና በስተ ሰሜን የሚገኙት አካባቢዎች በደን የተሸፈኑ ናቸው።

ልጅ ሳለሁ መደባደብና በጦር መሣሪያዎች መጫወት እወድ ነበር። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ብዙ ሰዓታትን አሳልፍ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሕገ ወጥ መሣሪያዎችን፣ ጥይቶችንና ጩቤዎችን እሠራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን መነገድን ሥራዬ ብዬ ተያያዝኩት። የሠራኋቸውን መሣሪያዎች ለወንጀለኞች በመሸጥ ረገድ በደንብ የተደራጀሁና የተዋጣልኝ ነጋዴ ነበርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1990ዎቹ መባቻ ላይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ በእነሱ ላይ እምነት አልነበረኝም። ሰዎችን በጥያቄ የሚያሰለቹ ይመስለኝ ነበር።

አንድ ቀን፣ አንድ የይሖዋ ምሥክር በሮሜ 14:12 ላይ የሚገኘውን “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” የሚለውን ሐሳብ አነበበልኝ። ከዚያም ለአምላክ ምን መልስ እንደምሰጥ ማሰብ ጀመርኩ። ይህ ጥቅስ አምላክ ከእኔ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት እንዳደርግ አነሳሳኝ።

በቈላስይስ 3:5-10 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት አደረግሁ“ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህምዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ . . . ቍጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። . . . አዲሱን ሰው [ልበሱ]።”

እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ውድ የሆኑ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን አስወግጄ የነበረ ቢሆንም የቀድሞ “ደንበኞቼ” ጠቀም ባለ ገንዘብ መሣሪያዎችን እንድሸጥላቸው ይወተውቱኝ ነበር። እንዲሁም ሰዎች ሲሰድቡኝ ችዬ ማለፍ ይከብደኝ ነበር። ይሁንና አምላክና ክርስቶስ ስላሳዩኝ ፍቅር ስማር እነሱን መውደድ ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ አጠና የነበረ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እገኝ እንዲሁም አምላክ እንዲረዳኝ እጸልይ ነበር።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ክርስቲያን ወንድሞቼ በሰጡኝ እርዳታ አማካኝነት ከብዙ ትግል በኋላ ባሕርዬን ማሻሻል ቻልኩ። ይሖዋ አምላክ ለእያንዳንዳችን ሌላው ቀርቶ ለሞቱ ሰዎች እንደሚያስብ ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) የይሖዋ ምሥክሮች ቅኖች፣ እምነት የሚጣልባቸው እንዲሁም ለአምላክ ታማኞች መሆናቸው አስደነቀኝ። ከልብ የመነጨ አሳቢነት ስላሳዩኝ አመስጋኝ ነኝ።

በመጀመሪያ ላይ፣ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ አንዳንዶቹ አዲስ እምነት በመያዜ ተቃውመውኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን በወንጀል ተግባር ከመሠማራት ይልቅ ሃይማኖተኛ መሆኔ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸው ጀመር። አሁን ሕይወቴ የጦር መሣሪያዎችን በመሸጥ ላይ ሳይሆን ሰዎችን የሰላም አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ በመርዳት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሕሊና ወቀሳ ለመሸሽ ስል በካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ እካፈል ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተደላደለ ኑሮ የነበረኝ ቢሆንም ደስተኛ አልነበርኩም